
አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን አቅም ለመገንባት በትኩረት እየሠራች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡ ባለፉት ዓመታት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተከናወኑ ሥራዎች ጉልህ ስኬቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያዘጋጁት ‹‹የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ETEX-2025›› ትናንት በአዲስ አበባ በተጀመረበት ወቅት እንዳመላከቱት፡– ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ሂደት ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን አቅም ለመገንባት የሚያስችላት ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ፣ በማስተዳደር እና ጥበቃ በማድረግ የቴክኖሎጂውን ሥነ–ምህዳር ለማስፋፋት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ ዲጂታል ኢትዮ ጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቴክኖሎጂን ለማሳደግ ትርጉም ያለው ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ተለዋዋጩን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት ሁለንተናዊ ደህንነትንና የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል። ቀጣይነት ያለውና ሁሉ አቀፍ አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ቴክኖሎጂ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂን ከቁልፍ መሠረተ ልማቶች ውስጥ በማካተት እየሠራች መሆኑን አመላክተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የዲጂታል የክፍያ አማራጮችን ማስፋፋትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ይህ ኤክስፖ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማሳያ መሆኑን አንስተዋል። በቀጣይም ተተኪው ትውልድ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ንቁ እና ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወቱ ማነቃቃት የሚያስችል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የምትመኘውን ዕድገት እውን ለማድረግ ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ዲጂታል ቴክኖሎጂው ትልቅ ሚና አለው። ለመጪው ትውልድ የምትሆን ሀገርን ለማቆየት አርተፊሻል ኢንተለጀንስን የመሰሉ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን በራሳችን ሁኔታ መጠቀም አስፈላጊ ነው።
አሁን ላይ የዓለም ሀገራት በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ኤክስፖው የአፍሪካ ሀገራትም ከዓለም ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን በትብብር ለመሥራት እና ልምድ ለመለዋወጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካን በቴክኖሎጂ ከዓለም ጋር የሚያስተሳስር የዲጂታል መሠረተ ልማት መገንባት ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ይህ ደግሞ ከአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ጋር የሚሄድ ነው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትግስት ሀሚድ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ETEX-2025 በምስራቅ አፍሪካ ትልቁና የመጀመሪያው ነው ብለዋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ አስደናቂ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። በዚህም በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በጤና ፣ ደህንነት እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመልክተዋል።
የአይሲቲ ዘርፉ ከአምስቱ ቁልፍ የልማት ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን ቀርጻ እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ አይሲቲ መሪ ሆኖ ለሁሉም ሥነ ምህዳር እንደሚያገለግል ከማድረግ አንጻር አይነተኛ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በሳይበር ደህንነት፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በፋይናንስና ቴክኖሎጂ ( ፊንቴክ)፣ በቴክኖሎጂ ትምህርት እና በስማርት ሲቲን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አድርጎ እንደሚካሄድ የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ በኤክስፖው ከ10 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የሚጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ETEX-2025›› ከግንቦት 8 እስከ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም