
አዲስ አበባ፡– ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር የግብርና ሥርዓት ለመገንባት የዲጂታል መረጃን ከዘርፉ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር የማስተሳሰር ሥራዎች ውጤት እያሳዩ መሆኑን የግብርና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ እንደ ሀገር የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ የዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ለመፍጠርና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር የግብርና ሥርዓትና አቅም ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሠራ ነው። በተለይም በዘላቂነት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎች እንደ ሀገር ካስገኙት ውጤት ባሻገር ሌሎች ሀገራት ምሳሌ በመሆን ላይ ናቸው፡፡
እንደ ሀገር የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቋቋም ከሚደረጉ ጥረቶች ባሻገር አስቀድሞ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራትና አማራጮችን እየተቃኙ ስለመሆኑ ያስገነዘቡት አቶ ኢሳያስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል አቅም መገንባት በሚከናወኑ ተግባራት መረጃን ከግብርና ዘርፍ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር የማስተሳሰርና በተለይም የዲጂታል መረጃ ሥርዓት ወሳኝ አቅም ለመጠቀም እየተሠራ ነውም›› ብለዋል፡፡
ሀገራዊው የዲጂታል ስትራቲጂም ቴክኖሎጂን ከግብርናው ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር ረገድ ለውጥ መታየት መጀመራቸውን ያመላከቱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፣ ለአብነትም የገጠር መሬት ምዝገባ ሥርዓት አርሶ አደሩን ከእንግልት ያዳነና ተጠቃሚነቱን እንዲያጎለብት ያስቻለ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
መረጃን ከግብርና ዘርፍ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር በማስተሳሰር ሂደት ከኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት የሚሠሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው የጠቆሙት አቶ ኢሳያስ፣ ይሁንና ሁሉንም አርሶ አደሩ ጋር ከመድረስ በተለይም መረጃዎችን በፍጥነት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተዘረጉ ሥርዓቶች በቂ የሚባሉ እንዳልሆኑና ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ገልፀዋል፡፡
ከአየር ሁኔታ ትንበያ ጋር የተገናኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ተጽእኖውን መቋቋም የሚችሉበት አቅም ለመገንባት በተለይም ልምድና እውቀቱ ካላቸው የተለያዩ ሀገራትን ዓለም አህጉራዊ የትብብር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ኢሳያስ፣ ለአብነትም ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ጋር በዘርፉ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና እውቀቶችን ለመለዋወጥ የሚያስችል DIGITAL AGRO-CLIMATE ADVISORY SERVICES (DACAS) KNOWLEDGE NETWORK የተሰኘ የዲጂታል መረጃ ሥርዓት ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
ይህ የዲጂታል የመረጃ ሥርዓትም፣ ከአየር ሁኔታ ትንበያ ጋር የተገናኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እድል የሚፈጥርና በተለይ የአየር ጠባይን መሠረት ያደረጉ ትንበያዎችን ምክረ ሃሳቦችን በሚመለከት ሀገራት እርስ በእርስ ልምድ የሚለዋወጡበትና የጋራ ግንዛቤ የሚፈጥሩበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር የግብርና ሥርዓት ለመገንባት የዲጂታል መረጃን ከዘርፍ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር ለማስተሳሰር በሚከናወኑ ተግባራት እውቀቱ፣ ልምዱና ቴክኖሎጂው አለን የሚሉ ባለሙያና ባለድርሻ አካላትን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም