“የትግራይን ሕዝብ አግቶ የግል ጥቅሙን የሚያሳድደው ኔትወርክ መፍረስ አለበት” – አቶ ጌታቸው ረዳ በምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ሚንስትር

አዲስ አበባ፡- ‹‹አሁን ላለንበት ትርምስ እና ሥርዓት አልበኝነት የበቃነው መጠየቅ የሚገባቸው ባለመጠየቃቸው እና በወንጀል ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሰዎች ባለመጋለጣቸው ነው›› ሲሉ የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

አቶ ጌታቸው ሰሞኑን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት መንግሥት እና ሥርዓት የሚያውቅ ሕዝብ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ከትግራይ ሕዝብ ጥቅምም ሆነ ከሰላሙ ጋር የተያያዘ ምንም አጀንዳ በሌላቸው ጥቂት ጥቅመኞች በአፈና ውስጥ እንዳለ ተናግረዋል።

ሕዝቡ የወርቅ ንግድ ባሰከራቸው ዘራፊዎች መታገቱን እና ወጣቶች ሳይቀሩ ራሳቸውን ለማስመለጥ ለስደት የተዳረጉበት ሁኔታ እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

እነዚህ አካላት ተጠያቂ ባለመደረጋቸው ምክንያት አሁንም በክልሉ ሌላ የግጭት እና የትርምስ ድባብ እየተፈጠረ መሆኑ የሚያስቆጭ ነው ብለዋል። በዘረፋ ከሚያገኙት የግል ጥቅማቸው ውጭ ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ያልቆሙ መሆናቸውን ሕዝቡ ራሱ እንዲያውቅና አንቅሮ እንዲተፋቸው ተግባራቸውን መግለጽ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ብዙኋኑ አመራር ለትግራይ ሕዝብ ሰላምና ተጠቃሚነት የቆመ ቢሆንም አምስት በመቶ የማይሞሉ ሌቦችና ዘራፊዎች ሥልጣናቸውን ተጥቅመው ክልሉን እያመሱት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይቅርታ ካልጠየቀና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ሴቶችን ከደፈረው የሻቢያ መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት መዋዋል የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ማስከበር ሳይሆን በሕዝብ ላይ ክህደት እንደመፈጸም የሚቆጠር መሆኑን ተናግረዋል። የትግራይን ሕዝብ አግቶ የራሱን የግል ጥቅም የሚያሳድድ የወንጀል ኔትወርክ መፈራረስ እንዳለበትም አመልክተዋል።

የሻቢያ መንግሥት በተገኙበት ሁሉ ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ያላቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከመቅጽበት ፍቅር በፍቅር ሆነው የጫጉላ ሽርሽር ውስጥ መግባታቸው ለጥቅማቸው ሲሉ ነብሳቸውን ሳይቀር ያስያዙ ስለመሆናቸው ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የወርቅ ንግድን ለማጧጧፍ ሁልጊዜ ግጭት የሚቀሰቅሱ እና የትግራይን ወጣት ሰለባ የሚያደርጉ አካላትን ማስቆም እንደሚገባም ገልጸዋል።

በፖለቲካ አመራሩ ውስጥ ያለውና በወርቅ ዘረፋ ላይ የተሰማራው ኮር ሃይል ችግሮችን በሰላም የመፍታት አጀንዳ እንደሌለውና ለሰላም የነበረው ዝግጁነቱ ዜሮ እንደሆነ አስረድተዋል። በዚህም የወንጀል ኢንተርፕራይዝ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የትግራይ ሴቶችን ደፍሮ ትንሽ የንስሃ ምልክት ካላሳየና ይቅርታ በአደባባይ ካልጠየቀ ሃይል ጋር የትግራይን ሕዝብ ጥቅም አስከብራለሁ ብሎ መንቀሳቀስ ክሪሚናል ኢንተርፕራይዝ ነው ብለዋል።

እነዚህ አካላት ጥቅማቸው እስከተረጋገጠ ድረስ እያንዳንዱን ለዘረፋ የሚመች ሥራ ከመሥራት ወደ ኋላ የሚሉ አለመሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ከአሁን በፊት ሲዘመር በነበረው አካሄድ የትግራይን ወጣት ለሌላ መስዋዕትነት ለመዳረግ የሚደረገውን ሙከራ አቶ ጌታቸው የማይቀበሉት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከራሱ ጥቅም በስተቀር የትግራይ ሕዝብ ጥቅም አጀንዳው ያልሆነ የክራይም ኔት ወርክ እንዲበጣጠስ አበክረው የሚሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You