የኦሊምፒክ ከዋክብት የዶሃ ዳይመንድ ሊግ ፍልሚያ

የ2025 ዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ሦስተኛ መዳረሻ ከተማ ዶሃ ዛሬ ተጠባቂውን ውድድር ታስተናግዳለች። በዚህ የዳይመንድ ሊግ ፉክክር በግልና በቡድን በኦሊምፒክ መድረክ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻሉ 45 ከዋክብት አትሌቶች በትራክና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ተፎካካሪ ናቸው። ከነዚህ መካከል ሰባት አትሌቶች በኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፍ የቻሉ ናቸው።

በኳታሯ መዲና ደማቅ ምሽት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በተለያዩ ርቀቶች የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷቸው ወደ ውድድር ይገባሉ። ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሚሳተፉበት የወንዶች 5ሺህ ሜትር ፉክክር ኩማ ግርማ ለድል ይጠበቃል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በ5ሺህ ሜትር ድንቅ ብቃት እያሳዩ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች አንዱ የሆነው ኩማ ከአራት ወር በኋላ በቶኪዮ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ5ሺህ ሜትር ኢትዮጵያ ተስፋ ካደረገችባቸው አትሌቶች አንዱ ነው። ከአስር ቀን በፊት በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ የርቀቱ ኮከብ በሪሁ አረጋዊ በድንቅ ብቃት የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ባሸነፈበት ፉክክር ኩማ 12:50.69 የሆነ የራሱን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል። የ3ሺህ ሜትር መሰናክል ስፔሻሊስቱ አትሌት ለሜቻ ግርማ ወንድም የሆነው ኩማ በቶኪዮ ሀገሩን ለመወከል የሚያበቃውን ብቃት ከወዲሁ እያሳየ ይገኛል።

በ3ሺህ ሜትር መሰናክል ይበልጥ የሚታወቀው ጌትነት ዋለ ዛሬ ዶሃ ላይ ትኩረት ከሚሰጣቸው ኮከቦች አንዱ ሲሆን፣ በ5ሺህ ሜትር በተለያዩ ፉክክሮች ብርቱ ተወዳዳሪ ከመሆኑ በተጨማሪ ለአሸናፊነት ግምት እንዲሰጠው የሚያደርጉ ፈጣን ሰዓቶችንም በማስመዝገብ ይታወቃል። የቀድሞው የሁለት የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የ1500 ሜትር አሸናፊ አትሌት ሳሙኤል ተፈራም ዛሬ ዶሃ ላይ በ5ሺህ ሜትር ከሚሳተፉ ጠንካራ አትሌቶች አንዱ ይሆናል። በተጨማሪም ይሁኔ አዲሱ፣ አዳነ ካሳዬና ካሂሪ ቤጂጋ በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

በሌላኛው ተጠባቂ የሴቶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር ወጣቷ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ እና ሎሚ ሙለታ ተፎካካሪ ናቸው። ባህሬናዊቷ የርቀቱ የኦሊምፒክ ቻምፒዮን ዊንፍሬድ ያቪ፣ የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ዩጋንዳዊት ፔሩዝ ቼሙታይ እንዲሁም የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ኬንያዊት ፌይዝ ቼሮቲች አንድ ላይ በሚፋለሙበት የዶሃ ዳይመንድ ሊግ ኢትዮጵያውያኑ ወጣት አትሌቶችም ቀላል ግምት አልተሰጣቸውም። በተለይም የዓመቱ ምርጥ ወጣት አትሌት ሽልማት አሸናፊዋና የርቀቱ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮን ሲምቦ የዛሬው ውድድር ምናልባትም የርቀቱን ክብር ከነባሮቹ የምትረከብበት ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት የአፍሪካ ጨዋታዎች የርቀቱ የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሎሚ ሙለታም ብርቱ ተፎካካሪ እንደምትሆን ይጠበቃል።

በሴቶች 1500 ሜትር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እየታዩ የሚገኙ በርካታ አትሌቶች ተሳታፊ ናቸው። በርቀቱ 4:08.10 የሆነ የራሷ ምርጥ ሰዓት ያላት ኤልሳቤት አማረ አንዷ ስትሆን ፣ በመካከለኛ ርቀቶች ተስፋ የተጣለባት አትሌት ወጣት ሳሮን በረኸ 3:59.21 በሆነ ሰዓት ተፎካካሪ ትሆናለች። ትዕግስት ግርማ፣ መብርሂት መኮንን፣ ሳምራዊት ሙሉጌታ፣ ባይሴ ቶሎሳ በዛሬው ዳይመንድ ሊግ ሲፎካከሩ የምናያቸው ኢትዮጵያውያን ይሆናሉ።

የአምናው የዶሃ ዳይመንድ ሊግ በኳታር ስፖርት ክለብ የተለየ ደማቅ ድባብ የታየበት ነበር። በአራት የተለያዩ ውድድሮች የዓመቱ ፈጣን ሰዓቶች እንዲሁም ሁለት የቦታው ክብረወሰኖች የተሻሻሉበት ነበር። ዘንድሮም በርከት ያሉ የኦሊምፒክ የሜዳሊያ አሸናፊዎች ሲፋለሙ አዘጋጆቹ የተለየ ነገር ለመመልከት ተስፋ እንደሚያርጉ ቀደም ብለው ገልፀዋል። በየትኛውም ውድድር የቦታውን ክብረወሰን ለሚያሻሽል አትሌትም አምስት ሺህ ዶላር ጉርሻ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You