
አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ 49 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ለውጭ ሀገራት ከቀረበ ኃይል ሽያጭ 85 ነጥብ 34 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘቱንም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 99 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 85 ነጥብ 34 ሚሊዮን ዶላር ሽያጭ ተከናውኗል፡፡
ወደ ጂቡቲ 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ 20 ነጥብ 39 ሚሊዮን ዶላር ፣ ሱዳን 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ታቅዶ 860 ሺህ ዶላር ብቻ ተገኝቷል፡፡ ኬንያ 63 ነጥብ 96 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 64 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ተቋሙ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ሀገራት የኃይል ሽያጭ 47 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር
አስታውሰው፤ 49 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማግኘት ችሏል፡፡ ይህም ከእቅድ በላይ 103 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ለውጭ ሀገራት ኃይል ሽያጭ መቀነስ በሱዳን የሚስተዋለውን የሰላም እጦት ተከትሎ በመሠረተ ልማቶቻቸው ላይ የደረሰው ጉዳት በዋናነት እንደሚቀንስ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
ከሀገር ውስጥ ደንበኞች መካከል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከቀረበው ኃይል 12 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር ለመሸጥ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፤ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በማግኘት የእቅዱን 94 ነጥብ 16 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡
የከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎችም አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ፤ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ማግኘት መቻሉንም ጨምረው ገልጸው፤ ለኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ከተሸጠ ኃይልም 35 ሚሊዮን ብር ታቅዶ፣ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በጥቅሉ ሲታይ ከኃይል ሽያጭ የተገኘው ገቢ ከእቅዱ በአራት በመቶ ብልጫ ያለው ነው ያሉት አቶ ሞገስ፤ ለውጤቱ መገኘት የኃይል ማመንጨት አቅም መጨመር እና የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉ ተጠቃሽ ምክንያች መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም