
ጥሎብኝ ኩነት events እወዳለሁ።በተለይ የእንግሊዝ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ክዋኔ፤አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲመረጥ ባኪንግሀም ቤተመንግሥት ሄዶ ከንጉሱ ዘንድ አዲስ መንግሥት እንዲመሰርት ይሁንታ የሚያገኝበት፤ እሱም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኦፊሴላዊ መኖሪያና ቢሮ ወይም ዳውኒግ ስትሪት ናምበር 10 ፊት ለፊት ቆሞ ንግግር ሲያደርግ፤ አዳዲስ የካቢኔ አባላቱ የጋዜጠኞችን መንጋ የእጅ ሰላምታ እየሰጡ ወደ ናምበር 10 ሲያልፉ፤ በአለማችን ቀደምት የሆነው የእንግሊዝ ፓርላማ የስብሰባ ክዋኔን ፈዝዤ ነው ማየው።
ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ተመራጭ አባላትና የተቃዋሚ ፓርቲው ተመራጮች ፊት ለፊት በአረንጓዴ ሌዘር በተለበጠ አግዳሚ ቁጭ ይላሉ። በመሐላቸው የአንደ ሻምላ ያህል ርዝመት ያለው ርቀት አላቸው። አቤት ሙግታቸው ደስ ሲለኝ። ሌላው አፍ የሚያስከፍተው ሁነት የዩናይትድ ኪንግ ደም ንጉሳዊ ስርዓት የተለያየ ኩነት ነው። ባለፈው ንግስቷ ሲሞት የተገለጸበት፣ የአስከሬን ስንብት የተደረገበት፣ የቀብር ስነ ስርዓቱ፤ ልጇ በእሷ እግር ንጉስ ሆኖ የተቀባበት ስርአት፤ ልዑላን ልጅ ሲወልዱ ለሕዝብ የሚያበስሩበት ስርዓት በየጊዜው እንደ አዲስ ባየው ባየው አይሰለችኝም።
አንዳንድ ጊዜ ጊዜ ሸነጥ ሲያደርገኝ የሰለሞናዊው ንጉሳዊ ስርዓት ሰርሞኒያል ወይም ፓለቲካዊ ስልጣን ሳይኖረው ወደ ዙፋኑ ቢመለስ ሁሉ ብዬ አስቤ አውቃለሁ። ቢመለስ አንድ ያደርገን ይሆን ብየ ራሴን እጠይቃለሁ። ለሀገራችን ገጽታና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው አስተዋጾኦ ይኖረው ብየም እጠይቃለሁ። ወደ ነገረ ኩነት ስመለስ የአፍሪካ ዋንጫ፣ የአለም ዋንጫ፣ የኦሎምፒክ፣ ወዘተረፈ መክፈቻና መዝጊያ ዝግጅቶችን በተመስጦ ነው የምመለከታቸው።ሰሞነኛው የሮማ ርዕሳነ ሊቃ ጳጳሳት ፍራንሲስ ሞት መርዶና ፍታት የተደረገበት፣ የአስከሬን ስንብት የተከናወነበት፤ እሳቸውን የተኳቸው ፓፕ የተመረጡት ሚስጥራዊ ምርጫን ወይም ኮንክሌቭ በደንብ ነው የተከታተልሁት።
መቼስ የቀደሙ 265 ርዕሳነ ሊቃ ጳጳሳት ታሪክ መለስ ብለን ብንቃኝ የፍራንሲስን ያህል ያለ ሀይማኖት፣ ያለ ርዕዮተ አለም፣ ያለ መደብ፣ ያለ የቆዳ ቀለምና ያለ የጾታ ልዩነት ከጋዛ እስከ ጁባ፤ ከቫቲካን እስከ ዋሽንግተን፤ ከካራካስ እስከ ፓሪስ በአለማችን የተወደሰ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የለም። በሰሞነኛው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ሳይቀር ከአፍ እስከ ገደፋቸው በሞሉት የኤምሬትስና የካምፕ ኑ ስታዲየሞች የሰላምና የፍትሕ ጳጳስ ተብለው ታስበዋል።
አሁን ፍታቱም ቀብሩም ተጠናቋል። ጥያቄው ፍራንሲስን ወይም ፍራንችስኮስ ማን ይተካቸዋል።በጭስ አይነት የሚለየው ይህ እጅግ ሚስጥራዊ የሆነው ምርጫ ወይም ኮንክሌቭ እንዴት ይካሄዳል።
አድማጭ ተመልካቹን በተለይ 1 ነጥብ 4 ካቶሊካውያንን በስሜት በጉጉት ሰቅዘው ከሚይዙ ሁነቶች ቀዳሚው ለክፍለ ዘመናት የቀጠለው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሳነ ሊቀ ጳጳሳት ሚስጥራዊ የምርጫ ሂደት ወይም ኮንክሌቭ ነው።
በትንሳኤው ማግስት ከዚህ አለም ድካም ያረፉት ርዕሳነ ሊቀ ጳጳሳት ፍራንሲስ ወይም ፍራንችስኮስ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ኢትዮጵያዊት አስለቃሽ ብትገኝ፦
“ጾም ስግደቱ ሲቆም ጸሎቱም ሲረሳ፣
እኛ መሞት ጀመርን አንተ ስትነሳ፤”
ብላ ስንኝ መቋጠሯ አይቀርም ነበር።
የካቶሊካዊቷ ቤተ ክርስቲያን 266ኛው ርዕሳነ ሊቀ ጳጳሳት ፓፕ ፍራሲስ በትንሳኤ ማግስት በ88 አመታቸው ከዚህ አለም ድካም ማረፋቸው ይታወሳል።ቀብራቸውም ከመላው አለም ወደ ጣሊያን ሮም ቫቲካን በጎረፉ ከ250ሺህ በላይ ምዕመንና የሌላ ዕምነት ተከታዮች፤ከ50 በላይ የሀገራት መሪዎች፤የ145 ሀገራት ልዑካን እና 10 ነገስታት፣ንግስታትና ልዑላን በተገኙበት የቀብር ስርዓታቸው ተፈጽሟል።
ይህ አለማቀፍ የቀብር ስነ ስርዓት ባልተለመደ ሁኔታ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ዜለንስኪንና የአሜሪካውን አቻቸውን ትራምፕን ፊት ለፊት አገናኝቶ በማወያየት በታሪካ ሲወሳ ይኖራል። ይሄን በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ደጀ ሰላም የተካሄደ ክስተት የሚገልጸው የመሪዎቹ ፎቶ በማህበራዊም ሆነ በመደበኛው ሚዲያ ሲዘዋወር ብዙዎቹ ተቀባብለውታል። በነገራችን ላይ ከላቲን አሜሪካ የመጡ የመጀመሪያው ጳጳስ፣ የመጀመሪያው የየሱሳውያን ጳጳስ እና ከ1200 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው አውሮፓዊ ያልሆኑ ጳጳስ ነበሩ።
ጳጳሱ ከሞቱ ወይም ከስንት አንድ በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ አለማችን በጥፍሩ ቆሞ በጉጉት የሚጠብቀው የአዲሱን ጳጳስ የምርጫ ስነ ስርዓት ነው። በዚህ የምርጫ ሂደትና ሽኩቻ ዙሪያ በታዋቂው ደራሲ ሮበርት ሀሪስ ተጽፎ ለአንባቢዎች የደረሰው “ኮንክሌቭ” የተሰኘው ረጅም ልቦለድ ወደ ፊልም ተቀይሮ በኔትፍሊክስ እየታየ ይገኛል ይለናል። ለመሆኑ ይህ ልዩ የምርጫ ስርዓት እንዴት ያለ ነው።
የአዲሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ በሮም በሚገኙት ብጹዓን ካርዲናሎች አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን ከዚያ በፊት ካርዲናሎቹ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በኋላ ለዘጠኝ ቀናት በሚቆይ ጠቅላላ ስብሰባ፣ አስተንትኖ እና በየዕለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ እንደሚገኙ ቫቲካን ኒውስ ታውቋል።
ብጹዓን ካርዲናሎቹ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነፍስ በእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ ዕረፍት ታገኝ ዘንድ ለዘጠኝ ቀናት ጸሎት ሲያቀርቡ ከቆዩ በኋላ ከሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ጀምሮ አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ ዝግ ጉባኤ ወይም ኮንክሌቭ ጀመሩ።
በሮም የሚገኙት ካርዲናሎች ሰኞ ሚያዝያ 20/2017
ዓ. ም. ማለዳ ላይ በቫቲካን ባካሄዱት አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸው ከተሰበሰቡት 180 ካርዲናሎች መካከል አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ የበቁ ከ 100 በላይ ካርዲናሎች እንደሚሆኑ ወስነዋል። ስብሰባው የሚካሄደው በቫቲካን በሚገኝ የሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ሲሆን፥ በምርጫ ቀናት ጸሎት ቤቱ ለጎብኚዎች ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል። ከጉባኤው ቀደም ብሎ መራጭ ካርዲናሎች በኅብረት ሆነው የምርጫ መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴን የሚያሳርጉ ሲሆን፥ ከሰዓት በኋላ ዝግ ጉባኤን ለማካሄድ ወደ ሲስቲን ጸሎት ቤት እንደሚያመሩ የምርጫ መርሃ ግብር ያመለክታል።
ባለፈው ሀሙስ የቀን ቅዱስ ሌዮ 14ኛ፥ አዲሱ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተሰይመዋል። የካርዲናሎች ጉባኤ ሮበርት ፍራንሲስ ፕሬቮስትን 267ኛው የሮም ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጎ መርጧቸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ታዳሚዎች ይህን ያበሰሩት የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ ዲያቆን ብጹዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ ናቸው።
አዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በቅድሚያ፥ “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!” በማለት በአደባባዩ ለተገኘው በርካታ ቁጥር ላለው ሕዝብ ሰላምታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ የካርዲናሎች ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀ ዲያቆን ብጹዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ ቀደም ብሎ ባሰሙት ንግግር፥ “ደስታን እነግራችኋለሁ”፣ “ጳጳስ አለን!” በማለት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መመረጥ በማብሰር፥ “እጅግ የተከበሩ የሮም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ካርዲናል ሮበርት ፍራንሲስ ፕሪቮስት፥ ሌዮ 14ኛ የሚል አዲስ ስም ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ሊቀ ዲያቆን ብጹዕ ካርዲናል ዶሚኒክ ማምበርቲ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማዕከላዊ ሰገነት በኩል ቆመው ባሰሙት አጭር ንግግር፥ “ሃቤሙስ ፓፓም” ውይም “ጳጳስ አለን” በማለት ለሮም ከተማ ነዋሪዎች እና ለመላው ዓለም ሕዝብ ካርዲናል ሮበርት ፍራንሲስ ካርዲናል ፕርቮስት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ተብለው መመረጣቸውን አብስረዋል።
በአሜሪካ ቺካጎ ተወልደው ያደጉት የ69 ዓመቱ ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት፣ፖፕ ወይም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተብለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመረጡ። ካርዲናል ፕሪቮስት በፔሩ ጳጳስ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በሚሺነሪነት አገልግለዋል።ሊቃነ ጳጳሱ ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ጣሊያንኛ እና ስፓኒሽኛ የሚናገሩ ሲሆን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎታቸው እንዲሁም አዳማጭነታቸው ይጠቀሳሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት እአአ በ2023 ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የቫቲካን የጳጳሳት አለቃ አድርገው በመሾም ቀጣዩን የጳጳሳት ትውልድ በመምረጥ ውስጥ ቁልፍ ሥልጣን እንዲኖራቸው አድርገዋል።
ካርዲናል ፕሮቮስት ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ ተብለው ለመጠራት መወሰናቸው ተገልጿል።
ለሁለት ቀናት አዲሱን ሊቀጳጳስ ለመምረጥ የተሰባሰቡት የቤተ ክርስቲያኗ ካርዲናሎች ከተሰበስቡብት ቤተ መቅደስ አናት ላይ አዲስ ሊቀ ጳጳስ መመረጡን የሚያሳየው ነጭ ጭስ የታየው ሀሙስ ከስዓት ነበር። አሜሪካዊው ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን አዲሱን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ ለሁለተኛ ቀን የተሰባሰቡት ካርዲናሎች በምሥጢር ድምጻቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ነው አዲስ ሊቀ ጳጳስ መሆናቸው ይፋ የተደረገው። ድምጽ መስጠት ከሚችሉት 133 ካርዲናሎች መካከል የ89ኙን ይሁንታ ያገኙት ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በረንዳ ላይ ብቅ በማለት ለሕዝብ ታይተዋል። በወጉና በስርዓቱ መሠረት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰባሰቡ የእምነቱ ተከታዮች ሊቀ ጳጳሱን ሲመለከቱ ደስታቸውን በጩኸት እና በእንባ ገልጸዋል። ዕድሜያቸው እስከ 80 ዓመት የሚሆን 133 ካርዲናሎች ቀጣዩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ማን ሊሆን እንደሚገባ ከተወያዩ በኋላ ይሆናሉ ያሏቸውን ነው ባለፈው ሀሙስ የመረጡት።
አዲሱ የሮማ ካቶሊክ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጣሊያንኛ እና በስፓኒሽኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ንግግራቸውን ሲያደርጉ፤”ይህ ሰላም የሞላበት ሰላምታዬ ለሁላችሁም ልብ እና ቤተሰብ እንዲሁም በዓለም ላሉ ሕዝቦች እንዲደርስ ይሁን” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆነው ሕዝብ ባደረጉት ንግግር “እግዚአብሔር ሁላችንንም ይወደናል፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ” ብለዋል። በማከልም “ሰብዓዊነት በእግዚአብሔር እና በፍቅሩ የሚደረስበት ድልድይ ክርስቶስን ይፈልጋል። አግዙን፤ እርስ በርሳችሁም ተረዳዱ። ድልድይ እንገንባ” ብለዋል።
በንግግራቸው በሞት የተለዩትን ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ያስታወሱት ተተኪያቸው ለሕዝቡ እርሳቸው እንዳደረጉት ምዕመናኑን መባረክ እንደሚፈልጉ ተናግረው ቡራኬ ሰጥተዋል። ድምጻቸውን የሰጧቸውን ካርዲናሎች ያመሰገኑት ሊቀ ጳጳስ ሊዮ 14ኛ “እግዚአብሔር ወዳዘጋጀልን ቤታችን ሁላችንም በጋራ እንጓዛለን” ካሉ በኋላ “ለሮማ ቤተክርስቲያን ልዩ ሰላምታ ይድረስ” ብለዋል።
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት የእምነቱ ተከታዮች አንድነት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሊቀ ጳጳሱ ሁሉም በጸሎት እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል።
ለመሆኑ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ እንዴት ይካሄዳል ? የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ካርዲናሎች ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ ዝግ ጉባኤ ማድረግ ጀመሩ። በምርጫው ከፍተኛ ድምጽ የሚያገኙት ካርዲናል ቤተ ክርስቲያኒቱን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትነት ይመሯታል። የመራጭ ካርዲናሎች የድምጽ መስጫ ካርዱ በብረት ምድጃ ውስጥ እንዲቃጠል ከተደረገበት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1939 ዓ. ም. ጀምሮ በሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ የሚከናወነውን የአዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከተለው እናስቃኛችኋለን።
“Eligo in Summum Pontificem” ወይም “እንደ ጠቅላይ ጳጳስ ሆኜ እመርጣለሁ” የሚለው ጽሑፍ 133 መራጭ ካርዲናሎች 267ኛውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ በሚጠቀሙባቸው እያንዳንዱ የድምፅ መስጫ ካርድ ላይ የታተሙ ቃላት ናቸው። የድምጽ መስጫው ካርድ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሲሆን የላይኛው ግማሽ የላቲን ጽሑፍ ያለው ሲሆን ከታች በስተግራ በኩል ያለው ግማሽ ክፍት ቦታ መራጭ ካርዲናል የመረጧቸውን እጩ ስም የሚጽፉበት ነው። “መላው የእግዚአብሔር መንጋ” በሚለው ሐዋርያዊ ሕግ ዝርዝር ውስጥ እንደተደነገገው፥ የድምጽ መስጫ ካርዱ ለሁለት እንዲታጠፍ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።
የድምጽ መስጫ ካርድ እደላ፦
እያንዳንዱ መራጭ ካርዲናል ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት የምርጫ ካርዶችን ይቀበላል። ካርዶቹ በሥነ-ሥርዓቱ አስተባባሪዎች እንዲታደሉ ይደረጋል። ከዚያም ከፍተኛው ካርዲናል ዲያቆን የምርጫ ድምጾችን የሚቆጥሩ እና የሚመረምሩ ሦስት አባላትን፣ በድምጽ መስጫው ወቅት ሕመም ቢያጋጥማቸው ድምጾቻቸውን የሚሰበስቡ ሦስት የጤና ባለሞያዎችን፣ የድምጽ ቆጠራውን ትክክለኛነት በመገምገም የሚያረጋግጡ ሌሎች ሦስት አባላትን ይሰይማል። ከተሰየሙት መካከል አንዳቸውም በሕመም ወይም በሌሎች ምክንያቶች ሚናቸውን መወጣት ካልቻሉ በምትካቸው አዲስ ስሞች ይዘጋጃሉ። ይህ ደረጃ የምርጫ ቅድመ ምርመራ በመባል ይታወቃል።
ድምጽ መስጠት ከመጀመሩ በፊት ሁሉም መራጮች፥ የካርዲናሎች ኅብረት ዋና ጸሐፊን፣ የጳጳሳዊ ሥርዓተ አምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ እና የሥነ-ሥርዓቱ አስከባሪዎችን ጨምሮ ሁሉም ከሲስቲን ጸሎት ቤት ለቅቀው ይወጣሉ። እነርሱ ከወጡ በኋላ ከፍተኛ ካርዲናል ዲያቆን የጸሎት ቤቱን በሮች ይዘጋዋል። እንደ አስፈላጊነቱ የታማሚ ካርዲናሎች ድምጽ ለመሰብሰብ ሲሄዱ እና ሲመለሱ ይከፍታቸዋል፣ ይዘጋቸዋልም።
እያንዳንዱ ካርዲናል በቅደም ተከተሉ መሠረት የመረጡትን እጩ ስም በድምጽ መስጫው ካርድ ላይ በመጻፍ እና በማጠፍ፥ ካርዱ እንዲታይ ከፍ በማድረግ ወደ መንበረ ታቦት ይወስድና በዚያም ክዳን ባለው ጽዋ ውስጥ ያስገባል። እያንዳንዱ መራጭ ካርዲናል በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈውን ጮክ አድርጎ ያነበዋል። ትርጉሙም የሚከተለው ነው፥ “ፈራጄ እና ምስክሬ የሚሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እጠራለሁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመረጥ ብዬ ላመንኩት ጳጳስ የምርጫ ድምፄን እሰጣለሁ” ካለ በኋላ የምርጫ ካርዱን ጽዋው ውስጥ አስገብቶ በመንበረ ታቦት ፊት ከሰገደ በኋላ ወደ መቀመጫው ይመለሳል።
ምርጫውን የተሳተፉ ነገር ግን በሕመም ምክንያት ወደ መንበረ ታቦት ድረስ መምጣት ያልቻሉ ካርዲናሎች የታጠፈውን የድምጽ መስጫ ካርድ ለአንደኛው መርማሪ ይሰጣሉ። እርሱም ወደ መንበረ ታቦት አምጥቶ ካስቀመጠው በኋላ በተመሳሳይ መንገድ ቃለ መሐላን ያቀርባል። አዎ ሕመም የሚሰማቸው ካርዲናሎች ከክፍላቸው ሆነው ድምጽ ይሰጣሉ።
ካርዲናሎች በሕመም ምክንያት በጸሎት ቤቱ ውስጥ መገኘት ካልቻሉ የእነዚህን ካርዲናሎች ድምጽ የሚሰበስቡ ሦስት የጤና ባለሞያዎች፥ በውስጡ የምርጫ ካርድ እንደሌለበት አስቀድሞ የተረጋገጠውን እና በቁልፍ የታሸገውን ሳጥን ይዘው ወደሚገኙበት ክፍል ይሄዳሉ። የሳጥኑ የላይኛው ክፍል የታጠፈ የድምፅ መስጫ ካርድ የሚገባበት ቀዳዳ አለው። ድምጾች ከተሰጡ በኋላ የጤና ባለሞያዎቹ ሳጥኑን ወደጸሎት ቤቱ መልሰው በመራጮች ፊት ከፍተው የምርጫ ድምጽ ካርዶችን ከቆጠሯቸው በኋላ በዋናው ድምጽ መሰብሰቢያ ውስጥ ያስገቧቸዋል።
ሁሉም የምርጫ ድምጾች ከተሰበሰቡ በኋላ የመጀመሪያው መርማሪ በድምጽ መስጫ ሳጥኖች ውስጥ የሚገኙ ካርዶችን ለመደባለቅ ሳጥኑን ያናውጣል። ከዚያም የመጨረሻው መርማሪ አንድ በአንድ ከቆጠራቸው በኋላ ወደ ሁለተኛው ባዶ ጽዋ ውስጥ ያስተላልፋል። የድምጽ መስጫዎቹ ቁጥር ከመራጮች ቁጥር ጋር የማይዛመድ ከሆነ ሁሉም የድምፅ መስጫዎች ከተቃጠሉ በኋላ አዲስ ድምጽ የመስጠት ሂደት ይካሄዳል። ቆጠራው ትክክል ከሆነ ጽዋዎቹ ተከፍተው የምርጫ ድምጽ ካርዶች ይነበባሉ።
ነገሩ እንዲህ ነው ሦስቱም የድምጽ መስጫ ካርድ መርማሪዎች በመንበረ ታቦት ፊት ባለው ወንበር ይቀመጣሉ። የመጀመሪያው በድምጽ መስጫው ካርድ ላይ የተጻፈውን ስም ካነበበ በኋላ ለሁለተኛው ያስተላልፋል። እሱም ስሙን አረጋግጦ ለሦስተኛው ያስረክባል። ሁሉ ሰው እንዲሰማው ጮክ ብሎ ካነበበው በኋላ እንዲመዘገብ ያደርጋል። ሁለት ድምጽ መስጫ ካርዶች በአንድ ሰው የተፃፉ እና ተመሳሳይ ስም ካላቸው እንደ አንድ ድምጽ ይቆጠራል። ምንም እንኳን አጠቃላይ ድምጹ ትክክለኛ ቢሆንም ነገር ግን የተለያዩ ስሞችን የሚያሳዩ ከሆነ ሁለቱም ውድቅ ይደረጋሉ።
ሁሉም የድምፅ መስጫ ካርዶች ከተነበቡ እና ከተሰበሰቡ በኋላ የመጨረሻው መርማሪ እያንዳንዱን ድምጽ “መርጫለሁ” የሚል ቃል በተጻፈበት መርፌ ወግቶት በሲባጎ ያስራቸዋል። የሲባጎው ጫፎች ተቋጥረው የድምጽ መስጫ ካርዶቹ ደህንነታቸው በተጠበቀ ሥፍራ ይከማቻሉ።በነገራችን ላይ አዲስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ የሁለት ሦስተኛው አብላጫ ድምፅ ያስፈልጋል። ባለፈው ረቡዕ ሚያዝያ 29/2017 ዓ. ም. በተጀመረ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ከተሳተፉ 133 መራጭ ካርዲናሎች መካከል ተመራጩን ለመለየት ቢያንስ 89 ድምጾች ያስፈልጋሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዕለቱ ይመረጡ ወይም አይመረጡ የምርጫ ገምጋሚዎቹ የድምጽ ቆጠራውን ሂደት በጥንቃቄ በመከታተል ሁሉም በትክክል መከናወኑን ለማረጋገጥ በተቆጣጣሪዎቹ የተሠሩ ማስታወሻዎችን ይመለከታሉ። ከዚህ በኋላ መራጭ ካርዲናሎች ከሲስቲን ጸሎት ቤት ከመውጣታቸው በፊት ሁሉም የድምፅ መስጫ ካርዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1939 ዓ. ም. ጥቅም ላይ መዋል በጀመረው የብረት ምድጃ ውስጥ እንዲቃጠሉ ይደረጋል። መርማሪዎቹ ይህንን የሚያከናውኑት በከፍተኛ ዲያቆን ካርዲናል በተሰየሙት በካርዲናሎች ኅብረት ዋና ጸሐፊ እና በሥነ-ሥርዓት አስፈጻሚ አባላት እገዛ ነው።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2005 ዓ. ም. የተገጠመው ሁለተኛ ምድጃ ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚታይ የጭስ ማውጫ ጋር የተገናኘ ነው። ለጭሱ የሚፈለገው ማለትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያልተመረጡ ከሆነ ጥቁር ጭስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተመረጡ ከሆነ ነጭ ጭስ እንዲወጣ ለማድረግ ኬሚካሎች ይጨመሩበታል። ሁለት ተከታታይ ድምጽ መስጫ ሂደቶች የተካሄዱ እንደሆነ ሁለቱም የምርጫ ድምጾች በሁለተኛው ዙር መጨረሻ አንድ ላይ እንዲቃጠሉ ይደረጋል።
ድምጽ የመስጠት ሥነ-ሥርዓት በቀን አራት ጊዜ ማለትም ጠዋት ሁለት ጊዜ ከሰዓት በኋላ ሁለት ጊዜ ይካሄዳል። ከሦስት ቀናት በኋላ እጩ ካልተመረጠ፣ ድምጽ የመስጠቱ ሥነ-ሥርዓት ከፍተኛ ካርዲናል ዲያቆን ከሚመሩት አጭር መንፈሳዊ ምክር እና ጸሎት ጋር መደበኛ ባልሆኑ ውይይቶች ለአንድ ቀን እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ እንደገና ይጀምራል። በየሰባት ተጨማሪ ዙሮች ያለ ስኬት ከቀረ በቅድሚያ በሊቀ ካርዲናል ቄስ፣ በኋላም አስፈላጊ ከሆነ በሊቀ ካርዲናል ጳጳስ መሪነት በጸሎት የማሰላሰል እና የዕረፍት ጊዜ ይመደባል።
ከ21 ዙር ድምጽ መስጠት በኋላ አሁንም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ካልተመረጡ ለጸሎት፣ ለውይይት እና ለአስተንትኖ የመጨረሻ ጊዜ ይመደባል። ነገር ግን በዚህ ጊዜ ካርዲናሎቹ ባለፈው ዙር ብዙ ድምጽ ካገኙ ሁለት እጩዎች መካከል አንዱን ሊመርጡ ይችላሉ። በዚህም ጊዜ የሁለት ሦስተኛ ድምጽ ያስፈልጋል። ብዙ ድምጽ ያገኙ ሁለቱ እጩዎች ድምጽ እንዲሰጡ አይፈቀድላቸውም።
ሻሎም !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም