ውድድሩ የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑ የታየበት ነው

አዲስ አበባ:- አራተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድሩ የሀገራችን ተስፋ ብሩህ ብልፅግናዋም አይቀሬ መሆኑ የታየበት ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ገለፁ።

በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አራተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ማጠቃለያ መርሃ ግብር ትናንት ሲካሄድ እንዳሉት፣ የክህሎት ልማትና የፈጠራ ሥራ ምርታማነትን፣ ተወዳዳሪነትና ሁለንተናዊ እድገትን ለማስመዝገብ ጉልህ ሚና አለው፡፡ የፈጠራ ሥራ አቅምን ማሳደግ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያመጣ፤ ችግሮችን የሚፈታ፣ የማህብረሰብ ኑሮን የሚያሻሽል ነው ብለዋል።

በውድድሩም ላይ የታዩት የቴክኖሎጂ ውጤቶች የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚያሳዩና ብልፅግናዋም አይቀሬ መሆኑን የጠቆሙ ናቸው ያሉት አቶ አደም፤ ለዚህም ሁሉም የፈጠራ ሥራ ባለሙያዎች ለጥረታቸው እና ለቁርጠኝነታቸው ምስጋና እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አደም ፋራህ ገለጻ፤ የክህሎት ልማት ላይ በትኩረት መሥራት ዘለቄታዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ይረዳል፤ ፈጠራን ያሳድጋል፡፡ በተጨማሪም ሥራ አጥነትን ይቀንሳል፡፡

በመንግሥት በኩል የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ለማስፋፋት፤ ጥራት ያለው ሥልጠና እንዲሰጡም ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተው፤ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የኢንዱስትሪውን ገበያ የሚያሟሉ ዜጎችን የማፍራት ሥራ እየተሠራ ነው፤ የተጠናቀቀው የክህሎት ውድድርም የፈጠራ አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ያለውን ሥራ የሚያሳይ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

 

የክህሎት ልማትና የፈጠራ ሥራን ለማሳደግ ውድድሮችን ከታች ጀምሮ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የፈጠራ ሥራዎችን ይበልጥ በማሳደግ የታለመውን ሁለተናዊ ብልፅግና ለማሳካት በቁርጠኝነት እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። የክህሎት ልማትና የፈጠራ ሥራ ለማሳደግ የዘርፉ ተዋንያንና የፈጠራ ባለቤቶች በትኩረትና በትስስር መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የክህሎት ውድድሩ ማህበረሰቡ በሙያ እና ክህሎት ትምህርቶች ላይ ያለውን ግንዛቤ የሚያሳድግ ወጣቶችን ለሥልጠና የሚያነሳሳ፤ እየተሠሩ ያሉት የፈጠራ ሥራዎችን ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል የሚረዳ እንደሆነ ጠቁመው፤ ውድድሩ ወጣቶች ላይ አወንታዊ ተጽእኖ ለማሳደግ የሚጠቅም፣ እርስ በእርስ እንዲማማሩ እድልን የሚፈጥር፣ የክህሎት ደረጃዎችን በማሳየት በዘርፉ ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች ለባለድርሻዎች የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመዋል። የውድድሩ አሸናፊዎች የክህሎት ጅማሪያቸው ማሳያ እንጂ ፍጻሜ አይደለም፡፡ ገና ብዙ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የሥራ እና ክህሎት ሚንስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ ውድድሩ በመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የቴክኖሎጂና የክህሎት ሥራዎችን የያዙ ተወዳዳሪዎች የተገኙበት መሆኑን ገልጸው፤ የቀረቡት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውድድሮች ችግር ፈቺ የሆኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ሚንስትሯ ገለፃ ፤ውድድሩ ከፍተኛ የፉክክር እና የአርበኝነት ስሜት የታየበት ነው። ከፍተኛ ትምህርትም ተወስዶበታል። በአይነቱም በጥራቱም የተሻለ ውድድር ነው። ውድድር ስለሆነ ማበላለጥ ስለሚያስፈልግ እንጂ ሁሉም ተወዳዳሪዎች አእምሯቸውን እና እጆቻቸውን ተጠቅመው አዲስ ነገር ማምረት ስለቻሉ አሸናፊዎች ናቸው። ዳኝነቱን ግልፅ እና ፍትሃዊ ለማድረግ ውድድሩ በበይነ መረብ እንዲተላለፍ ተደርጓል ነው ያሉት።

ውድድሩ ከውድድር በላይ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ሚንስትሯ፤ ክልሎች ለነበራቸው ሚናም እውቅና ሰጥተዋል።

የሽመና ማሽን የሠራው ወጣት ደምስ ኪዳኔ በበኩሉ የ500ሺ ብር ተሸላሚ መሆኑን ገልጾ፤ የተበረከተለት ገንዘብ የራሱን ሥራ ለመፍጠር የሚያስችለው መሆኑን ተናግሯል። በዚህም ሁሉም ፕሮግራሙን ያዘጋጁ ተቋማት እና መምህራኖቹን አመስግኗል፡፡ በቀጣይም ተመሳሳይ ውድድሮች የፈጠራ ባለሙያዎችን የሚያበረታቱ በመሆናቸው ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

በውድድሩ በአራት ማእከላት በ22 ዘርፎች ሲካሄድ የቆየ ሲሆን 70 ቴክኖሎጂዎችም ለእይታ ቀርበዋል። በሠልጣኝ፣ በአሠልጣኝና በኢንተርፕራይዝ ለተወዳደሩ ተሳታፊዎች እውቅና እና ከ300ሺህ እስከ 500ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቷል።

አራተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር በሥራና ክህሎት ሚንስቴር አዘጋጅነት ለተከታታይ ስድስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል፡፡

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You