ዘለንስኪ ‹‹ዲፕሎማሲ ውድቀት ውስጥ ገብቷል›› ሲሉ ወቀሱ

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ በካናዳ ሲካሄድ የሰነበተው የ‹‹ቡድን ሰባት›› አባል ሀገራት የመሪዎች ስብሰባ ለዩክሬን የጋራ የድጋፍ መግለጫ ሳያወጣ በመጠናቀቁ ‹‹ዲፕሎማሲ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበታል›› ሲሉ ወቀሱ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስብሰባውን አቋርጠው ወደ ዋሺንግተን በመመለሳቸው እና ፕሬዚዳንቱ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን በሰላም ስምምነት ለመቋጨት ፍላጎት ስላላቸው ሩሲያን የሚያወግዝ መግለጫ ሳይወጣ እንደቀረ እና ትራምፕና ዘለንስኪም እንዳልተገናኙ ተዘግቧል።

ዘለንስኪ በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ከካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያና ጃፓን መሪዎችና ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ ጋር ተወያይተዋል። ከውይይቱ በኋላም ‹‹አሁን ዲፕሎማሲ ውድቀት ውስጥ ገብቷል›› በማለት ተናግረዋል። ሌሎቹ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያላቸውን ተፅዕኖ ተጠቅመው ጦርነቱ መቋጫ እንዲያገኝ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋቸዋል።

ለዩክሬን የጋራ የድጋፍ መግለጫ ለማውጣት ቢታቀድም ከአሜሪካ ተቃውሞ እንደገጠመውና እንደቀረ አንድ የካናዳ ባለሥልጣን ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒይ ቃል አቀባይ ኤሚሊ ዊሊያምስ ግን በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ዩክሬንን የተመለከተ የመግለጫ ረቂቅ ሃሳብ ለመሪዎቹ እንዳልቀረበ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር የሚያደርጉትን ንግግር ለመቀጠል ባላቸው ፍላጎት ምክንያት ዩክሬንን የተመለከተ የጋራ መግለጫ የማዘጋጀት ሃሳብ ፈፅሞ እንዳልነበር ሌላ የካናዳ ባለሥልጣን ገልፀዋል። ‹‹በጉዳዩ ላይ ሁሉንም የቡድን ሰባት አባል ሀገራትን የሚያስማማ አገላለጽ እንደማይኖር ግልጽ ነው›› ብለዋል።

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በተካሄዱት የ‹‹ቡድን ሰባት›› ስብሰባዎች የቡድኑ አባላት ሩሲያን የሚያወግዙና ዩክሬንን የሚደግፉ መግለጫዎችን ሲያወጡ እንደነበር ይታወቃል። ዘንድሮ ግን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስብሰባውን ሳያልቅ ወደ ዋሺንግተን በመመለሳቸው እና ፕሬዚዳንቱ ከሩሲያ አቻቸው ጋር የሚያደርጉትን ንግግር በመቀጠል ጦርነቱን በሰላም ስምምነት ለመቋጨት ባላቸው ፍላጎት ምክንያት ሩሲያን የሚያወግዝና ዩክሬንን የሚደግፍ የጋራ መግለጫ ሳይወጣ ቀርቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የስብስቡ አባል የነበረችው ሩሲያ ከቡድኑ እንድትወጣ መደረጉ ትክክል እንዳልሆነም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ተናግረዋል። ሩሲያ እ.አ.አ ከ1998 ጀምሮ የቡድኑ አባል ሆና ቆይታ እንደነበር እና እ.አ.አ በ2014 ክሪሚያን ከዩክሬን ነጥቃ ወደ ግዛቷ በመቀላቀሏ ከቡድኑ መታገዷ ይታወሳል።

የኢራን እና የእሥራኤል ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ እየተካሄደ ያለውን የቡድን 7 ጉባኤ ከመጠናቀቁ በፊት አቋርጠው መመለሳቸው ይታወሳል። ፕሬዚዳንቱ ጉባኤው ከመጠናቀቁ በፊት ቀድመው ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው ምክንያት ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ እና ከሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር ታቅደው የነበሩ ውይይቶች አልተካሄዱም።

ዋይት ሐውስ ‹‹በኢራን እና በእሥራኤል መካከል እየተባባሰ ከመጣው ግጭት ጋር ተያይዞ ፕሬዚዳንቱ ወደ ዋሽንግተን መመለስ አለባቸው›› ሲል አስታውቆ ነበር። ትራምፕ ‹‹ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ቀደም ብዬ መመለስ አለብኝ›› ሲሉ ወደ ዋሽንግተን የመመለሳቸውን ምክንያት ለትልቅ ጉዳይ መሆኑን እንደተናገሩ እና የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤትም እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውም ይታወሳል። ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያንና ጃፓን የሚገኙበት የቡድን 7 ሀገራት መሪዎች ስብሰባ ትራምፕ ጉባኤውን ሳያጠናቅቁ ቀድመው መሄዳቸውን እንደሚረዱት ገልጸዋል።

ከአጋሮች ተጨማሪ ድጋፍ ለመጠየቅ እና ለሰላም ድርድር ዝግጁ እንደሆኑ ለመግለጽ ወደ ካናዳ የተጓዙት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ፣ ከካናዳ የአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ አግኝተዋል። ከወታደራዊ ድጋፉ በተጨማሪ ካናዳ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ የፋይናንስ ማዕቀቦችን እንደምትጥል አስታውቃለች።

51ኛው የ‹‹ቡድን ሰባት›› (G7) አባል ሀገራት ጉባዔ በካናዳ፣ አልበርታ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ካናናስኪስ ከተማ ተካሂዷል። በጉባኤው የስብስቡ አባላት የሆኑት የአሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ኢጣሊያ እና ካናዳ መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ የሜክሲኮ፣ የሕንድ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የዩክሬን፣ የአውስትራሊያ፣ የብራዚል፣ የኢንዶኔዥያና የደቡብ ኮሪያ መሪዎችም ከካናዳ ግብዣ እንደቀረበላቸው የሚታወስ ነው።

የዘንድሮው ጉባኤ፣ ከወቅታዊ ጂኦ ፖለቲካዊና የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች አንፃር ጉባኤው በውጥረት የተሞላና የተራራቁ ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት ስብሰባ ሊሆን እንደሚችል ሲነገር ቆይቷል። ጉባኤው የመካከለኛው ምሥራቅ ባላንጣዎቹ እስራኤልና ኢራን ውጊያ እያደረጉ ባለበት እና የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ በመጣላቸው አስቸጋሪ የንግድ ድርድሮች በሚደረጉበት ወቅት የተካሄደ እንደሆነ ይታወቃል።

‹‹በመላው ዓለም ያሉ ማኅበረሰቦችን መጠበቅ፣ የኃይል መሠረተ ልማት ደኅንነትን ማረጋገጥና ዲጂታል ሽግግርን ማፋጠን እና የወደፊት ትብብሮችን መገንባትና ማጠናከር›› የሚሉ ዋና ዋና ተግባራትን ማዕከል አድርጎ ተካሂዷል በተባለው በዘንድሮው ጉባኤ፤ የሩሲያ-ዩክሬን እንዲሁም የእሥራኤል-ኢራን ጦርነት፣ የቻይና ተፅዕኖ እና ዓለም አቀፍ ንግድም በስብሰባው ትኩረት አግኝተዋል፤ ቻይናም ስሟ ተደጋግሞ ተነስቷል።

‹‹ቡድን ሰባት›› የሚባለው በኢኮኖሚያቸው የበለፀጉ ሀገራት ስብስብ የምጣኔ ሀብት አቅም ከዓለም አጠቃላይ ምርት 44 በመቶውን እንዲሁም ከዓለም ሕዝብ ደግሞ 10 በመቶውን ይሸፍናል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You