ኮሪዶር ልማቱ ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎችን ከስጋት ነፃ ማድረግ ችሏል

አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ እየተከናወነ ባለው የኮሪዶር ልማት ሥራ ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ አካባቢዎችን ከአደጋ ስጋት ነፃ ማድረግ ተችሏል ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) ገለጹ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ የአደጋ ስጋት ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እና ከአደጋ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ በቂ መሠረተ ልማቶች ባለመኖራቸው በርካታ ሰዎች የአደጋ ተጋላጭና ጉዳት ሲደርስባቸው ቆይቷል።

ለአብነት በፒያሳና በካዛንቺስ አካባቢዎች በቂ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የጎርፍ ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነበር ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ በኮሪዶር ልማቱ የመንገድ፣ የመብራት እና የቴሌኮም መሠረተ ልማት ግንባታዎች የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባታቸው የአደጋ ስጋት ተጋላጭነት እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።

የተጠላለፉ የኤሌክትሪክ መስመሮችና የኤሌክትሪክ መስመሮችን የሚነኩ ዛፎች በብዛት መኖርም ሌላው የዜጎች የአደጋ ተጋላጭነት ደረጃን እንዲጨምር ያደረገ ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ በኮሪዶር ልማቱ ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችንም የአደጋ ተጋላጭነት ወደሌለባቸው አካባቢዎች የማዘዋወር ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

በኮሪዶር ልማቱ መልሶ ማልማት የተሠራባቸው አካባቢዎች የነበሩ ቤቶች የሰው ልጅን ክብር የማይመጥኑ እና ቤት ለመባል ራሱ ብቁ ያልነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህንን ሁኔታ በኮሪዶር ልማት ሥራው በመቀየር ታሪክ መሥራት መቻሉን ገልጸዋል።

እሳቸው እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ ከሶስት ዓመት በፊት ውብና ምቹ መሠረተ ልማት አልነበራትም። ኮሪዶር ልማቱ ባመጣው እሳቤ በከተማዋ መሠረተ ልማትን ማሟላት ብቻ ሳይሆን በአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠት የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ ተሠርቷል። በዚህም የአደጋ ተጋላጭነት ደረጃን መቀነስ ተችሏል።

በተለይ በወንዝ ዳርቻ ልማት በተከናወነው ተግባር በአብዛኛው ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ቦታዎችን ከአደጋ ስጋት ነፃ ማድረግ ተችሏል። አስቀድሞ ወንዞች ቆሻሻ የሚጣሉባቸው ሥፍራዎች ነበሩ። በዚህ ምክንያት በቂ ጎርፍ መሸከም ባለመቻላቸው የየአካባቢውን ነዋሪዎች ለጎርፍ፣ ለመሬት መንሸራተት፣ ለቤት መደርመስ አደጋ እንዲጋለጥ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

የመኪና መንገዶች ስፋት ጠባብ መሆን በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ፤ የአብዛኛዎቹ መንገዶች አንደኛው መስመር አሽከርካሪዎች መኪናዎቻቸውን ያቆሙባቸው ስለነበር የትራፊክ መጨናነቅ እንዲፈጠር ሲያደርግ ኖሯል ብለዋል።

በዚህም የአደጋ ምላሽ ሰጪ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት አደጋው የደረሰበት ቦታ እንዳይደርሱ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። ይህን ችግር የኮሪዶር ልማቱ መፍታቱን ጠቅሰው፤ በኮሪዶር ልማቱ የተገነቡ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የታክሲ ማቆሚያና ማውረጃ ቦታዎች የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት በማሳለጥ ከዚህ በፊት የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ የቀነሱና ለአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ አብዛኛዎቹ የከተማዋ የውሃ መሠረተ ልማቶች ከተገነቡ የቆዩና በቂ የውሃ መጠን የሚሸከሙ አልነበሩም። በዚህም የተነሳ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሰጪ ተሽከርካሪዎች ውሃ ሊቀዱ ሄደው ታንከሮቻቸውን ለመሙላት ረጅም ሰዓት የሚጠብቁባቸው ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ መሠረተ ልማቶች በኮሪዶር ልማቱ ተቀይረዋል።

የእሳት አደጋ መኪኖች ታንከሮቻቸውን ውሃ የሚሞሉባቸው ቦታዎች ሩቅ ነበሩ። በኮሪዶር ልማቱ እነዚህ መሠረተ ልማቶች በየግማሽ ኪሎ ሜትሩ እንዲኖሩ ማድረግ ተችሏል። ይህም የአደጋ ጊዜ ምላሽ አቅምን ያሳደገ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው በሁሉም የኮሪዶር ልማት በተካሄደባቸው ቦታዎች የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች መዘርጋት የሚቻልባቸው ሁኔታዎችንም መፍጠር ተችሏል። ይህም በአደጋ ጊዜ ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ለማሳለጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You