የትግራይ ሕዝብ የጥፋት መንገድን በግልጽ እና በአደባባይ የሚቃወምበት ወቅት አሁን ነው!

በምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ሕወሓት ከነጻ አውጪ ግንባርነት ሀገር እስከ መምራት የደረሰ የ50 ዓመት ጉዞ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው ። በዚህ ረጅም ዘመን ባስቆጠረው የህልውና ዘመኑ ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍሏል። በተለይም ከውልደቱ ጀምሮ የትግራይን ሕዝብ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በትግሉ ወቅት በነጻነት እና በዴሞክራሲ ስም በአስር ሺዎች የሚጠጉ የክልሉ ተወላጆች ለሞት እና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል ።

ለአስራ ሰባት ዓመታት ባደረገው የትጥቅ ትግል ክልሉ የጦርነት አውድማ ሆኗል ፤ በዚህም ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት ደርሷል። የመንግሥት ሥልጣን ከያዘም በኋላ በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ክልሉ እና የክልሉ ሕዝብ የጦርነቱ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ነበር። የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖርም ከፍ ያለ የሥነልቦና ጫና ፈጥሮበት ቆይቷል።

ሕወሓት ሀገርን አንደ ሀገር ሲመራ በቆየባቸው 27 ዓመታት ውስጥ በተፈጠሩ ሕዝባዊ ቅሬታዎች፤ ሀገራዊ ለውጥ ተከስቶ ከሥልጣን ተወግዷል ። በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የተባለ መንግሥት በሕጋዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን መጥቷል፤ እንደ ሀገርም ተስፋ ሰጪ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተደርጓል።

ሕወሓት ይህን ተስፋ ሰጪ የፖለቲካ ሽግግር ለማደናቀፍ፤ ገና ከጅምሩ ከመሀል ሀገር ነቅሎ ወደ መቀሌ በመግባት ሰፊ ሙከራዎች አድርጓል። ለውጡ ይዞት የመጣውን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንደማነስ ቆጥሮ በብዙ ፉከራ እና ቀረርቶ ሀገር እና ሕዝብን ብዙ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈለ የጦርነት ግጭት ውስጥ ገብቷል።

ጦርነቱ እንደ ሀገር ከፈጠረው ውድመት ውጪ ፤ ለትግራይ ሕዝብ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖ ከቀደሙት ጊዜያት የከፋ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አምራች፤ ለሀገር እና ለሕዝብ ተስፋ የሆኑ የትግራይ ወጣቶችን ጠብመንጃ አሸክሞ ተጨማሪ ሀገራዊ የእልቂት ትርክት ፈጥሯል። ክልሉን ፤ ከክልሉም አልፎ አጎራባች ክልሎችን የግጭት ማዕከል አድርጓል።

በዚህም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችን ለሞት እና ለአካል ጉድለት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል። የክልሉን ሕዝብ ለከፋ የኢኮኖሚ ውድቀት ፤ በቢሊዮን የሚገመት የሀገር ሀብት ለውድመት ዳርጓል። ብዙዎችን ከተረጋጋ ሕይወታቸው አውጥቶ ጠባቂ የሆኑበትን ፤ ቀድመው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ይመሩ የነበሩትን የከፋ ችግር ውስጥ ከቷል።

ጦርነቱ በመንግሥት አርቆ አሳቢነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላም ፤ ስምምነቱ ምን ያህል የራሱን ህልውና ሳይቀር እንደታደገ የአደባባይ ሚስጥር እንደሆነ እየታወቀ ፤ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዳይሆን ደንቃራ ሆኖ ቆይቷል። በስምምነቱ መሠረት የተዋቀረው የጊዜያዊ አስተዳደር የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ በማድረግ በስምምነቱ ተስፋ የተደረጉ የሰላም ፤ የተሀድሶ እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዳይከናወኑ አድርገዋል።

በክልሉ ሕጋዊ ሥርዓት ሰፍኖ ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ እንዳይመለስ ፤ በእብሪት እና በማን አለብኝነት ፤ እራሱን ከሕግ እና ሥርዓት በላይ አድርጎ በመቁጠር፤ ሕዝቡ እንደ ሕዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እና የዘላቂ ሰላም ተስፋ በማደብዘዝ ተመልሶ ወደ ፉከራ እና ቀረርቶ ከገባ ውሎ አድሯል። ሕዝቡ ስለ ሰላም ድምጹን ከፍ አድርጎ እየጮኸ ባለበት ሁኔታ ከጥፋት እና እልቂት ውጪ ለትግራይ ሕዝብ አንዳች የረባ ነገር ለማያመጣ ጦርነት ራሱን እያዘጋጀ ይገኛል።

ይህ ቡድን በለውጡ ማግስት ራሱን ዘመኑ በሚጠይቀው የፖለቲካ አስተሳሰብ ገርቶ እንደ ሀገር የተጀመረው የለውጥ አካል በመሆን ፤ እወክለዋለሁ ለሚለው የትግራይ ሕዝብ የተሻሉ ነገዎች አስቻይ ሁኔታ መፍጠር እና አቅም መሆን ሲችል በተከተለው የማናለብኝነት እና እብሪት የራሱን ህልውና ሳይቀር አደጋ ውስጥ የከተተ የታሪክ ክስተት ፈጥሯል። የትግራይንም ሕዝብ ከዚህ ቀደም ካስከፈለው ያልተገባ ዋጋ የከፋ ዋጋ እንዲከፍል አድርጓል።

ከውልደቱ ጀምሮ እየሠራ ካለው ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆነው ፤ በትግራይ ሕዝብ ስም ጥፋቱን እያወራረደ ዛሬ ላይ የደረሰው ሕወሓት አሁንም የክልሉን ሕዝብ ለሌላ ጥፋት አጋላጭ በሆነ የእብሪት እና የማን አለብኝነት መንገድ ላይ ይገኛል። መርሕ በሌለው መንገድ ለትግራይ ሕዝብ ሆነ ለኢትዮጵያውያን በጎ ሕሊና ከሌላቸው ፤ እንዲያውም የትግራይን ሕዝብ ስብራት በብዙ ተስፋ ከሚያደርጉ ኃይሎች ጋር ህብረት ፈጥሯል።

ይህ የመላው ሕዝባችንን ከዛም በላይ እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይን ሕዝብ የሰላም እና የልማት አጀንዳ የማደናቀፍ፤ ጽንፍ የረገጠ፤ የጥፋት መንገድ ሊያስከትል የሚችለው ሁለንተናዊ ጥፋት ከዚህ ቀደሙ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም። በተለይም የትግራይ ሕዝብ ከዚህ የድርጅቱ አደገኛ አካሄድ የሚተርፈው ጥፋት ነገዎቹን ብቻ ሳይሆን ዛሬዎቹንም የሚበላ ነው።

ይህንን የቡድኑን አደገኛ አካሄድ ለመግራት እና ለማስቆም የትግራይ ሕዝብ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው። በተለይም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የሆነው የትግራይ ወጣት የሕወሓትን የጥፋት መንገድ በግልጽ እና በአደባባይ መቃመው ፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅበታል።

የትግራይ ወጣት ሁሌም ለመሞት የሚዘጋጅበትን ሳይሆን ፤ የተሻለ ሕይወት በክብር ለመኖር የሚያስችለውን እድል መፍጠር ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ስለሰላም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ራሱን ማዘጋጀት እና ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይገባዋል ። ለዚህ ደግሞ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው !

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You