አፍሪካነርስ በመባል የሚታወቁት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ነጭ ዜጎችን አሜሪካ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በስደተኛነት ልትቀበል መሆኑን ደቡብ አፍሪካ ተቸች። ነጭ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ ገብተው የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ዶናልድ ትራምፕ “ቅድሚያ” የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።
ስደተኞቹን የመቀበል ሂደቱ በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀምር ዋይት ሐውስ በይፋ አላረጋገጠም። የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አሜሪካ “በፖለቲካ ምክንያት” የምትፈጽመው ይህ ድርጊት የደቡብ አፍሪካን “ሕገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲ ሥርዓትን” የናቀ ነው ብሏል።
ባለፈው የካቲት ወር ትራምፕ አፍሪካነርስ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ “የዘር መድልዎ” ሰለባ ናቸው ብለው የተናገሩ ሲሆን፣ እነዚህ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ መጥተው መኖር የሚያስችላቸውን ውሳኔ አሳልፈዋል። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ወደ አሜሪካ መሄድ የሚፈልጉ ሰዎችን እንደማያስቆም ገልጾ፤ በዚህ ሂደት ወደ አሜሪካ የሚወሰዱት ግለሰቦች የወንጀል ክስ ያለባቸው አለመሆናቸው መረጋገጥ እንዳለበት አሳስቧል።
ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መድልዎ ደርሶባቸዋል የሚለውን ክስ ግን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አጣጥሎታል። በእርሻ አካባቢዎች በሚደርሱ ጥቃቶች ነጮች በተለየ ሁኔታ ዒላማ አለመደረጋቸውንም አክሏል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ እንደገለጹት፣ አሜሪካ መኖር የሚፈልጉ ደቡብ አፍሪካውያን ነጮችን ቃለ መጠይቅ እየተደረገላቸው መሆኑን እና “የዘር መድልዎ የገጠማቸው አፍሪካነርስ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል” ሲሉም አስታውቀዋል።
እነዚህ ወደ አሜሪካ በመሄድ መኖር የሚፈልጉ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መቼ ወደ ዚያው መጓዝ እንደሚጀምሩ ግን አልተጠቀሰም። ደቡብ አፍሪካ የነጮችን መሬት ያለ ካሳ ነጥቃለች ሲልም የትራምፕ አስተዳደር ከሷል። ደቡብ አፍሪካ ይህንን አስተባብላለች።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያደገው የትራምፕ አማካሪ ኢሎን መስክ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ነጭ አርሶ አደሮች ላይ “የዘር ጭፍጨፋ” ፈጽሟል ሲል በተደጋጋሚ ይሰማል። በመጀመሪያው ዙር 54 አፍሪካነርስ ወደ አሜሪካ እንደሚወሰዱ ተጠቁሟል።
አሜሪካ ከተቀረው ዓለም የስደተኞችን ጥያቄ ላለመቀበል ወስና ሀብታም ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን እንደ ስደተኛ ለመቀበል መፍቀዷ ያለውን ተቃርኖ ትችት ቀርቦበታል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም