ውይይቱ በሚዲያው ዘርፍ የተደረጉ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመተርጎም የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ከቻይና ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሚኒስቴር ጋር ያደረገው ውይይት በሚዲያው ዘርፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመተርጎም የሚያስችል እንደሆነ ገለጸ።

መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ከቻይና ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር ሚንስትር በሳዎ ሹሚንግ ከተመራ ሉክ ጋር ትናንት ውይይት አካሂደዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ውይይቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ወደ ፊት ከሚያራምዱ ነገሮች አንዱ፤ በቻይና አፍሪካ ፎረም በየዓመቱ የሚደረሱ ስምምነቶች ናቸው። የዘንድሮ ቻይና አፍሪካ ፎረም በቤጂንግ በተካሄደበት ወቅት ቻይና እና አፍሪካ በጋራ ለመሥራት 10 ዋና ዋና ነጥቦች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን በማውሳት፤ ከነጥቦች አንዱ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ላይ ያተኮረ እንደሆነ አንስተዋል።

በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ቀደም ብሎ የሁለቱ ሀገራት ሚንስትሮች ስምምነት ማድረጋቸውን አንስተው፤ ሁለቱ ሚንስትሮች ያደረጉት ውይይትም ስምምነቱን ወደ መሬት ለማውረድ፤ ያለበትን ደረጃ ለመዳሰስ እና ተጨማሪ ሥራዎችን ለመሥራት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ተስፋሁን እንደተናገሩት፤ በውይቱም አምስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተዋል። የመጀመሪያው ይዘት ከማምረት ጋር ተያያዘ ሲሆን ሁለቱም ሀገራት የረጅም ታሪክ ባለቤት እና ብዙ ሊነገር የሚችል ታሪክ ያላቸው በመሆናቸው፤ በምን መልኩ ይዘቶችን አዘጋጅተው በተሻለ ጥራት በሀገር ውስጥ እና ወደ ሌሎች ዓለማት ማድረስ እንደሚችሉ ተወያይተው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ሁለተኛው የውይይት አጀንዳ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያነሱት ሚንስትር ዴኤታው፤ ቴሌቪዥን፤ ሬዲዮ እና ዲጂታል ሚዲያ በየጊዜው እያደገ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚታዩበት ስለሆነ፤ በቀጣይነት እንዴት ማሳደግ ይቻላል በሚለው ላይ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

ሚዲያዎች በሰው ኃይል፤ በይዘት ፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ጠንክረው እንዲወጡ ምን አይነት ድጋፍ ያስፈልጋል የሚለው ሶስተኛው አቅጣጫ እንደሆነ ጠቁመው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ለመድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የተሞክሮ ልውውጥ በተመለከተ ውይይት መደረጉን በማንሳት፤ በቻይና በተለያዩ የሚዲያ ዘርፎች ተሞክሮ ማግኘት እንደሚቻል አመልክተው፤ ሁለቱም ሀገራት የልምድ ልውውጥ ማድረግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ከስምምነት መደረሱን አስረድተዋል።

ሌላው የሰው ኃይል አቅም ግንባታ መሆኑን ገልጸው፤ እንደ መንግሥት ሆነ እንደ መገናኛ ብዙሃን የአቅም ግንባታ ዘርፎችን በመለየት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵውያን ቻይና በመሄድ ሥልጠና እንደሚወስዱ በመግለጽ፤ ከዚህ በተጨማሪ እንደሚዲያው እና እንደ መንግሥት ኮሙኒኬሽ ዝርዝር ፍላጎቶች ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You