
አዲስ አበባ፡- በገጠር አካባቢዎች ያለውን የመንገድ ተደራሽነትና የትስስር ችግር ለመቅረፍ በ407 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የገጠር መንገድ ትስስር ፕሮጀክት ሊተገበር መሆኑ ተገለጸ። ፕሮጀክቱን በተቀናጀ ሁኔታ ለመተግበር የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን የከተማና መሠረት ልማት ሚንስቴር አስታውቋል። ሚንስቴሩ ለፕሮጀክቱ አፈጻጸምና ክትትል ከሰባት ባለድርሻ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ትናንት ተፈራርሟል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚንስቴር ዴኤታ አቶ የትምጌታ አስራት እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በ407 ሚሊዮን ዶላር በጀት፣ በ126 ወረዳዎች የሚተገበር ነው። በገጠር በመሬት አቀማመጥና በሌሎች ምክንያቶች ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን በማስተሳሰር ማህበራዊ ግልጋሎት ሰጪ ተቋማትን ለማህበረሰቡ የማዳረስ ዓላማ ያለው ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቱ ከሰባት ሺህ በላይ የገጠር መንገዶች ግንባታ፣ ከ10ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገድ ጥገና፣ ከሰባት መቶ በላይ የመሻገሪያ ድልድዮች እና እና ከሦስት መቶ በላይ ተንጠልጣይ የእግረኛ መሻገሪያ ድልድዮች ግንባታ እንደሚከናወንም ጠቅሰዋል።
‹‹ፕሮጀክቱ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ ሀገራዊ ፕሮግራም›› ነው ያሉት ሚንስትር ዴኤታው፤ ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከዓለም ባንክ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘና ክልሎች ደግሞ 107 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያዋጡ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ባለድርሻ ከሆኑ ከሰባት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙንና ስምምነቱም ፕሮግራሙን በተባበረ መልኩ ለመተግበር እንደሚያስችል ገልፀዋል።
እንደ አቶ የትምጌታ ገለፃ፣ ሚንስቴሩ የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመው ከኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ ከፌዴራል የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን፣ ከኮንስትራክሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከፌዴራል ሥነ-ምግባና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን እና በተንጠልጣይ ድልድዮች ግንባታና ማማከር ዘርፎች ልምድ ካለው ‹‹ሄልቬታስ ኢትዮጵያ›› ከተሰኘ ድርጅት ጋር ነው።
በፕሮጀክቱ የሚሠሩ መንገዶች፣ ድልድዮችና መሻገሪያዎች በጥራት እንደሚገነቡ የጠቀሱት ሚንስትር ዴኤታው፤ ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ፕሮጀክቱን የሚያስተባብረው ጽህፈት ቤት ከሚያደርገው ቁጥጥር ባሻገር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በቁጥጥር ሥራዎች ላይ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ፕሮግራሙን በብቃት መፈጸም እንዲቻል የአቅም ግንባታ እና ጠንካራ የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች ስለሚያስፈልጉ፣ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር እገዛ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል።
‹‹በፕሮግራሙ የአካባቢ ጥበቃና የማህበራዊ ደህንነት ጉዳዮች ተገቢ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሉት›› አቶ የትምጌታ፤ በፕሮግራሙ ትግበራ የሚተከሉ በርካታ ችግኞች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ በዘርፉ ክፍተት እንዳይፈጠር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
እንደ አቶ የትምጌታ ገለጻ፤ ፕሮግራሙ ሲተገበር ለፕሮግራሙ የሚውል ሀብት በሁሉም ደረጃ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል ይጠበቃል። ብልሹ አሠራር እንዳይኖር የፌዴራል ግዢና ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን እንዲሁም የፌዴራል ሥነ ምግባር የጸረ ሙስና ኮሚሽን በጋራ ይሠራሉ።
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ-ሙስናና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፤ በዘርፉ በርካታ የአገልግሎትና የማሽን ግዢዎች እንደሚኖሩ ጠቁመው፣ በፕሮጀከቱ የሚሳተፉ አካላት በሕግና በውል ስምምነት ብቻ የተሰጣቸውን ሥራ እንዲሠሩና ከዚህ ያፈነገጡ የማጭበርበርና የሙስና ተግባራት እንዳይፈፀሙ ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
ዜጎች የፕሮጀክቱን ትግበራ በግልጽ የማየት እድል ስለሚኖራቸው ካሉበት ቦታ ሆነው የሙስና ተግባራትን ለመጠቆም የሚያስችል የዲጅታል አሠራር እንዳለም ጠቁመዋል።
‹‹ዜጎች ይህ ፕሮጀክት ለሙስናና ለብልሹ አሠራር እንዲጋለጥ መፍቀድ የለባቸውም። ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክት በመሆኑ ውጤታማ ሆኖ እንዲተገበርና የዜጎች ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጠው መሥራት አለባቸው›› ብለዋል። በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሆነው ገንዘቡን ከፕሮጀክቱ ዓላማ ውጪ ለመጠቀም የሚያስቡ አመራሮችም ሆነ ባለሙያዎች ቢኖሩ ሕብረተሰቡ ማጋለጥ እንዳለበትም ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን ጥራት ማረጋገጥ ግዴታችን ነው›› ያሉት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታምራት ሙሉ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፤ ሰፊ ሽፋን ያለውን ፕሮጀክት በአደራ ተቀብሎ መጀመር የሚያኮራ እና ይህንንም ማሳካት የሀገር ግንባታ አንዱ አካል በመሆኑ፣ ኢንስቲትዩቱ ኃላፊነቱን በትኩረትና በጥንቃቄ እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም