
የሌማት ትሩፋት ሰዎች የመንደራቸውን እና የደጃፋቸውን ጸጋ ተጠቅመው እያመረቱ የተመጣጠነ ምግብ እንዲመገቡና የምግብ ዋስትናቸውንም እንዲያረጋግጡ የተዘረጋ አዲስ ኢንሼቲቭ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ፕሮግራም በተለይም ከከተማ ግብርና ጋር ተጣምሮ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ አመቺነት ባላቸው መንደሮችና ደጃፎች ሁሉ የጎጆ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እየተመረቱ ይገኛል፡፡ ለዚህም የሀረር ከተማ ተሞክሮን እንመልከት፡፡
በሀረሪ ክልል፤ ሀረር ከተማ በዶሮ ርባታ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል አንዱ አኑዋር ሸምሰዲን ነው፡፡ አኑዋር የኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ነው፡፡ በተመረቀበት ሙያ ሥራ በማፈላለግ ጊዜውን ማባከን ሳያስፈልገው ገና በጠዋቱ ወደ ዶሮ ርባታ እንደገባ ይናገራል።
‹‹አባቴ የእንስሳት ህክምና ሠራተኛ ስለነበር ልጅ ሆኜ ዶሮዎችን ሲያረባና ሲንከባከብ አይ ነበር›› የሚለው አኑዋር የአባቱን ሥራ አስፋፍቶ የመሥራት ፍላጎት ያደረበት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ ይገልጻል። በዚህም የተነሳ ቤተሰቦቹ የሰጡትን መነሻ ካፒታል ይዞ ጥቂት የእንቁላል ዶሮዎችን በመግዛት ነበር ሥራ የጀመረው።
የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር እንደሀገር ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ደግሞ ከወንድሙ ጋር ተደራጅቶ የብድር አገልግሎት እንዲያገኝና ሥራውን አስፋፍቶ የመሥራት እድል እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ዛሬ ከሌማት የተረፈ እና ለገበያ የሚቀርብ የእንቁላል ምርት እያፈሰ ይገኛል፡፡ የዶሮዎቹን ብዛት 3 ሺህ 500 አድርሷል፡፡ በቀን ከ2ሺህ 500 እንቁላል በላይ ያገኛል፡፡
ይሁንና አልፎ አልፎ በሚከሰት የዶሮ በሽታ ምክንያት በአንድ ወቅት ውጤታማነቱን የማስቀጠል ችግር አጋጥሞት እንደነበር እና እስከ መክሰር ደረጃ እንደደረሰም ያስታውሳል፡፡
አኑዋር አሁን ከኪሳራ አገግሞ የ2 ሚሊዮን ብር ካፒታል እያንቀሳቀሰ እንደሚገኝ እና በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ለ150 ሰዎች የሥራ እድል እንደፈጠረ ይናገራል፡፡ የእንቁላል ምርቱን ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግ ገበያውን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ያስረዳል። ከእርሱ የሚረከቡ ነጋዴዎች ከአካባቢው ሰው ፍላጎት የሚተርፈውን ምርት ወደ ሶማሊላንድ እየወሰዱ መሸጥ መጀመራቸውን ይጠቅሳል፡፡ በቀጣይ ራሱን ችሎ ከፍተኛ የእንቁላል ምርት ወደ ሶማሊላንድ በመላክ የውጭ ምንዛሪ የማስገባት እቅድ እንዳለው ያስረዳል፡፡
ጎን ለጎንም ዶሮዎቹ ምርታማነታቸው እንዲጨምርና እንቁላላቸው የተሟላ ንጥረ ነገር እንዲኖረው ለማድረግ እንደ አልፋ-አልፋ እና ቆስጣን የመሳሰሉ በሙያተኞች የተመረጡ የዶሮ መኖዎችን እያመረተ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡
እንደ ብላክ ሶልጀርፊላይ፣ ኃይድሮ ፖኒክፎደር የመሳሰሉ የዶሮ መኖዎችን የማምረት ጅምር ላይ እንዳለም ይገልጻል፡፡ በተለይም ኃይድሮ ፖኒክፎደር አንድ ኪሎ በቆሎን ስምንት ኪሎ ቦቆሎ እንዲሰጥ አድርጎ የማምረት ሂደት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በሙከራ ደረጃ በሠራው ሥራም ውጤት ማየት እንደቻለ ገልጿል፡፡ ይሁንና ሥራውን በስፋት ለማከናወን ውሃ የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቅሶ የሚመለከታቸው አካላት የውሃ አቅርቦት ጥያቄውን እንዲመልሱለት መልእክት አስተላልፏል። እስከ አሁንም የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ የግብርና ባለሙያዎችና ቤተሰቦቹ ያደረጉለት ድጋፍ ለዚህ ደረጃ እንዳበቃው ተናግሯል፡፡
ወደ ፊትም በዓሳ እና በፍየል ርባታ ላይ ለመሠማራት እቅድ እንዳለው አስረድቷል፡፡ የዶሮዎችን ተረፈ ምርት ዓሳው ለምግብነት መጠቀም የሚችል በመሆኑ ውጤታማነቱ ከዚህም የበለጠ አስተማማኝ እንደሚሆን ተስፋ አድርጓል፡፡
የሀረሪ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሮዛ አህመድ በበኩላቸው እንደሚያስረዱት፤ የሌማት ትሩፋት እንደሀገር ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ክልሉ አቅዶችን አውጥቶ በከተማም ሆነ በገጠር የተለያዩ ሥራዎችን እየተገበረ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሠረት የወተት መንድር፣ የማር መንደር፣ የዶሮና የዓሣ መንደሮችን በመለየት እና የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማትም ህብረተሰቡ እንደ አመቺነቱ በእነዚህ ዘርፎች ተሳታፊ እንዲሆን ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡
በሀረሪ ክልል ዶሮን የማርባት ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ወጣቶች ተደራጅተው ከሚሠሩት ሥራ በተጨማሪ ሴቶችም በዶሮ ርባታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተመረጡ አካባቢዎች ለሚገኙ እማወራዎች ለእያንዳንዳቸው 25 የዶሮ ጫጩቶችን በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ስለመደረጉ ገልጸዋል። ይህ ተግባር የአካባቢውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በእጅጉ ረድቷል ይላሉ፡፡
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም