የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ የተለያዩ ሥልጠናዎች ተሰጡ

የባህል ስፖርቶች ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች አንዱ በባለሙያዎች ጭምር የእውቀት ወይም የግንዛቤ እጥረት በተደጋጋሚ ይጠቀሳል። የባህል ስፖርትን ለማሳደግ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እያከናወነ ከሚገኘው ተግባራት አንዱ ይህን ክፍተት ለመሙላት ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሙያዊ ሥልጠና መስጠት ነው። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ሙያዊ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

ከነዚህ ሥልጠናዎች አንዱ ለስፖርት ሳይንስ ምሁራን ከሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም ጀምሮ የተሰጠው ሥልጠና ከትናንት በስቲያ መጠናቀቁ ታውቋል። ከ48 ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ የስፖርት ሳይንስ መምህራን የ2ኛ ደረጃ የዳኝነት እና የአሠልጣኝነት ሥልጠና በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተሰጥቷል።

በሥልጠናው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት መሀመድ እንደገለፁት፣ የባህል ስፖርቶችን ማሳደግ የእያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነት ነው። በትምህርት ተቋማት የሚገኙ ምሁራኖች ደግሞ ስፖርቱን ሊያሳድጉ የሚችሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን፣ በሕግና ደንቦች ላይ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሃሳቦችን በመለገስ ማገዝ ያስፈልጋል።

ፕሬዚዳንቷ አክለውም፣ የተሰጡ ሥልጠናዎች በዋናነት በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከማለም ባሻገር መምህራንን በባህላዊ ስፖርቶች ዙሪያ ያላቸውን እውቀት በማሳደግ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል። ከሥልጠና ባሻገር የተለያዩ ውድድሮችን በማብዛት ሀገር አቀፍ ባህሎችን ለዓለም ለማስተዋወቅም እየተሠራ እንዳለም ተናግረዋል።

በከፍተኛ ደረጃ የባህል ስፖርቶች ዳኞችንና አሠልጣኞችን ቁጥር በማሳደግ ረገድ የሚነሱ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ፣ ብቁ ዳኞችንና አሠልጣኞችን መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህም ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል መሰል ሥልጠናዎችን በብዛት ማዘጋጀት አንዱ እንደሆነም ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል። በቀጣይ ተያያዥ ሥራዎችን ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ገልፀውም፣ ሥልጠናው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የተባበሩ አካላትን እና የተሳተፉ ሠልጣኞችን አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዓባይ በላይሁን በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል። ሠልጣኞቹም በነበራቸው ቆይታ ደስተኞች እንደሆኑ ገልፀው በንድፈ ሃሳብ እና በተግባር ተደግፎ የወሰዱት ሥልጠና ከዚህ በፊት ስለ ባህላዊ ስፖርቶች የነበራቸውን ግንዛቤ እንዳሰፋላቸው እና በቀጣይ በዘርፉ ላይ በእውቀት እና በሥነ-ምግባር የታነፀ ባለሙያ በመሆን ለመዳኘት እና ለማሠልጠን የሚበቃ እውቀት እንዳገኙ ተናግረዋል።

በተጨማሪ ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት ጎን ለጎን በትምህርት ተቋማት ውስጥ የባህላዊ ስፖርቶች ፕሮጀክት በማቋቋም የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። በቀጣይ ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ማሕቀፎች በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ከሥልጠናው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በብቃት ለማሠልጠን እና ለመዳኘት ዝግጁ እንደሆኑም አስረድተዋል።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሰውነት ማጎልመሻ እና ስፖርት ኢንስቲትዩት ዲን ወገኔ ዋልተንጉሥ (ዶ/ር) በሥልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለፁት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ራሳቸውን በጥናት እና በምርምር በማበልፀግ የባህላዊ ስፖርቶች ለማሳደግ የራሳቸውን ዐሻራ ሊያስቀምጡ ይገባል። የባህል ስፖርቶቻችን መታወቅ በሚገባቸው ልክ ያልታወቁና ያለሙ በመሆኑ ይህን ክፍተት ለመሙላት በየአካባቢው ያሉትን የባህል ስፖርቶች ለማጥናት እና ለማሳደግ በስፖርት ሳይንስ ዘርፍ ግንባር ቀደም የሆነው የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሚገኝ ወገኔ ዋልተንጉሥ (ዶ/ር) አመላክተዋል።

ከመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ሴት የስፖርት ሳይንስ መምህራን ሲሰጥ የቆየው የ1 ኛ ደረጃ የአሠልጣኝነት ሥልጠናም ትናንት ተጠናቋል።

ፌዴሬሽኑ ከሳምንት በፊትም በኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርቶች ዙሪያ ለስፖርት ጋዜጠኞች ለተከታታይ ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መስጠቱ ይታወቃል። ይህም የባህል ስፖርቶችን በሚፈለገው ልክ ለማሳደግ በተደራጀ መልኩ የዜና ሽፋን መስጠት እንዲሁም በባህላዊ ስፖርቶች ዙሪያ ሰፊ የአየር ሰዓት በመመደብ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ የስፖርቱ እድገት የሚለካበት እንደሆነም ፕሬዚዳንቷ ጠቁመዋል።

ስለ ባህላዊ ስፖርቶች ምንነት፣ መመሪያና ደንቦች እንዲሁም ስለ አበርክቷቸው ትኩረት ያደረገ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ሥልጠና ለስፖርት ጋዜጠኞች መሰጠቱ በቀጣይ በጋራ ለሚሠሩ ሥራዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ተብሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You