ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ቤተሰብ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል

አዲስ አበባ፡- የቤተሰብን የሥራ ባህል እና ገቢን በማሳደግ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ላይ ሚናውን እንዲወጣ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ገለፀ።

ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን አከባበር ላይ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ እንደገለፁት፤ ቤተሰብ ትውልድን ለማስቀጠልና መልካም ዜጋ ለማፍራት ወሳኝ ነው። በመሆኑም በቤተሰብ ውስጥ ጠንካራ የሥራ ባህልና ኢኮኖሚ በመገንባት ሁለንተናዊ የሀገር ግንባታ ላይ የጎላ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

ቀጣዩ ትውልድ ተገቢውን ልምድ እና ዕውቀት እንዲያገኝ የቤተሰብ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ሚንስትር ዴኤታዋ፤ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገቢውን ድርሻ እንዲወጣ ባለድርሻዎች በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የአረጋውያን እና የቤተሰብ መሪ ሥራ አስፈፃሚ በማደራጀት እየሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች በማዘጋጀት ሰፋፊ ውጤታማ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ በቤተሰብ አባላት ባለው ደካማ የሥራ ባህል እንዲሁም በሙያ እና የሥራ ፈጠራ ማነስ የቤተሰብ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ እንመለከታለን ያሉት ሚንስትር ዴኤታዋ፤ ቤተሰብ ደህንነቱ በተጠበቀበት አግባብ ራሱን ከመደገፍ በዘለለ ለሀገር ኢኮኖሚ እና ብልፅግና ውስጥ አወንታዊ ሚና እንዲያበረክት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ በገጠር እና በከተማ የቤተሰብ የሥራ ባህል እንዲሻሻል እና በቤተሰብ መካከል የሚፈጠር አለመግባባት እንዲፈታ ለማድረግ የተሻለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመፍጠር እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፤

የቤተሰብ ቀን ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ከግንቦት 7 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ጠቁመው፤ ሁሉም ባለድርሻ አካል በሚሠራው ሥራ የቤተሰብ ጥበቃ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልም አስገንዝበዋል።

በሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ የቤተሰብ መልካም ግንባታ የዴስክ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ቢምረው በበኩላቸው፤ የቤተሰብ ደህንነት እና ኢኮኖሚ ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። በመሆኑም የቤተሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት እና ጥበቃ እንዲጎለብት የገቢ መሻሻል እና ኢኮኖሚ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የቤተሰብ ግጭቶችን በመቀነስ፣ የቤተሰብን ገቢ በማሳደግና በሳይንስ የተደገፈ የፋይናንስ አጠቃቀም በመተግበር የቤተሰብን ሁለንተናዊ ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚቻልም ጨምረው ገልጸዋል።

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ”የተሻሻለ የቤተሰብ ሥራና ገቢ ለሀገር ኢኮኖሚ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You