
ዜና ሀተታ
የከተሞቹ ውበት ዓይንን ይማርካል፤ ግርምትን ያጭራል። መንገዶቹ፣ ህንጻዎቹ ፣ የትራንስፖርት ፍሰቱ አግራሞትን፣ መደነቅንና መደመምን ይፈጥራል። ዛሬ ይህች የበለጸገች ሀገር የዛሬ 60ና 50 ዓመት በፊት በድህነት ውስጥ ነበረች ቢባል ማን ያምናል። እውነታው ግን ይህ ነው።
እ.አ.አ ከ1959 እስከ 1961 በቻይና ምድር በተከሰተው ከፍተኛ ቸነፈር (ረሃብ) ሕዝቦቿ የሚበሉት አጥተው ለከፍተኛ ችግር እንደተጋለጡ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ቻይና እጆቿን ለምጽዋት ዘርግታ የእለት ጉርሷን አልፈለገችም። ይልቁንም አንጀቷን አስራ፤ ጥርሷን ነክሳ ፤ በመሥራት በዘላቂነት ከችግሯ ለመወጣት ታገለች እንጂ። ቻይና ያደረገችው ጥረት እና ያገኘችው ስኬት ዛሬም ድረስ በሀገሪቱ ዜጎች ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም በምሳሌነት የሚጠቀስ የዚያች ሀገር ታላቅ ገድል ነው።
ከዚህ ገድሏ ጀርባ የነበሩት የኮሚኒስት ፓርቲው አቀንቃኝና የሀገሪቱ መሪ ማኦ ዜዱንግ ቻይና በዚያ የችግር ወቅት ያለማንም አጋዥነት በራሷ ጥረት ብቻ የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥ የወሰዱት ቆራጥ ርምጃ፤ ቻይናውያን ተግቶ በመሥራት ችግሮቻቸውን ማሸነፍ እንዲችሉ መሠረት ያኖሩበትና ለዛሬው እድገትና ሥልጣኔያቸው እርሾ የጣሉበት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተደርጎ ይታያል። ‹‹ችግር ብልሃትን ይወልዳል እንዲሉ›› ቻይና በአንድ ወቅት ያጋጠማትን ረሃብና ቸነፈር ወደ ጥሩ እድል የቀየረች ሀገር ለመሆን በቅታለች።
ቻይና ዛሬ በኮንስትራክሽን፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ እና በሌሎችም ዘርፎች ታላቅ አቅም ፈጥራለች። ለሌሎች ሀገራት በተለይም ለአፍሪካ ሀገራት ልምዷን እና ተሞክሮዋን በማካፈል መነቃቃት እየፈጠረችም ትገኛለች።
የቻይና መንግሥት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ባለው አጋርነት ከሰሞኑ ኢትየጵያን ጨምሮ ከጋምቢያ፣ ኬንያ ፣ ዛምቢያና ዛንዚባር ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ወጪያቸውን ሸፍኖ በቤጂንግ እና በሌሎች ከተሞች ለሶስት ሳምንት የቆየ ሴሚናር አካሂዷል። ሴሚናሩ ከአጫጭር ገለጻዎችና የውይይት መድረኮች በተጨማሪ የተለያዩ የቻይና ግዛቶችን በመጎብኘትም የታጀበ ነው።
የሴሚናሩ ተሳታፊዎች በቤጂንግ፣ በሻንግሻና በዩያንግ ከተሞች ባደረጉት ቆይታ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ የጥናትና ምርምር ተቋም፣ የቻይናውያን ታሪክና ባህል አስረጂ የሆኑ ሙዚየሞች፣ ቅርሶችና ታሪካዊ ቦታዎችን ጎብኝተዋል። በተጨማሪም በሴራሚክ ሥራና ጥንታዊ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጦችን የሚያሳዩ የአርኪዎሎጂ ስፍራዎች፣ የግብርና ምርምር ተቋማት፣ በጥንት ዘመን ለጽሑፍ አገልግሎት ሲውሉ የነበሩ የቀርከሃ ቁሳቁሶችን የያዘ ሙዚየም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት የተመዘገቡት ታላቁ የቻይና ግንብና ቴምፕል ኦፍ ሄቨን፥ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ የለማ ፓርክ፣ የኤክስፖርት ወደብና የኢንቨስትመንት ድርጅቶች የጉብኝቱ አካል ናቸው::
የጉብኙቱ መዳረሻዎች ቻይና ከየት ተነስታ የት እንደደረሰች የሚናገሩ፤ የዜጎችን የሥራ ትጋት እና ፍሬ የሚያሳዩ ናቸው። እያንዳንዳቸው መዳረሻዎች ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች የሚያስገርሙ፣ የሚያስደምሙ፣ የሚያስደስቱና ትምህርት የሚቀስምባቸው እንደሆኑ ተመልክተናል።
በጉብኝቱ ከተሳተፉት ጋዜጠኞችም መካከል በኬንያ ለኔሽን ሚዲያ የሚሠራው ጋዜጠኛ አግሬ ሙታምቦ በቻይና በነበረው የሶስት ሳምንታት ቆይታው ‹‹ቻይና በልዩ ልዩ መስኮች በፍጥነት እያደገች ያለች ሀገር መሆኗን ተመልክቻለሁ›› ብሏል። የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት የሆነችው ቻይና በአሁኑ ጊዜ በፍጥነት ዘመናዊነትን እየተላበሰች እንደሆነም ተናግሯል።
ጋዜጠኛ አግሬ፤ አፍሪካ ከቻይና ልትቀስማቸው ይገባል ብሎ ከጠቀሳቸው ዋና ዋና መልካም ተሞክሮዎች መካከል በራስ መንገድና በራስ አቅም ማደግ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ እንደሆነችና ከምርጥ ሥራዎቿ ትምህርት እንደሚገኝበት ገልጿል:: ሌላው የቻይና መሪዎች በትክክል ለሕዝባቸው የሚሠሩባት ሀገር መሆኗ ሌሎች ሊማሩበት ይገባል ብሏል። ሥልጣን የሕዝብ ማገልገያ መሆኑንና ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ተቀናጅቶ መሥራት አፍሪካ ከቻይና ልትቀስመው የሚገባ መልካም ተሞክሮ መሆኑን ተናግሯል።
የዛምቢያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋዜጠኛ የሆነው ቫላንታይን ሻንዳ በቻይና ቆይታው ሀገሪቷ ምን ያህል እንዳደገች ብዙ ማሳያዎችን መመልከቱን ይናገራል። “አንዱ ልጠቅሰው የምችለው ምሳሌ የሚሆን ሥራ የቻይና የግብርና ሳይንስ አካዳሚ የሚሠራቸውን ነው” ብሏል። በተለይም ፒዮኒ ተብሎ የሚጠራው የአበባ ዓይነት ላይ እሴት በመጨመር ከምግብ ነክ ምርቶች እስከ የውበት መጠበቂያ በርካታ ምርቶችን ለማምረት እየተጠቀሙበት እንደሆነ ከጉብኝቱ መረዳቱን ገልጿል።
በተመሳሳይ በአፍሪካም የተፈጥሮ ሀብት ስለሚገኝ ጥሬ ዕቃዎች ላይ እሴት በመጨመር ሀገራዊ ገቢን ለማሳደግ ሊውል እንደሚችል ሃሳቡን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አጋርቷል። ሌላው ቻይና ልማቷን ከአካባቢው ጥበቃ ጋር አስማምታ እንደምትሠራ መመልከቱን ገልጾልናል። ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ አፈሯንና ወንዞቿን በሚገባ እየተንከባከበች እንደሆነ የሚመሰክሩ ሥራዎች አሏት ብሏል። ከዚህ አንጻር የአፍሪካ ሀገራትም ተሞክሮውን ወስደው ሊሠሩበት ይገባል ሲል ተናግሯል።
በተጨማሪም ባህልን በመንከባከብና በማቆየት ረገድም ቻይና ብዙ ርቀት ሄዳለች። አፍሪካም በልዩ ልዩ ባህሎች የታደለች በመሆኗ ከቻይና ተሞክሮ በመውሰድ ፍሬ የሚያፈራ ሥራ መሥራት እንደሚችል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሲካሄድ የነበረው ሴሚናር ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም መጠናቀቁን ተከትሎ በመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የቻይና የዓለም አቀፍ ጥናትና ከፍተኛ ማሠልጠኛ ተቋም (CICG Institute of International Studies & Advanced Training) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሃን ሊኪያንግ እንደገለፁት፤ ሴሚናሩ ከአፍሪካ ለመጡ ጋዜጠኞች የጥንቷና የአሁና ቻይና ባህል እንዲተዋወቁ የሚያስችል ነው። አሁን ጊዜው በቀላሉ መረጃ የሚገኝበት ቢሆንም በአካል ተገናኝቶ ልምድ መለዋወጥ ሊተካ የማይችልና ልብ ውስጥ የሚቀር ተሞክሮ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
“ይሄ ሴሚናር ጋዜጠኞች ስለቻይና ትክክለኛ አመለካከት እንዲጨብጡ ከማስቻሉ ባሻገር እኛም ስለአፍሪካ ይበልጥ እንድናውቅ ዕድል ፈጥሮልናል” ብለዋል። ጋዜጠኞች ወደ መጡበት ሲመለሱ በሚሠሯቸው ዘገባዎች አማካኝነት የቻይናና አፍሪካ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዙ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
ጋሻው ታደሠ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም