ኢትዮጵያ ያላት ስትራቴጂካዊ መገኛ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት የፕላንና ልማት ሚንስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚንስትሯ በኢንቨስመንት ኢትዮጵያ 2025 ቢዝነስ ፎርም ላይ ባደረጉት ገለጻ እንዳመለከቱት ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ስትራቴጂካዊ መገኛና ሰፊ ተደራሽነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ሀገር እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊና በማደግ ላይ ያለ የሀገር ውስጥ ገበያ እንዳላት ጠቅሰው፤ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) መሥራች መሆኗም የ560 ሚሊዮን ሕዝብን የገበያ ዕድል ማግኘት እንደሚያስችላት አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣናም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ሰዎችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ግዙፍ ነጻ ንግድ ቀጣና እንደሆነም የጠቆሙት ሚንስትሯ፤ ይህም ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ገበያ ለመግባትም ቀዳሚ ተመራጭ ሀገር ያደርጋታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቂ የሰው ኃይልን ጨምሮ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች አሏት ያሉት ሚንስትሯ፤ ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ 54 ሚሊዮኑ ወጣትና የሰለጠነ የሰው ኃይል መሆኑም ሌላኛው ምቹ ሁኔታ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በሰብሰሃራን አፍሪካ ካሉ አምስት ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዱ የኢትዮጵያ መሆኑም ተጨማሪ ዕድል መሆኑን ፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን አስታውሰዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2023/24 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሏን አመላክተው፤ ይህም በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ፣ በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ 3ኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል ብለዋል፡፡

በጥቅሉ ሲታይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው ያሉት ፍፁም (ዶ/ር)፤ ባለፈው ዓመት የግብርናው ዘርፍ በ6 ነጥብ 9 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉ 9 ነጥብ 2 በመቶ፣ የአገልግሎት ዘርፉ 7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውንም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምና የፖሊሲ ማሻሻያ ርምጃዎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጨማሪ መደላድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመላክተው፤ ባለሀብቶች ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች በመገንዘብ በመረጡት ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You