የፍትህ መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚሆንበት የኮሙኒኬሽን ፖሊሲ ሊኖር ይገባል

ሰመራ፦ የፍትህ ሥርዓቱ መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የሚሆንበት የኮሙኒኬሽን ፖሊሲ ሊኖር እንደሚገባ የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ፤ ማህበረሰቡ ምን አይነት የፍትህ ጉዳይ በምን አይነት ሁኔታ እንደተከናወነ መረጃ ማግኘት እንዲችል የኮሙኒኬሽን ፖሊሲ ያስፈልጋል፤ ለማህበረሰቡ ጠቀሜታ ያላቸውንና አስተማሪ የሆኑ ክፍሎችን ለይቶ ማቅረብ እና ሌላውን ውሳኔ ማቆየት በሚሉት ላይ በፖሊሲ ቢታወቅ ተገቢ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮች አለአግባብ አየር ላይ ቢውሉ ፍትህ የማጓደል አቅም እንደሚፈጥሩም ጠቅሰው፤ ይህን ችግር የሚፈታ የኮሙኒኬሽን ፖሊሲ ሊኖር እንደሚገባና ሚዛናዊ አሠራርን መከተል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ምን አይነት ጉዳዮች በምን መልኩ ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ከጠቅላይ ፍርድ ቤት በኩልም ምን ያስፈልጋል በሚሉት ላይ ጥናቶችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመሥራት እየተነጋገረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፍርድ ቤት ጉዳዮችን መረጃ መስጠት እንደሚያስፈልግ፤ ህብረተሰቡ ማወቅ ያለበትን ጉዳይ እንዲያወቅ ማድረግ እንደሚገባ እና መገናኛ ብዙኋን የፍትህ ሁኔታውን የሚዘግቡበት የፍትህ ኮሙኒኬሽን ፖሊሲ መኖር እንዳለበት አመላክተዋል። በአፋር ክልል የዳጉ ጆርናሊዝም በተወሰነ መልኩ እውቅና እያገኘ መሆኑንም አስታውሰዋል።

‹‹በዳጉ›› የአፋር መረጃ የመለዋወጥ ባህል፤ በጅቡቲ ድንበር ላይ የተከሰተ ነገር አዋሽ አካባቢ ለሚኖር ሰው መረጃው በፍጥነት ይደርሰዋል ያሉት አቶ ሙሳ ፤ የአፋር ማህበረሰብ የመረጃን ጠቀሜታ ቀድሞ የተረዳ እና አስፈላጊነቱን የሚያውቅ ነው ብለዋል፡፡

የአፋር ሕዝብ የዳጉ ባሕል አንድ ቦታ ላይ የተከሰተን ነገር ወደ ሌላ ቦታ የማዳረስ የቆየ እሴት እንደሆነ ጠቅሰው፤ የፍትህ ሥርዓቱ መረጃዎችን እንደማህበረሰቡ ባህል ተደራሽ የሚደረግበት የኮሙኒኬሽን ፖሊሲ ሊኖር እንደሚገባ አቶ ሙሳ ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ለመደበኛው ሕግ ድጋፍ ሊሆኑ በሚችሉ ባሕላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ላይ በቅርበት እየሠራ እንዳለ ጠቅሰው፤ በሥርዓተ ትምህርቱ (ካሪኩለም) ባሕላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ስለመኖራቸው ማሳወቅ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የአፋር ክልል ቱባ የባህላዊ የፍትህ ሥርዓት ሀብት ያለው መሆኑን በመጠቆም ፤ ማህበረሰቡ ትክክለኛ የፍትህ ጭብጥ እንዲያገኝ ዘመናዊውን ፍትህ ከባህላዊው ፍትህ ጋር አመጋግቦና አጣጥሞ ውሳኔ መስጠት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የአፋር ሕዝብ ጊሌ ታጥቆ ቢሄድም በማህበረሰቡ ውስጥ በቀል የሚባል ባሕላዊ ዳኝነት እንደሌለ ጠቅሰዋል፤ በዚህም በክልሉ የግድያ ወንጀል ድግግሞሽ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You