
– አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ውልም ተፈርሟል
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 የቢዝነስ ፎረም የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት አቅምና ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችን ማስገንዘብ የተቻለበት መሆኑን የገንዘብ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ። በፎረሙ የአንድ ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ውል የተፈረመበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ፎረም ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት ያከናወነቻቸውን ሥራዎችና በቅርቡ ወደ ትግበራ ያስገባችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ያለመ ነው። በፎረሙም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙንና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራትን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ማስገንዘብ ተችሏል ብለዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ማበረታታት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትንም በስፋት ወደ ኢኮኖሚው ማምጣትን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ መድረክ ላይም አስፈላጊ ሂደቶችን ያጠናቀቁ አምስት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች አንድ ነጥብ 6 ቢሊዮን
ዶላር ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራርመዋል። ሌሎች የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ለማፍሰስ በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ከባለሀብቶች ጋር በቅርበት በመሥራት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዚህ መድረክ ኢንቨስትመንቱን ለመደገፍ የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎችን ማስተዋወቅ፣ መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየት፣ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ማስተዋወቅና የበሰሉ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ሥራ ማስገባትን ዓላማ አድርጎ የተካሄደ ነው። በዚህም ከተጠበቀውም በላይ ዓላማውን ማሳካት ችሏል ብለዋል፡፡
ፎረሙ ላይ ለመሳተፍ ለ59 በላይ ሀገራት ተሳታፊዎች መምጣታቸውን ጠቁመው፤ ይህም ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ ሀገር መሆኗን የሚያመላክት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ከ30 በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መኖራቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ስምምነት ከፈረሙት አምስት ኩባንያዎች መካከል ሦስቱ ወደ ተለያዩ ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የሚገቡ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በገንዘብ ሚንስቴር እና በአጋር የልማት ድርጅቶች አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025 ፎረም በትናንትናው እለት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በመድረኩ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችል ውይይትና መግባባት መፈጠሩም ተገልጿል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም