አለቃ ለሻይ ወጥቷል የማይባልበት ተቋም

ዜና ሀተታ

የሀገሪቷ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት 117 ዓመታትን ያህል አስቆጥሯል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ተቋማት በብዙ ከፍታና ዝቅታ ውስጥ አልፈዋል። የሚመሰገኑባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ የሚነቀፉባቸውም አሠራሮች አይታጡም። በተለይም በዚህ ዘመን ለበርካታ ምሬቶች ምንጭ የሆነው የአገልግሎቶች አሰጣጥ አለመዘመን ነው። በአንዳንድ ተቋማት ባለ ጉዳዮች በአጭር ሰዓት ማለቅ የሚችል ጉዳይ ኖሯቸው አሠራሮች ባለመዘመናቸው ምክንያት ፈጣን ምላሽ አጥተው ከቢሮ ቢሮ የሚንከላወሱ ወይም በረዣዥም ሰልፎች የሚማረሩ ሰዎችን መመልክት የተለመደ ነው። በስብሰባና በተለያየ ምክንያት ቢሮው ውስጥ የማይገኝን ጉዳይ ፈጻሚ ወይም ሃላፊ በማጣት የሚንገላታው ተገልጋይም ህልቁ መሳፍርት ነው።

አሁን አሁን በአንዳንድ ተቋማት ጉዳይን ለማስፈጸም በእግር መመላለስና መገተር ብቻውን ዋጋ እንደሌለው የታዘብነው ሀቅ ነው፤ በእጅ ካልተሄደባቸው በስተቀር ዞር ብለው የማያዩ ጉዳይ ፈጻሚዎች የመኖራቸው ነገር ከማንም የተሰወረ አይደለም። ይህም ተገልጋዮችን ሲያማርር የኖረና፤ የተቋማትንም ገጽታ ሲያበላሽ የኖረ ጸያፍ ተግባር መሆኑን ሳንወድ በግዳችን ተላምደነው ቆይተናል።

ለእንዲህ አይነቱ ክፍተት አንዱ ምክንያት ተቋማት ከዘመን ጋር ያልዘመኑ ፤ እድሜ አንገት ያስደፋቸው ኋላ ቀር አሠራሮችን የሚከተሉ መሆናቸው ነው። በተለይም በእጅ ንክክኪ የሚፈጸሙ ጉዳዮች የእጅ ሰንሰለቶች የሚበዙባቸው እንደመሆናቸው በእጅ እንዲኬድባቸው የተመቻቹ ናቸው።

በእስከ ዛሬው ሂደት የበዛ የወረቀት ሥራ እና አዝጋሚ ውሳኔ አሰጣጥ ብዙዎችን አሰልችቷል፤ ጉዳዮች እንደ ተከታታይ ፊልም በይደር እየተቀጠሩ፤ ለብዙዎች ምሬት ምክንያት ሆነዋል፤ የተገልጋይን ጊዜ በልተዋል ፤ ኪስን አሳስተዋል። አሁንም ሙሉ ለሙሉ ከዚህ ችግር ተላቀናል ማለት ባይቻልም ‹‹መሶብ›› የአንድ ማእከል አገልግሎት ግን ተስፋ ሰንቋል።

ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ አንድ ተቋም ሲሄዱ “አለቃው የለም! ስብሰባ ገብቷል! ለሻይ ወጥቷል! ፣ ነገ ተመልሰው ይምጡ፣ እኛ እናስጨርስሎት ወዘተ ሲባል ይስተዋላል። እንዲህ አይነቱ የጥቂት ኢሞራላዊ ግለሰቦች ተግባር በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አይነጥላ ሆኖ ኖሯል። እንደ ‹‹መሶብ›› አይነት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተቋም መምጣት እንዲህ አይነቱን ችግር የሚፈታ መሆኑ በጽኑ ታምኖበታል።

መሶብ ከአንድ ክፍለዘመን በላይ ባስቆጠረው ኋላ ቀር አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለዘመን ቅርብ መሆን የቻለ አዲስ አሠራር ሆኖ መምጣቱ በሀገራችን ስር እየሰደደ የመጣውን ብልሹ አሠራር ለማከም ተስፋ የሚሰጥ ነው። መሶብ የብዙዎች እንግልት ምላሽ የሚያገኝበት ፤ ለብዙዎች እረፍት መሆን የሚችል ተቋም ነው። በዚህ ተቋም ውስጥ ለሻይ ወጥቶ የሚቀር ፤ አልያም አዳማ ለስብሰባ ሄዶ የሚቆይ አለቃ አይኖርም። ሥራዎችን የሚያስተጓጉል፣ ጉዳዮችን የሚያክምና የሚያወሳስብ ሰበብም አይፈጠርም።

በ ‹‹መሶብ›› የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዘመነ ወረቀት እያበቃለት ይመስላል። መሶብም በዚህ ሂደት ውስጥ የራሱን ዐሻራ አሳርፏል። በማዕከሉ 12 ተቋማት እና 41 የፌዴራል አገልግሎቶች ስትር ተደርገዋል። ከ100 በላይ በሆኑ ካሜራዎች ክትትል የሚደረግበት ተቋም ነው። መሶብ የሕዝቡን እንግልት ይቀንሳል ተብሎ ታምኖበታል። እውነታውም ይህ ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎችም በመስክ ምልከታቸው ይህንኑ መታዘብ ችለዋል። በተቋሙ ውስጥ አገልግሎት ሰጪና ተቀባዮችን አነጋግረዋል።

በጉብኝቱ ውስጥ የተገኘው ቻይናዊው ሊ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ሊ በአገልግሎቱ ፍጹም ደስተኛ ነው። ‹‹ ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ስፍራ ማግኘቱ በተለያዩ ጊዜያትና ስፍራ በመሄድ እንዳይቸገርና ጊዜው እንዳይባክን ማድረጉን ጠቅሷል፤ በተለይ እንደ እርሱ ለሀገር እንግዳ ለሆኑም ሰዎች ማዕከሉ ስላለው ፋይዳ አንስቷል። በትውልድ ቀዬው ቻይና ሁሉም አገልግሎቶች መሶብን መሰልና ቀልጣፋም ናቸው ብሏል።

ሌላው በማዕከሉ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ደበበ ገብረመስቀል ይባላሉ። ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመጡት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ነው። ውክልና ለመስጠትና የብድር ውል ስምምነት ለመፈጸም ነበር የተገኙት። በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ባገኙት አቀባበል ፍጹም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሠራተኞች ጥሩ የሆነ ባህሪና የእንግዳ ተቀባይ ፊት እንዳላቸው ይናገራሉ።

ስለሠራተኞቹ ጥሩ አገልግሎት ሰጪነት መስክረዋል። ተባባሪና ለባለጉዳይ አስፈላጊውን መረጃ የሚያጋሩ ስለመሆናቸውም አንስተዋል። የገንዘብ አከፋፈሉም ዲጂታል መሆን ሥራውን የሚያቀል ሆኖ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ሀናን ታከለ ነች። በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ የሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ ባለሙያ ናት። ሀናን በዚህ ታሪካዊ ስፍራ መሥራት በመቻሏ ክብር እንደተሰማት ትናገራለች። አገልጋይ በመሆኗና ይህን እድል በማግኘቷ ተቋሟን አመስግናለች።

ተቋሙ ለተገልጋዮ ምቹና ቀልጣፋ አሠራር እንዳለው አንስታለች። ተገልጋዩ ስለሚፈልገው መረጃ በቀላል መንገድ በማየትና በማንበብ ይረዳል፤ ይህም አላስፈላጊ የሆነ ብክነትን በመቀነስ ጊዜና ገንዘብ ይቆጥባል። ውክልና ለመስጠት ምን ምን እንደሚያስፈልግ ኦንላይን ሲስተም ላይ መቀመጡም በተገልጋይና በአገልግሎት ሰጪው መካከል ያለው ንግግር እንዲቀንስ፤ አሠራሩም እንዲቀል አስችሏል ትላለች።

ሀናን ተቋሙ በሚሰጠው ፋይዳ ልክ ሕዝብ ጋር ሊደርስ እንደሚገባው ትናገራለች። ሚዲያዎች ስለ ተቋሙ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቅባቸውም አንስታለች። ለሕዝቡ ስለተቋሙ ተገቢ መረጃ በማድረስ ረገድ ያለው ሥራ ለነገ መባል እንደሌለበት ትገልጻለች።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You