
አዲስ አበባ በተለምዶ ጎተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባው “አዲስ ቱሞሮው” ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የሚያከናውኑት ነው። ግንባታው የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ ሞሎች፣ የንግድ ማዕከላትና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያካተተ ነው።
“አዲስ ቱሞሮው” ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለመዲናዋ አዲስ ገፅታ የሚያላብስ፣ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያጎላ፣ ተጨማሪ የውበት ምንጭ የሚሆን፣ ለነዋሪዎች ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥር፣ ንግድን የሚያሳልጥ፣ ትልቅ ዓለም አቀፍ የግብይት ማዕከል እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከትናንት በስቲያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ጋር በአጋርነት የሚያስገነባው የአዲስ ቱሞሮ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የምዕራፍ አንድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የሽያጭ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በምዕራፍ አንድ የግንባታ ሂደቱ አፓርትመንት እንዲሁም የንግድ ተቋማትን አጣምሮ በ45 ሺህ ሜትር ስኩዌር ስፍራ ላይ የሚገነባ ሲሆን በዚህም መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍቃደኛ ከሆኑ አምስት ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስምምነት ተፈፅሟል። ከዚህም ባለፈ የአፓርትመንት ቤቶች ሽያጭ ተከናውኗል።
የቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ) የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ዌይ ዣንግ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ኩባንያው በ 1990 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የገባ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት በሀገሪቱ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ችሏል።
ኢኮኖሚክ ዞኑ የኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማትና የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር የሚጣጣም ለአዲስ አበባና ለኢትዮጵያ ልማት አይነተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃ የሁለቱን ሀገራት አጋርነት የሚያጎለብት እንዲሁም ወዳጅነታቸውን የሚያጠነክር መሆኑንም ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱን በታለመለት ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በቂ ዝግጁነት አለ ያሉት ሚስተር ዌይ፤ ግንባታው ለከተማዋ አዲስ ውበት የሚያላብስ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንደሚገነባ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ዘለቀ ዋኬኔ በበኩላቸው፤ የአዲስ ቱሞሮ ፕሮጀክት እየተለወጠች ላለችው አዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነቷን የምትመጥን ከተማ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። የአዲስ ቱሞሮ ፕሮጀክትም ይህንን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰዋል።
አዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በአዲስ አበባ ጎተራ አካባቢ የሚገነባ ሲሆን ግንባታው በአራት ዞን ተከፍሎ የሚለማ ነው። ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የንግድ ዞን፣ የትምህርት እና የባህል ዞን፣ የፋይናንስና ቢዝነስ ዞን እንዲሁም ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ዞን ተብሎ እንደተከፋፈለም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታን ነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግሥት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ ለማድረግ በርካታ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ነው። በዚህ ረገድ ሶስት አሠራሮችን እንደሚከተል ጠቅሰው፤ አንደኛው በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚለሙ ሥራዎች ናቸው። የአዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ፕሮጀክት ለዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህና ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶችም የነገዋን የአዲስ አበባ አዲስ መልክ የሚቀይሩና ለኑሮ ምቹ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው አብራርተዋል። ሌላኛው ሥራ በመንግሥት የሚከናወነው የኮሪዶር ልማት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የኮሪዶር ልማት በሁሉም አካባቢዎች ፍትሃዊና ተመሳሳይ ልማት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለማስተሳሰር ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ በግሉ ዘርፍ የሚከናወነው ሥራም ከተማዋን ለመቀየር የሚያግዝ ሶስተኛው አሠራር መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባን ለመቀየር መንግሥት እየተከተለ ባለው የፖለቲካ እሳቤ “ከሥራ ውጭ ህልማችንን የምንፈታበት ምንም ነገር የለም” በሚል መሆኑን ገልጸው፤ የከተማዋ ነዋሪዎችም በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ከመጠቀም ባለፈ በባለቤትነት እንዲንከባከቡና እንዲጠብቁ በወቅቱ ማስገንዘባቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም