
ዜና ትንታኔ
አሜሪካ ከየመን ሁቲ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሷን ይፋ አድርጋለች፡፡ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ሁነኛ አጋር እስራኤል ደግሞ በሁቲ ይዞታዎች ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሜሪካ በሁቲዎች ላይ የምትፈፅመውን የአየር ጥቃት ልታቆም መሆኑን ከቀናት በፊት ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ ባለፈው ሐሙስ ከካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ማርክ ካርኒይ ጋር በዋይት ሃውስ በተነጋገሩበት መርሃ ግብር ላይ ሀገራቸው በሁቲ ታጣቂዎች ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት ልታቆም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹ሁቲዎች ከአሁን በኋላ መርከቦች ላይ አይተኩሱም። መዋጋት አይፈልጉም፤ እኛ ደግሞ ያን እናከብራለን፤ እናም የአየር ድብደባ ማካሄዳችንን እናቆማለን፤ ስለዚህ እነሱም ጥቃት ማድረሳቸውን አቁመዋል፡፡ ሁቲዎች እንዳስታወቁት፣ ወይንም ቢያንስ ለእኛ እንደገለፁልን፣ ከአሁን በኋላ አይዋጉም፡፡ ነገር ግን የበለጠ ጠቃሚው ነገር ቃላቸውን አምነን መቀበላችን ነው›› ብለዋል።
አሜሪካንና ሁቲዎችን ያሸማገለችው ኦማን ናት። ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ላለመፈጸም መስማማታቸውን ኦማን አስታውቃለች። ውጥረቶች እንዲረግቡ ሀገራቸው ማሸማገሏን የተናገሩት የኦማን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ባድር አል ቡሳይዲ፣ ሁለቱም ወገኖች አንደኛቸው ሌላኛቸው ላይ ጥቃት ላለመሰንዘር መስማማታቸውን ገልጸዋል።
‹‹ወደፊት ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት አይፈጽሙም፤ በቀይ ባሕርም ሆነ በባብ አል መንደብ የአሜሪካ መርከቦችን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች በነጻነት እንዲቀዝፉ እንዲሁም የተሳለጠ ፍሰትን ለማረጋገጥ ተስማምተዋል›› ብለዋል። በሱልጣን ሃይታም ቢን ጣሪቅ አል ሳኢድ የምትመራው ኦማን፣ አሜሪካንና ኢራንን በኑክሌር ጉዳይ እያደራደረች እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ እንደተናገሩት ሁቲዎች መዋጋት የማይፈልጉት ‹‹መዋጋት ስላልቻሉ›› ነው። ትራምፕ ‹‹እነሱ ከዚህ በላይ መዋጋት አይችሉም›› ቢሉም፣ ሁቲዎች ግን ይህን የትራምፕ አባባል ውድቅ አድርገዋል፡፡ የሀውቲ ዋና ተደራዳሪ መሐመድ አብዱል ሰላም፣ ተኩስ አቁም እንዲደረግ የጠየቀችው አሜሪካ እንደሆነች ገልፀዋል፡፡ ‹‹ተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቁ ተደጋጋሚ መልዕክቶች በኦማን በኩል ከአሜሪካ ይደርሱን ነበር፡፡
እኛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥያቄ አላቀረብንም፡፡ የተቀየረው የአሜሪካውያኑ አቋም ነው፤ እኛ ከአቋማችን ዝንፍ አላልንም›› በማለት በታጣቂዎቹ ለሚታዘዘው ‹‹አል ማሲራህ›› የቴሌቪዥን ጣቢያ (Al Masirah TV) ተናግረዋል።
የትራምፕንም ሃሳብ ‹‹ዋሺንግተን ዲሲ የእስራኤልን መርከቦች መጠበቅ ባለመቻሏ ያጋጠማት ፍርሃት መገለጫ›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ስምምነቱን በተግባር ማክበሯን መገምገም እንደሚስፈልግና ስምምነቱን የማታከብር ከሆነ ግን ቡድኑ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል፡፡
ሁቲዎች እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ዘመቻ በመቃወምና ለሃማስ ያላቸውን ወገንተኝነት ለማሳየት ወደ እስራኤል በተደጋጋሚ ሚሳኤል ያስወነጭፋሉ። ነገር ግን የእስራኤል የፀረ-ሚሳኤል መከላከያ ሥርዓትን አልፈው መሬት ላይ የሚያርፉት ጥቂቶቹ ናቸው።
በምላሹ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሁቲ ኃይሎችን ዒላማ በማድረግ የመን ውስጥ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል። በአጸፋው የሁቲ አማጽያን ከእነዚህ ሀገራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሌሎች ሀገራት መርከቦችን ዒላማ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ይህ የአማጺያኑ ጥቃት በርካታ የመርከብ ድርጅቶች በዓለም የባሕር ንግድ ውስጥ 15 በመቶ ድርሻ ያለውን የቀይ ባሕር መስመርን እንዳይጠቀሙ እያስገደዳቸው ነው።
አሜሪካ ካለፈው ወር አጋማሽ ወዲህ በየመን በሀውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎች ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት እየፈፀመች ትገኛለች፡፡ የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ በየመን ሁቲዎች ላይ ስለተፈጸሙት ጥቃቶች ባወጣው ሪፖርት፣ ጦሩ ካለፈው ወር ጀምሮ ከ800 በላይ የአየርና የባሕር ዘመቻ ጥቃቶችን መፈፀሙን ይፋ አድርጓል፡፡ በጥቃቶቹም ‹‹በመቶዎች የሚቆጠሩ የሁቲ ተዋጊዎች እና በርካታ መሪዎች ተገድለዋል›› ብሏል።
በሁቲዎች ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንዲፈጸም ያዘዙት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ሁቲዎች ‹‹ሙሉ ለሙሉ እንደሚደመሰሱ›› ዝተው እንደነበር ይታወሳል። ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፕሬዚዳንትነት መንበሩ ከተመለሱ በኋላ የሁቲ ኃይሎችን ‹‹የውጭ ሽብርተኛ ቡድን›› በማለት ሰይመዋቸዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባይደን ግን ‹‹በየመን ያለውን ሠብዓዊ ቀውስ ለማቃለል›› በሚል ይህንን የቡድኑን ፍረጃ አንስተውት ነበር።
ሁቲዎች ከአሜሪካ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገናል ቢሉም፣ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ሁነኛ አጋር ከሆነችው እስራኤል ጋር ግን በደመኛ ጠላትነታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እስራኤልን እንደማያካትት ሁቲዎች ገልጸዋል፡፡ የቡድኑ ዋና ተደራዳሪ መሀመድ አብደል ሰላም ‹‹ስምምነቱ በምንም ዓይነት ሁኔታ እስራኤልን አይመለከትም›› በማለት ለ ‹ሮይተርስ› የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡
እስራኤልም በሁቲ ይዞታዎች ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ የሁቲ ታጣቂዎች ከአንድ ሳምንት በፊት ወደ እስራኤል ያስወነጨፉት እና አሜሪካ ሰራሹ ‹‹ታድ›› ፀረ-ሚሳኤል እና የእስራኤል የረጅም ርቀት የሚሳኤል መከላከያ ቴክኖሎጂዎች ሊያከሽፉት ያልቻሉት ባሊስቲክ ሚሳኤል፣ በርካታ መንገደኞችን በሚያስተናግደውና በማዕከላዊ እስራኤል በሚገኘው የቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ወድቆ በሰዎች፣ በመንገድና በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፤ በረራዎች እንዲስተጓጎሉና እንዲሰረዙ አድርጎ ነበር፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁም ሁቲዎች የሚፈፅሟቸው ጥቃቶች ጀርባ ሁሉ ኢራን እንዳለች ገልጸው፣ ‹‹እስራኤል በመረጠችውና ባቀደችው ጊዜና ቦታ በዋናው አውሮፕላን ማረፊያችን ላይ ለተፈፀመው የሁቲዎች ጥቃት ለሽብር አለቆቻቸው ለኢራን ምላሽ ትሰጣለች›› ብለው ነበር፡፡ እግረ መንገዳቸውንም እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ማጥቃት እንደምትገፋበትና ሀማስ የሚባል ቡድን በጋዛ ህልውና እንደማይኖረው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ተናግረው ነበር፡፡
የአጸፋ ርምጃ እንደምትወስድ የዛተችው እስራኤል ትናንት በሆዴይዳህ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ሦስት ወደቦች ላይ ጥቃት ፈፅማለች፡፡ ባለፈው ሳምንት የሁቲ ኃይሎች የአቅርቦት ማዕከል የሆኑት የሆዴይዳህ ወደብና ከወደቡ በስተምስራቅ የሚገኝ የሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም የሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያና ሌሎች ስፍራዎች በእስራኤል ጦር ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ይታወሳል። የሆዴይዳህ ወደብ የሀውቲ ታጣቂዎች ከኢራን የጦር መሣሪያ የሚያስተላልፉባት ወደብ በመሆኗ የጥቃት ኢላማ እንደሆነች የእስራኤል ጦር ገልጿል፡፡
ሁቲዎችም እስራኤል ለሰነዘረችባቸው ጥቃቶች ከባድ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል፡፡ የየመን የፖለቲካ ጠቅላይ ምክር ቤት ሊቀመንበር ማህዲ አል-ማሻት የሰንዓ ምላሽ አውዳሚ፣ ክፉኛ የሚያሳምምና እስራኤል ከምትገምተውና ልትቋቋመው ከምትችለው በላይ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹ከአሁን ጀምሮ በመጠለያችሁ ውስጥ ቆዩ፤ አልያም ወደምትሄዱበት ሂዱ፡፡ ከዚህ በኋላ የከሸፈው መንግሥታችሁ እናንተን ከጥቃት ሊጠብቃችሁ አይችልም›› በማለት ለእስራኤል ዜጎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሁቲ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀኔራል ያህያ ሳሪ በበኩላቸው፣ የትኛውም ዓይነት ወረራና ጥቃት የመን የፍልስጤማውያን ጭፍጨፋና የጋዛ ከበባ እንዲያቆም ለማድረግ ፍልስጤምን ከመደገፍ እንደማያግዳት ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ የእስራኤል መርከቦች በቀይ ባሕርና በአረቢያ ባህር ላይ እንዳያልፉ እንዲሁም የቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት እንዳይሰጥ የጀመረውን ርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል፡፡
እስራኤል ከሁቲዎች ጋር የምታደርገውን ጦርነት አፋፍማ በቀጠለችበት ሁኔታ፣ ዋና አጋሯ አሜሪካ ግን ከሁቲዎች ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረሟ በብዙ ወገኖች ዘንድ ጥያቄዎችን ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።
ሁቲዎች አሜሪካ ከወዳጇ ከእስራኤል ተነጥላ ስምምነቱን መፈረሟን እንደድል ቆጥረውታል፡፡ የቡድኑ ዋና ተደራዳሪ መሀመድ አብደል ሰላም የአሜሪካ እርምጃ እስራኤልን የሚያሳዝን ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እስራኤሎች በየመን ተራሮች ተውጠው ከመቅረት ለማምለጥ ሲሉ የተኩስ አቁም ስምምነት በፈረሙት በአሜሪካውያኑ አቋም አዝነዋል፡፡ ስምምነቱ እስራኤልን ብቸኛ አድርጎ አስቀርቷል›› ብለዋል፡፡
የዮርዳኖስ ኮሙኒስት ፓርቲ (Jordanian Communist Party) አባል ኢማድ አል-ሃታቤህ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ያልመለሳቸው ብዙ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ኦማን በአሜሪካ-ኢራን የኑክሌር ድርድር ውስጥ ያላትን ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የቀይ ባሕሩ የተኩስ ማቆም ስምምነት የኑክሌር ድርድሩ አካል ነው? አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመስማማት ብላ አንዳንድ የእስራኤል ፍላጎቶችን ወደ ጎን ትላቸዋለች? ስምምነቱ እስራኤልን እንደማይመለከት በመገለጹ፣ ይህ ስምምነት ለኔታንያሁን መንግሥት ምን ዓይነት ቦታ አለው?›› በማለት የተኩስ ማቆም ስምምነቱ ያልመለሳቸውን ጥያቄዎች ዘርዝረዋል፡፡
ስምምነቱን ‹‹በጦርነቱ መሀል የተሰማ የቀይ ባሕር ድንገተኛ ክስተት›› እንደሆነ የተናገሩት አል-ሃታቤህ፣ ‹‹ስምምነቱ የተፈረመው ሀውቲዎች በእስራኤል ቤን ጉሪዮን አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ ከፈፀሙት ጥቃት ሰዓታት በኋላ ነው፡፡ አሜሪካና ስለጥቃቱ ምንም ነገር አለመናገሯ አስገራሚ ሆኖ ተስተውሏል›› ብለዋል፡፡
የአልጀዚራው አሊ ሃሸም፣ ሁቲዎች በአሜሪካ መርከቦች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት እንዲያረግቡ የመከረቻቸው ኢራን ሳትሆን እንደማትቀር ዘግቧል። ‹‹በአሜሪካና በኢራን መካከል የሚደረገውን ድርድር የምትመራው ኦማን ናት፡፡ አሁን ደግሞ ሁቲዎችንና አሜሪካን አደራድራለች፡፡ ሁቲዎች ጥቃታቸውን እንዲያቆሙ ያሳመነቻቸው ኢራን ትሆናለች፡፡ ይህ ደግሞ የአሜሪካ-ኢራን የኑክሌር ድርድር እንዲፋጠን እንደማበረታቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ማዕቀቦችን በማንሳት ኑክሌር ማበልጸግን የመግታት ስምምነት ላይ የመድረስ ርምጃ እየተፋጠነ እንደሆነ የሚያመለክቱ ነገሮች አሉ›› በማለት አብራርቷል፡፡
‹‹ማዕቀቦችን በማንሳት የኑክሌር ማበልጸግን የመግታት ስምምነት›› ደግሞ ኢራን ፈፅሞ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን እንደሌለባት ለምታምነው እስራኤል አስተማማኝና ተመራጭ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ እስራኤል የኢራንን የኑክሌር መሠረተ ልማቶችን ማውደምን ትመርጣለች፡፡
በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሁካቢ፣ ‹‹አሜሪካ ከሁቲዎች ጋር ለመደራደር የእስራኤልን ፈቃድ መጠየቅ አይገባትም፡፡ አሜሪካ ሁቲዎች በእስራኤል ላይ ለሚሰነዝሩት ጥቃት ምላሽ የምትሰጠው እስራኤል ውስጥ የሚኖሩ አሜሪካውያን ዜጎች ከተጎዱ ብቻ ነው›› ማለታቸው አሜሪካ በቀጣናው እስራኤልን በቀጥታ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የምትወስነው አይሁዳዊቷን አጋሯን አማክራ ነው የሚል እምነት ላላቸው ሰዎች የሚዋጥ አልሆነም፡፡
አምባሳደሩ ‹‹ከፕሬዚዳንቱና ከምክትላቸው ጋር ተነጋግሬያለሁ፡፡ እስራኤል ውስጥ 700 ሺ አሜሪካውያን ይኖራሉ፡፡ ሁቲዎች በድርጊታቸው ቀጥለው እስራኤል ውስጥ የሚኖር አንድ አሜሪካዊ ከተጎዳ ነገሩ የእኛ ጉዳይ ይሆናል›› ብለዋል፡፡
የአልጀዚራው ማይክ ሃና ደግሞ ከዋሺንግተን ዲሲ ባሰራጨው ዘገባ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ስምምነቱ እስራኤል ከሁቲዎች ጋር ካላት ግጭት ጋር ግንኙነት እንደሌለው ስለመግለጹ ጠቁሟል፡፡ ‹‹ስምምነቱ ሁቲዎች በአሜሪካ መርከቦች ላይ ከሚፈፅሙት ጥቃት ጋር የተያያዘ ብቻ እንደሆነ ሚንስቴሩ በግልፅ አሳውቋል›› ብሏል፡፡
የሆነው ሆኖ ከሃማስ፣ ከሄዝቦላህ፣ ከሁቲ፣ ከኢራንና ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር የምፋለመው ለህልውናዋ እንደሆነ ከምስረታዋ ማግሥት ጀምሮ ደጋግማ የምትናገረው እስራኤል፣ በብዙ ሁኔታዎች ውስጥ ሆና ከእነዚህ ቡድኖች ጋር መፋለሟ የተመደ በመሆኑ፣ ዋና አጋሯ አሜሪካ ከሁቲዎች ጋር በደረሰችው የተኩስ ማቆም ስምምነት ምክንያት አኩርፋ የምትገታው ጥቃትም ሆነ የምትሰርዘው ወዳጅነት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም