
-9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የያዙ አንድ ሺህ 144 መዝገቦች ተከፍተዋል
አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት 9 ወራት ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የያዙ 686 መዝገቦች ውሳኔ እንደተሰጠባቸው የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አስታወቀ።
የፌዴራል የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው የኮሚሽኑን የ9 ወራት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በያዙ 686 መዝገቦች ላይ የዳኝነት ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
እንደ አቶ አያሌው ገለጻ፤ በኮሚሽኑ በ2017 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የያዙ አንድ ሺህ 144 መዝገቦች ተከፍተዋል። ከዚህም ውስጥ 686 መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል። ቀሪዎቹም በፍርድ ሂደት ውስጥ ያሉ ናቸው። ከመዛግብቱ ውስጥ 210 የሚሆኑት በገቢዎች መሥሪያ ቤት 476 የሚሆኑት ደግሞ በጉምሩክ ኮሚሽን ላይ የቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቀሪ በኮሚሽኑ ውሳኔ የሚጠብቁ መዝገቦች በገቢዎች ላይ 169 በጉምሩክ 289 በድምሩ 458 መዝገቦች ቅሬታ የቀረበባቸው መሆኑን አመልክተው፤ እነዚህ መዝገቦችም ከ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የያዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
458 ውሳኔ ካላገኙት መዝገቦች ውስጥ 51 ለመልስ የተቀጠሩ፣ 406 በቃል ክርክር ላይ ያሉ፣ አንድ መዝገብ ለብይን የተላለፈ እና ቀሪዎቹ አምስት መዝገቦች ለውሳኔ የተቀጠሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮ በጀት ዓመት ከአንድ ሺህ 144 መዝገቦች 686 መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል። ይህም እቅድ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ 99 ነጥብ 2 በመቶ መፈጸም ተችሏል። ከዓምናው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ብልጫ እንዳለው ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በገቢዎች እና ጉምሩክ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች መጀመሪያ ቅሬታቸውን በተቋሙ አቅርበው ተቋሙ ምላሽ ካልሰጣቸው በይግባኝ ቅሬታቸውን ተቀብሎ ውሳኔ እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሄዱት 17 መዝገቦች ውስጥ አምስቱ ተመርምረው በድጋሚ የጸኑ፤ ቀሪዎቹ 12 መዝገቦች በመታየት ሂደት ላይ ያሉ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሽረው ከሚመለሱት መዝገቦች ብዛት አንጻር ኮሚሽኑ ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ የታክስ ሥርዓትን እያረጋገጠ መሆኑን እና የውሳኔ ጥራትን እያረጋገጠ መሆኑን የሚጠቁም ነው ብለዋል።
በውሳኔ ሂደቱ ውስጥ አመልካቾች የሚያሲዙት የ50 በመቶ ክፍያ እንደ ሕግ ውሳኔው ለመንግሥት የሚጸናው እንዳለ ሆኖ ለባለጉዳዩ የሚመለሰው ደግሞ ተመላሽ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑም በ2018 ዓ.ም በአማራ፣ በኦሮሚያና በሲዳማ ክልሎች የታክስ ይገባኝ ኮሚሽን እንደሚያቋቁም ጠቁመዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም