‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት አበርክቶው የላቀ ነው››- ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን

– ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

የዛሬው የዘመን እንግዳችን ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን ይባላሉ። የተወለዱት በቀድሞ ወሎ ክፍለ ሀገር ደሴ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸወን አሰብ አስፋው ወሰን እና አዲስ አበባ በሚገኘው ፍሬ ሕይወት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ተግባረድ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን በንድፈ ሥራ ትምህርት ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል። በመቀጠልም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፤ በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። ለንደን በሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ኢንጂነር ጌታሁን ባላቸው እውቀትና ተሞክሮ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በበጎ ፍቃድ እያገለገሉ ካሉ ሀገር ወዳድ ምሁራን አንዱ ሲሆኑ በርካታ ማህበራትን በማቋቋምም ችግር ፈቺ ሥራዎችን በመሥራት፤ ለፖሊሲ ግብዓት የሆኑ ሃሳቦችን በማመንጨትና በሀገር ሰላምና አብሮነት መጠናከር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰው ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በበጎ ፍቃድ እያገለገሉ ካሉባቸው በርካታ ተቋማትና ማህበራት መካከልም የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነት፣ የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማት እና የዲሞክራሲ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ(የምሁራን ፎረም) በሰብሳቢነትና የኢትዮጵያ የሲቪል እና የሙያ ማህበራት ምክር ቤት በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።

ከዚህም ባሻገር የታላቁ ሕዳሴ አሠሪ ሕዝባዊ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስተዳደር የቦርድ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን ጋር ያደረገውን ውይይት እንደሚከተለው ይዞ ቀርቧል።

አዲስ ዘመን፡- በርካታ ማህበራትና ድርጅቶችን በኃላፊነት መምራት ይታወቃሉ፤ ይሄ ከምን የመነጨ እንደሆነ ያስረዱንና ወደ ውይይታችን እንግባ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- በመሠረቱ ብዙ ቦታዎች ላይ ገብቶ ማገልገል በአንድ በኩል መታደል ነው፤ ፀጋም ነው። ምክንያቱም ለሀገር፣ ለወገንና ለመልካም ነገር ጊዜን ጉልበትንና አቅምን ማዋል ከምንም በላይ ርካታ የሚፈጥር ነው። ሀገርንና ማኅበረሰብን ሊጠቅምና ሊያግዝ በሚችል መልኩ መሥራት፤ ለሀገራችን ሰላም እድገት፣ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ብሎም ለሌሎች ሀገሮች ምሳሌ የምትሆን ሀገር እንድትኖረን ከመሰል ኢትዮጵያውያን ጋር በመሥራቴም ራሴን እንደ እድለኛ ነው የምቆጥረው። ለዚህም ነው በተጠየኩበት ቦታ ሁሉ እምቢ አልልም፤ ምክንያቱም እምቢታ መሸነፍ ነው ብዬ ስለማምንና ሰው የአቅሙን ማበርከት ይገባዋል ብዬም ስለማምን ጭምር ነው። በሕይወት እስካለን ድረስ ሀገርንና ወገንን ማገልገል ህሊናዊም ፤ ሞራላዊም መንፈሳዊ ርካታ ስለሚሰጠኝ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ምሁራን በበጎ ፈቃድ ላይ ሲሳተፍ አይታይም፤ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- በመሠረቱ እኔ በዚህ ሃሳብ አልስማም፤ ታሪካችን እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ቀድማ ምሁር ያፈራችና በሊቅሃን ሀብት ረገድ የታደለች ሀገር ናት። ግን በተለያዩ ጊዜያት እነዚህ ምሁራን መጠቀም አልቻልንም። ይህ የሆነው ምሁራኑ ሀገራቸውንና ወገናቸውን ማገልገል ስላልፈለጉ ሳይሆን ሁኔታዎች ምቹ ባለመሆናቸው ነው ባይ ነኝ። እኛ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ብለን ”የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ሕዝባዊ ምክክር መድረክ” የሚል የምሁራን ፎረም አቋቁመናል። ምሁራን በየዘርፋቸው ለሀገር እድገትና ልማት እውቀታቸውን እንዲያውሉ ለማድረግ በማሰብ ነው ያቋቋምነው። ምክንያቱም ያሳደጋቸውን፤ ያስተማራቸውንና ነፃ ያወጣቸውን ሕዝብ በተማሩት ትምህርት የአቅማቸውን ማበርከት የሚገባቸው በመሆኑ ነው።

ይህንን የቲንክ ታንክ መድረክ ያቋቋምነው የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በነበሩበት ወቅት ሲሆን ፎረሙ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በማፍለቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት ቆይቷል። ከእነዚህም መካከል በመንግሥትም ተቀባይነት ያገኙ በርካታ ግብዓቶችን አቅርበናል። እንዲያውም በኢህአዴግ ጉባኤዎች ላይ እየተጋበዝን ኢህአዴግ በሚያካሂዳቸው የፖሊሲ ሃሳቦች ላይ ሃሳብ እንሰጥ ነበር። ስለዚህ በብዙ መንገድ ድጋፍ እናደርግ ነበር። ለምሳሌ በዓባይ ግድብ ዙሪያ ላይ የሕዝባዊ ምክር ቤት አባል ነበር። ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ ግንባታው የተሳካ እንዲሆን ፤ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የዓባይ ተፋሰሶችን የአፈርና ውሃ ጥበቃ በምን መልኩ ሊሠራ እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ሃሳብ አቅርበናል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ በጥቅሉ የሀገራችን ምሁራን አስተዋፅኦ እንዳላደረጉ ሊቆጠር አይገባም። ግን ደግሞ እድሉ ስልተሰጣቸው ጎልተው ሊወጡ አልቻሉም። በሌላ በኩል በሚያገለግሉበት ዘርፍ ተመጣጣኝ ክፍያ ስለማይከፈላቸው፤ ስለሚገለሉ፤ በተለያየ መንገድ ተፅዕኖ ስለሚደርስባቸው ሀገር ጥለው የተሻለ ፍለጋ የሚሰደዱበት ሁኔታ አለ። ከዚያ ባሻገር ያለውን ችግር ተጋፍጠው ለሀገርና ለሕዝብ ዋጋ እየከፈሉ የሚኖሩ በርካታ ምሁራን መኖራቸውን ልንዘነጋ አይገባም። ምሁራኑ ያላቸውን እምቅ አቅም ለሀገር እድገት ጥቅም ላይ እንዲያውሉት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይገባል፤ በተለይ መንግሥት ሰብዓዊ መብታቸውን ጠብቆ፤ አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ የሚመጥን ክፍያ በመስጠት ሁሉም በየዘርፍ አቅሙን አሟጦ እንዲጠቀም ማድረግ ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር በተለይ በግብርናው ዘርፍ ለኢትዮጵያ አይደለም ለአፍሪካ ጭምር ሊተርፉ የሚችሉ ምሁራን እዚህ ምቹ ሁኔታ ባለማግኘታቸው ወደ ሌላ ሀገር የሚሰደዱበት አጋጣሚን መጥቀስ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የሚመሩት የኢትዮጵያ ሰላም የልማትና የዲሞክራሲ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ ከተቋቋመበት ተልዕኮ አንፃር በተለይ በየአካባቢው ያለውን ግጭት እንዲቆም በማድረግ ረገድ ምን ሠርቷል?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- መድረኩ እንደ አፍሪካ የመጀመሪያና ትልቅ የምሁራን ስብስብ የያዘ ነው። ሁሉንም የሚያሳትፍ ነፃ አስተሳሰብ ያላቸው ስብስብ ነው። የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ተፅዕኖ የሌለባቸው ምሁራን ለሀገር ጥቅም የሚመክሩበትም ጭምር ነው። አስቀድሜ እንደገለፅኩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በነበሩበት ወቅትም በተለይ ሰላም ግንባታ ላይ ብዙ ሠርተናል። ለምሳሌ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልል አዋሳኝ ላይ የነበረ ከፍተኛ ግጭት የሀገር ሽማግሌዎችን ሕብረት በማቋቋም ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን የበላይ ጠባቂ በማድረግ፤ የክልሎቹን ፕሬዚዳንቶች በማነጋገር በብዙ ጥረት በሽምግልና እንዲፈታ ያደረገው ይኸው ፎረም ነው። በበሰለ መንገድ በጥሩ ዲፕሎማሲ አግባብ ግጭቶችን መፍቻ መንገድ በመጠቀም መልካም የሚባሉ ሥራዎችን ሠርተናል።

እንዲሁም የአፋርና ኢሳ መካከል የነበረው ግጭትን ለማስቀረትና በባሕላዊ ሥርዓት መሠረት እርቅ እንዲወርድ የሁለቱንም ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን አግባብተን የጋራ ኮሚቴ እንዲዋቀር አድርገን ችግሩ ዳግመኛ እንዳይፈጠር፤ ብሎም የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ጥረት አድርገናል። ግን ደግሞ በወቅቱ የነበሩት ፖለቲከኞች ራሳቸው ኮንትሮባንዲስቶች ስለነበሩ ግጭቱ እንዲረግብ አይፈልጉም ነበርና ጥረታችን ሳይሰምር ቀረ፤ አሁንም ድረስ በየጊዜው ተመሳሳይ ችግሮች ሲከሰቱ እንመለከታለን። በሌላ በኩል አሁን ላይ በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት አንድ ጠንካራ የሽማግሌዎች ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል። በተለይ መንግሥት ካገዘን በክልሉ ሰላም እንዲወርድ የቻልነውን ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅተናል። እንደ ሽማግሌም፤ እንደ ምሁርም ገልለተኛ በሆነ መንገድ፤ ሁለቱንም በሚያግባባ መልኩ በአንድ መድረክ ላይ እንዲግባቡ ለማድረግ ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። በማይግባቡበት ላይ ሽማግሌዎች ገብተው የሚዳኙበትን ሁኔታ የሚፈጠር ይሆናል።

በነገራችን ላይ የኬንያውያን እርቅ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ የእኛ ፎረም ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። የኮፊ አናን መልዕክተኛ ሆነው የኬንያን ሰላምና እርቅ መርሃ ግብር የመሩት የእኛ ፎረም አባል የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ዲንቃ (ዶ/ር) ናቸው። በእኛም ሀገር ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሰላም ለማስፈን በመጀመሪያ ምህረት ማድረግና ይቅርታ የማድረግ ልምድ ልናዳብር ይገባል። ይቅርታ ማድረግ ውርደት አይደለም፤ የእውቀት የመጨረሻው ጥግ እንጂ፤ ማንም ይሁን ማን ከልቡ ይቅር ማለትና ወደፊት መራመድ ይገባዋል። ወደ ሰላምና መግባባት መሄድ የሚቻለውም ልባዊ በሆነ መንገድ ይቅር ማለት ስንችል ነው። መድረኩ ከሀገር አልፎ በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኢትዮጵያ ፕብሊክ ዲፕሎማሲ እንዲዋቀር ሃሳብ ያቀረብነው እኛ ነን። የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመሩት የሕዳሴ ግድብ ብሔራዊ አሠሪ ኮሚቴ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ አቅርበናል። ሃሳባችን ተቀባይነት አግኝቶ ነው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የተቋቋመው።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ሰላም እንዲሰፍን ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- በእኔ እምነት ከሁሉም በፊት ለሰላም ጠንቅ የሆኑትን ነገሮች ማጥራት ያስፈልጋል። ብዙዎቻችንን በመጀመሪያ ደረጃ ሀገራዊ የሆነ አስተሳሰብና የሀገር ፍቅር እንዲኖረን ከቤተሰብ ጀምሮ ትውልዱ እያጣ ነው የመጣው። ትውልዱ ግብረገብና ማህበራዊ እሴቶችን አክብረን እንዲያድግ ባለመደረጉ ነው ግጭቶች እየተስፋፉ የመጡት ባይ ነኝ። ትወልዱ በራሱ ላይ ሊደርስ የማይፈልገውን በሌላ ላይ ማድረስ እንደማይገባ አልተነገረውም።

ይህን ዓይነቱን አስተሳሰብ ከታች ጀምረን እያሳደግን መምጣት አልቻልንም። በሌላ በኩል መንግሥት ፖሊሲ ሲያወጣ ሕዝቡ የሚደግፈው መሆን አለበት፤ የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት ሕዝብን ያሳተፈ የፖሊሲ ግብዓት ማዘጋጀት ይፈልጋል። ይህንን ማድረጋችን ለሰላም ጠንቅ የሆኑ ችግሮችን አስቀድሞ ለመቅረፍ ያስችለናል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ከልብ በሆነ መልኩ ይቅር ለመባባል መዘጋጀት ይኖርብናል። ምክንያቱም ይቅርታ የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ ነው። አስቀድሜ እንደገለፅኩት ይቅርታ መሸነፍ አይደለም። እውቀት ነው፤ ልህቀት ነው። ትልቅ ሀብትና ፀጋ ነው። ከይቅርታ በኋላ የጋራ መግባባት ላይ መደረስ አለበት። ለቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲህ ዓይነቱ የሰላም እጦትና ግጭቶችን ለማስወገድ አራት ምክረ ሃሳቦችን ሰጥተናቸው ነበር። ስለዚህ ከአሁን በኋላም ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ የሰው ሕይወት በየጊዜው እያለፈ፤ ሀብት፣ ቅርሳችንን ገንዘባችን እየወደመ፤ የሀገር ገፅታ እየጠፋ ነው ያለው።

ለዚህ ደግሞ በተለይ መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ ወገኖቻችንን እንዲሁም ሳይገባ ልቡ ሸፍቶ የተቀመጠውን ሳይቀር በሀገር ጉዳይ ላይ የሚሳተፍበትን እድል ሊፈጥር ይገባል። የጠፋ ጠፍቷል፤ ግን ደግሞ እንዳይደገም በሆደ ሰፊነት ሁሉንም በሚያግባባ መልኩ ተቀራርቦ መሥራት፤ ችግራቸውን ማድመጥና እንዲፈታ ቁርጠኝነቱን ሊያሳይ ይገባል። በሀገራዊ መግባባት ኮሚሽኑ እየተሠራ ካለው ሥራ ጎን ለጎን ነፃ የሆኑ ምሁራን ኃላፊነቱን ወስደው መንግሥትን ማገዝ ይኖርባቸዋል። መንግሥት እድሉን ሊፈጠር ይገባል፤ ምሁራንም አንኳክተው ጭምር ለመፍትሔ ሊሠሩ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ሌላው እርስዎ የሚመሩት የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን በተለይ በአሠሪውና በሠራተኛው መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በመፍታት ረገድ ምን አበርክቶ አምጥቷል ማለት ይቻላል?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን የሀገር፤ የመንግሥት፤ የማኅበረሰቡ፤ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የሰላም የጀርባ አጥንት ናቸው። አሠሪ ከሌላ ሠራተኛ አይኖርም፤ ሠራተኛ ከሌላ ደግሞ ምርት አይኖርም፤ ኢኮኖሚያዊ እድገት ሊመጣ አይችልም። አሠሪ ሲኖር ሠራተኛ ይኖራል፤ ሠራተኞች ደግሞ ከበስተጀርባቸው ብዙ ቤተሰብ አላቸው። አሠሪ ሁሉ ነገር ተመቻችቶለት በሀገሪቱ ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ አሠሪዎችን የሚያስተዳድረው ሕግና ደንብ   እንዲጠበቅ አድርጓል።

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ የአሠሪዎችን ኮንቬንሽን በጄነባ የፈረመችው ሀገር ነች። ኮንቬንሽኑ አሠሪ፣ ሠራተኛና መንግሥት በሶስትዬሽ በጋራ በእኩልነት የሚመክሩበት መድረክ ነው። አሠሪው ለበርካቶች የሥራ እድል የሚፈጥር እንደመሆኑ፤ ጨዋ አሠሪ እንዲሆን፣ ሕግና ሥርዓትን እንዲያከብር በማድረግ፣ የሥራ አካባቢ ደህንነት፣ መብት እንዲጠበቅ በማድረግ ረገድ ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል።

ከሁሉ በላይ ግን ሀገርን የሚወድ፣ ጨዋ፣ ሕግና ሥርዓትን የሚያከብር፣ ኮንትሮባንድ የማይነግድ፣ በጊዜው የሚፈለግበትን የመንግሥት ግዴታውን የሚወጣ፣ ሠራተኞችን የሚያከብር፣ መብታቸውን የሚጠብቅና የሚያበረታታ፣ በአሠሪዎች ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ እንዲወገድ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው። በግጭት በመካሰስ ሳይሆን ችግሮችን በማኅበራዊ መድረክ መፍታት የሚቻልበትንም ሥርዓት በመፍጠር የበኩሉን ጥረት አድርጓል። የኢትዮጵያ አሠሪዎች ወደ አንድ እንዲመጡ በማድረግም የኮንፌዴሬሽኑ አበርክቶ ከፍተኛ ነው። ከዚያ አልፈን የአፍሪካ አሠሪዎች ሕብረት አባልም ጭምር መሆን ችለናል። በተለይ ከስደት ተመላሾችና የሌላ ሀገር ስደተኞች ሳይቀሩ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፤ መብታቸው እንዲጠበቅ በማድረግም ኮንፌዴሬሽኑ ጠንካራ ሥራ ነው የሚሠራው።

በርግጥ በአሁኑ ወቅት ብዙ ተፅዕኖዎች አሉበት፤ የባንክ ብድር እያገኘ አይደለም፤ የተማረ የሰው ኃይል አያገኝም፤ በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች በሥራው ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ለአሠሪው እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ አነስተኛ በመሆኑ ሚናውን በሚገባ እንዳይወጣ አድርጎታል። እንዲያውም የውጭ ኢንቨስተሮች እየመጡ የኢትዮጵያ አሠሪዎችን እየገፉ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። በመሠረቱ ኮንፌዴሬሽኑ የኢትዮጵያ አሠሪዎችና መንግሥት በጋራ የሚሠሩበት፤ በሥሩ በርካታ ፌዴሬሽኖች ያሉ ትልቅ መድረክ ነው። በዚህ ረገድ ብዙ የግንዛቤ መድረኮችን ፈጥረናል፤ በተለይ በምርታማነት ላይ፤ ሕግና ደንቦች ላይ እንዲሁም የሥራ ጥራት ትስስር ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ሠርተናል። እርስ በርስ የሚደጋገፉበት፤ አንዱ የሌላውን ክፍተት የሚሞላበት፤ ግብዓት የሚያመርትበት ሁኔታ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የሚያበረታታ ሥራ እየተሠራ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ምን ይመስላሉ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ኢንዱስትሪውን አቅም ለማሳደግ መንግሥት የተቻለውን ጥረት እያደረገ መሆኑን እረዳለሁ። ግን እድገቱ እንደጠበቅነው እየሄደ አይደለም። ኢትዮጵያ ካላት የተፈጥሮ ሀብት፣ ታላቅ ፍላጎት አኳያ ኢንዱስትሪው ማደግ ነበረበት። ኢንዱስትሪው ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፤ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ማደግ መቻል አለበት። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እውቀቱና አቅሙ ያላቸውን አካላት መንግሥት ማሽነሪ የሚገዙበት የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻቸት፣ ክህሎትን በማሳደግ፣ የሥራ አካባቢን ምቹ በማድረግ፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር ሊደግፋቸው ይገባል። በተለይ መነሻ ካፒታል በፋይናንስ ተቋማት በኩል እንዲያገኙ በማድረግ ልዩ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል የሚል እምነት አለኝ።

የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ እንዲሰጣቸውን ማበረታቻ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል። ዝም ብሎ ብቻ ያዋጣኛል ብሎ ባለሀብቱ የሚያመርተው ምናልባት በጥሩ ጥናት ላይ የተመሠረተ ላይሆን ይችላል። መንግሥት የሀገሪቱን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ሊያበረታታቸውና ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር ሊደግፋቸው ይገባል።

በሌላ በኩል ኢንዱስትሪዎች እንደሚያመርቱትና እንደሚጠቀሙት ግብዓት ታይቶ በየክልሉ መቋቋም መቻል አለባቸው። በሚቋቋሙበት ቦታ ደግሞ ማኅበራዊ ደህንነታቸው ሊጠበቅላቸው ይገባል። በተለይ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ኢንሹራንስ በአግባቡ የሚያገኙበት እድል መፍጠር ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ የፖሊሲ አውጪው መንግሥት ኃላፊነት ብቻ አይደለም፤ ኩባንያዎቹ መሪ ተዋናይ ሊሆኑ ይገባል። ይህንን ማድረግ ስንችል ነው ከውጭ የሚመጣውን ማስቀረትና እዚሁ ሀገራችን ውስጥ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት ማምረት የምንችለው። ምቹ የተፈጥሮ ሀብት እያለን በሚፈለገው ልክ እየሠራን አይደለም፤ ግብዓቱ እዚሁ እያለ ወረቀት እንኳን ከውጭ ነው የምናስመጣው። ስለዚህ ሊሠሩ የሚችሉ ከአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ወደ መካከለኛ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ ማፋጠኑ ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ።

አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መጀመር ለኢንዱስትሪው ማበብ ምን ዓይነት ሚና እየተጫወተ ነው ብለው ያምናሉ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በጣም የሚደገፍና አንቺም እንዳልሽው ለዘርፍ ማበብ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ነው የሚገኘው። ብዙዎቹን ከሥር መሠረት ጀምሮ በማሳደግ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም እረዳለሁ። የተመረቱ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙና ትስስር እንዲፈጠርላቸው ከማድረግ አኳያ የሚበረታታ ሥራ እየተሠራ ነው ብዬ ነው የማስበው። ደግሞም እኛ እንደ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን የምናበረታታው ጉዳይ ነው። ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት ብንሠራ ደግሞ የበለጠ ልናግዝ እንችላለን። ምክንያቱም በርካታ የውጭ ተሞክሮዎችና ዘርፉን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሃሳቦች ያሉን በመሆኑ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ የትኞቹን ምርት ላይ ትኩረት ሰጥታ ብትሠራና ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፋ ወደ ውጭ መላክ የምትችልበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል። ሁሉንም ነገር ለመንግሥት ብቻ መጣል ሳይሆን አብሮ መሥራት ነው ሀገራችን የሚያሳድጋት፤ የግሉንም ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርገው። በዚህ ረገድ የመንግሥት ተቋማት በራቸውን ክፍት ሊያደርጉና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መነጋገርና አብሮ መሥራት ያስፈልጋል።

ከዚህ ባሻገር ግን በዘርፍ መሳተፍ ለሚሹ የፈጠራ ሰዎችን መንግሥት የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸውና ሊደግፋቸው ይገባል ብዬ አምናለሁ። አሁን ላይ በርካታ ወጣቶች በሮቦቲክ ኢንጂነሪንግና በተለያዩ ፈጠራዎች እየመጡ ነው ያሉት። ግን ደግሞ አሁን ያሉን ኢንዱስትሪዎች በዚያ ልክ በፈጠራ ሥራዎች እየተመሩ ነው ብዬ አላምንም።

በመሆኑም በተለይ አግሮ ኢንዱስትሪውን የሚደግፉ የፈጠራ ሥራዎች እንዲመጡ መንግሥት የፈጠራ ባለሙያዎችን ሊያበረታታና ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ይገባል ብዬ አምናለሁ። የግብርና እና የአግሮ ኢንዱስትሪው ትስስር በሚፈለገው እየተሳለጠ ስለመሆኑ በትክክል ማረጋገጥ ይገባል፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ብናውለው መንግሥትም ማታለል ነው የሚሆነው። በመሆኑም ከግብርናው ጀምሮ በኢንዱስትሪው ተመርቶ ሸማቹ ጋር እስከሚደርስ ያለው ሰንሰለት ጤናማ እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል። በጥቅሉ እንደ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪዎቻችን ማደግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው እናምናለን፤ የላቀ ውጤት እንዲመጣ ክፍተቶችን እያየን የበኩላችን እገዛ የምናደርግ ነው የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለይ ለአምራች ዘርፍ ላይ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ምን ዓይነት አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለው ያምናሉ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓ ለሁሉም ዘርፍ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ። መንግሥት ሪፎርሙን ለማካሄድ ያስገደደው ዋነኛ ምክንያት የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ብሎ እንደሆነ እረዳለሁ። በተጨማሪም በተለይ ሪፎርሙን ተከትሎ የመጣው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፈታት ያደረገው ጥረት ለዘርፍ ወሳኝ ሚና እንዳለው አምናለሁ። እግረ መንገድም ሕገወጦችን ለመከላከል ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ግልጽ ነው። በጥቅሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት አበርክቶው የላቀ ነው ማለት ይቻላል።

ሆኖም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ውይይት የምናደርግበት እድል ቢፈጠር መልካም ነበር። ማክሮ ኢኮኖሚ በደንብ ካልተመራ ይወድቃል። በየጊዜው እንደ ወቅቱ እየታየ የሚከለስ መሆን መቻል አለበት። ለዚህ ደግሞ ነፃ የሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት መከተል መቻል አለበት። ሁሉም ደረጃውን የጠበቀ ምርት ማምረት አለበት፤ ለዚያ የሚያመች የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይላል። አሁን ላይ ኢንዱስትሪዎች የባንክ ብድር በስፋት የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠር ይገባዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ባለሀብቱ በአግባቡ ኢንቨስት አድርጎ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊደግፍ በሚያስችል መልኩ እየተሳተፈ አይደለም።

በሌላ በኩል ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ ባንኮች ላይ ያለው አሠራር በተጨባጭ ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና ላላቸው ዘርፎች ትኩረት ሊያደርግ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። በተለይ በውጭ ጥገኝነት ለተመሠረተ ኢንቨስትመንትና የገቢ ንግድ ተዋናዮች ከመስጠት ይልቅ ተኪ ምርት አምራች ለሆኑ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ብድር እንደልብ የሚያገኙበትን ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል። አይደለም የሀገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ፋይናንስ ተቋማትም ብድር እንዲያገኙ መንግሥት ዋስትና ሊሰጥ ይገባል። እነ ኬንያና ሩዋንዳ ያደጉት መንግሥት ዋስትና ሊሰጥላቸው ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት ብትሆን በተለይ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምን ዓይነት ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?

ኢንጂነር ጌታሁን፡- ይሄ ጥያቄ በጣም ጥሩና ወቅታዊ ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ትልቁና ታሪካዊ ስህተት የሆነውን ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነቷን ያጣችበት ሁኔታ ማንሳት ይገባል። በመሠረቱ በኤርትራ መገንጠል ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅና አልሰጠም። ይልቁኑም ሻዕቢያና ሕወሓት አመራሮች ውሳኔ ነው ተፈፃሚ የሆነው። እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን ወረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ዓይን፣ ጆሮና እጅ አስረው ነው ኤርትራን የገነጠሉት። እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ድርሻ ኖሮት ሳለ፤ ታፍኖ ስለመብቱና በገዛ ሀብቱ ላይ እንዳይወስን ነው የተደረገው። መገንጠሉ አልበቃ ብሎ በድንበር ላይ የነበረብን ባለቤትነት እንዳናስከበር በአፈና የተፈፀመ ተግባር ነው።

ይህ ታሪካዊ ስህተት ከተፈፀመም በኋላ በሂደት የሁለቱን ሕዝቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው እንዲጠናከር አልተሠራም። ትልቅ ሃሳብ ትልቅ ሀገር ለመፍጠርም የነበሩት መንግሥታት ያደረጉት ጥረት አልነበረም። ከዚያ ይልቅም ሥልጣን ወዳዶች፣ እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይበቀል ባዮች የድሃውን ሕዝብ ሕይወት ያደናቀፈ ፖሊሲ ነው ተግባራዊ ያደረጉት። ግን ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ለመሥራትና ለማደግ አሁንም ድረስ ፍላጎት እንዳላቸው እናውቃለን። በሌላ በኩል ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለባቡር ትራንስፖርት ማሠሪያ ሀብት፤ ገንዘብ ሲያጡ ጅቡቲን ለ99 ዓመት በሊዝ አስያዙ እንጂ ጅቡቲ ሌላ ሀገር እንድትሆን አልወሰኑም። ይሁንና የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን መያዝ አቅቷቸውና በውጭ ተፅዕኖ ምክንያት ጅቡቲ እንድትገነጠልና ነፃ እንድትወጣ አደረጉ። በጥቅሉ በየዘመኑ የነበሩ መንግሥታት እስከ የመን ድረስ ግዛቷ የሰፋውን ኢትዮጵያ ዛሬ አሰንሰዋት ጭራሹኑ ወደብ አልባ እንድትሆን የተደረገበት ሁኔታ ለሁላችንም ልብ ሰባሪ ጉዳይ ነው።

አሁን ላይ መንግሥት እያደገ ካለው የሕዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚ አኳያ ሀገሪቱ ወደብ አልባ መሆን እያመጣባት ያለውን ጉዳት ተመልክቶ አጀንዳ አድርጎ የጀመረው ንቅናቄ የሚበረታታ ነው። ይህንን ጥያቄ ግን በዲፕሎማሲ አግባብ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማቅረብ ይገባዋል። ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተለይም ታሪካዊ ዳራዎችን በማንሳት ኢትዮጵያ ይህንን ያህል ሕዝብ ቁጥር ይዛ ወደብ አልባ መሆንዋ ያመጣባትን ችግር የዓለም ማኅበረሰብ እንዲያውቀውና እንዲረዳው ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህም ግን ሊሆን የሚገባው ከጦርነት መለስና በሰላማዊ መንገድ ነው።

ወደብ ባላቸው ሀገራት ተጽዕኖ ስር ስለሚወድቅ የባሕር በር የሌለው ሀገር አያድግም። በሞባሳ፣ በላሙ ወደብ፣ በሃርጌሳም ሆነ በጅቡቲ በኩል የምናገኘው የወደብ አገልግሎት የራስን ያህል ሊሆን አይችልም። ከዚያ ይልቅም ከኤርትራ ጋር ፍፁም በሆነ መግባባት የአሰብን ወደብ ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ማድረግ መቻል አለብን። ይህንን ደግሞ ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይቃወሙታል ብዬ አላምንም። በቋንቋ፣ በባሕል አንድ የሆኑን አብረን የተጋባንና የተዋለድን ሆነን ሳለ አሳልፈው ለሳውድ ዓረቢያ የሚሰጡ አይመስለኝም።

አሁን ላይ መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት መልካም ሆኖ ሳለ ጥያቄው ግን የሕዝብም ጭምር በመሆኑ ሕዝባዊ እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅበታል። በየትኛውም ዓለም ያለው ኢትዮጵያዊ፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሠሩ ማድረግ መቻል አለብን። በተለይ የውጭ መንግሥታትን የማሰመን ሥራ መሥራት አለባቸው። ጅቡቲ ላይ የተለያዩ ኃያላን ሀገራት የጦር ካምፖቸውን አስፍረዋል፤ ሆኖም የጅቡቲ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ኢትዮጵያ ናት። ጅቡቲ ላይ አንድ ቀን ኃያልን ሀገራቱ እርስ በርስ ቢጋጩ ወይም ሌላ ችግር ቢፈጠር የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ምርት ይቆማል ማለት ነው። ስለዚህ አማራጮችን መፈለግ መቻል አለብን። በሌላ በኩል ከውጭ የምናስመጣቸውን ምርቶች እዚሁ ሀገራችንን ውስጥ የማምረት አቅማችንን ማሳደግ አለብን።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ኢንጂነር ጌታሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You