“በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት የሽማግሌዎች ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል” -ኢንጅነር ጌታሁን

-ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን  የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ሕዝባዊ የምክክር ፎረም ሰብሳቢ

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት አንድ ጠንካራ የሽማግሌዎች ቡድን እንዲቋቋም መደረጉንና በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉንም ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማት እና የዲሞክራሲ ሕዝባዊ የምክክር ፎረም ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን አስታወቁ::

የፎረሙ ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ያለውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ያስችል ዘንዳ አንድ ጠንካራ የሽማግሌዎች ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል::

የሽማግሌዎች ቡድኑ ከየትኛውም ፖለቲካ ድርጅት ውግንና የሌለው ሲሆን የክልሉ ሕዝብ ለሰላሙ እውን መሆን በይቅርታና በመቻቻል ይበልጥ እንዲቀራረብ የማድረግ ሥራ ይሠራል ብለዋል::

ፎረሙ እንደሽማግሌም፤ እንደምሁርም ገልለተኛ በሆነ መንገድ፤ ሁሉንም አካላት በሚያግባባ መልኩ ለመሥራት መዘጋጀቱን የተናገሩት ኢንጅነር ጌታሁን፤ በዋናነትም ልዩነት ያላቸው አካላት በአንድ መድረክ ላይ በማምጣት እንዲግባቡ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል::

‹‹በማይግባቡበት ላይ ሽማግሌዎች ገብተው የሚዳኙበትን ሁኔታ የሚፈጥር ይሆናል፤ በተለይ መንግሥት ካገዘን በክልሉ ሰላም እንዲወርድ የቻልነውን ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅተናል›› ሲሉ ገልጸዋል::

በክልሉ ትክክለኛ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ ሁሉም አካል ከልብ በሆነ መልኩ ይቅር ለመባባል መዘጋጀት እንደሚገባው አመልክተው፤ ‹‹ይቅርታ የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ ነው፤ ይቅርታ መሸነፍ አይደለም:: እውቀት ነው፤ ልህቀት ነው:: ትልቅ ሀብትና ፀጋ ነው›› በማለትም ተናግረዋል:: በመሆኑም ከይቅርታ በኋላ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ተገቢ መሆኑም ገልፀዋል::

በዚህ ረገድ ፎረሙ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እንዲህ አይነቱ የሰላም እጦትና ግጭቶችን ለማስወገድ አራት ምክረ ሃሳቦችን መስጠቱን አስታውሰው፤ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ የሰው ሕይወት በየጊዜው እያለፈ፤ ሀብት፣ ቅርሳችን ገንዘባችን እየወደመ፤ የሀገር ገፅታ እየጠፋ መሆኑን ተገንዝበን ለይቅርታ ልባችንንና በራችንን ክፍት ልናደርግ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል::

ለዚህ ደግሞ በተለይ መንግሥት ትልቅ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ ወገኖቻችንን እንዲሁም ሳይገባ ልቡ ሸፍቶ የተቀመጠውን ሳይቀር በሀገር ጉዳይ ላይ የሚሳተፍበትን እድል ሊፈጥር እንደሚገባ አመልክተዋል::

በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እየተሠራ ካለው ሥራ ጎን ለጎን ነፃ የሆኑ ምሁራን ኃላፊነቱን ወስደው ማገዝ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል::

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You