እሥራኤል የኢራኑን የበላይ መሪ ለመግደል የነበራትን እቅድ ትራምፕ ውድቅ አደረጉ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሥራኤል የኢራኑን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኾሜኒን ለመግደል የነበራትን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን ሦስት ባለሥልጣናት ገለጹ። እንደ አንድ ባለሥልጣን መረጃ ከሆነ ትራምፕ ለእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ኾሜኒን መግደል “ጥሩ ሃሳብ አይደለም” ሲሉ ነግረዋቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ መረጃ ላይ በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም። በሁለቱ መሪዎች መካከል ውይይቱ የተካሄደው እሥራኤል በኢራን ላይ ዓርብ ጥቃት ከከፈተች በኋላ ነው ተብሏል። ኔታንያሁ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅት ትራምፕ አያቶላህን ለመግደል የነበራቸውን እቅድ ውድቅ ማድረጋቸውን ሮይተርስ መዘገቡን ቢጠየቁም በቀጥታ ከማረጋገጥ ወይም ከማስተባበል ተቆጥበዋል።

የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር “በፍፁም ያልተከሰቱ ሐሰተኛ የውይይት መረጃዎች አሉ እና ወደዚያ መግባት አልፈልግም” ብለዋል።

አንድ የእሥራኤል ባለሥልጣን ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት “በመርሕ ደረጃ” እሥራኤል “የፖለቲካ መሪዎችን አትገድልም። እኛ ትኩረታችን በኒውክሌር እና በወታደራዊ ተቋማት ላይ ነው። ስለ እነዚያ ፕሮግራሞች ውሳኔ የሚሰጥ ማንም ሰው በነፃነት እና ያለ ምንም ተጠያቂነት መሆን አለበት ብዬ አላምንም” ብለዋል።

እሥራኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በኢራን የኒውክሌር መሠረተ ልማት እና ሌሎች ዒላማዎች ላይ ጥቃት የሰነዘረችው ባለፈው ሳምንት ዓርብ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ ሀገራት መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ ጥቃቱ እሁድ ዕለት ሦስተኛ ቀኑን ይዟል።

ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ ስለመጣው ግጭት በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ “ኢራን እና እሥራኤል ስምምነት ማድረግ አለባቸው” ካሉ በኋላ፣ ሁለቱን ሀገራት ግጭቶችን እንዲያቆሙ እንደሚያደርጉ ሲገልፁ በቅርቡ ግጭት ውስጥ ገብተው የነበሩትን ሀገራት በመጥቀስ “ልክ ሕንድ እና ፓኪስታንን እንዳስማማሁት ሁሉ” ብለዋል።

ትራምፕ በካናዳ ወደሚካሄደው የቡድን ሰባት ሀገራት ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ለእሥራኤል የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል ገልጸው፤ ሀገሪቱ በኢራን ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንድታቆም ጠይቀው እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።

የአሜሪካ እና የኢራን ስድስተኛ ዙር የኒውክሌር ድርድር እሁድ ዕለት ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የአሸማጋይዋ የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሰይዲ መሰረዙን አስታውቀዋል። ኢራን ለኳታር እና ኦማን በእሥራኤል ጥቃት እየተፈጸመባት የተኩስ አቁም ስምምነትን ለመደራደር ዝግጁ እንዳልሆነች መናገሯን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት፤ አሜሪካ “በኢራን ላይ ከደረሰው ጥቃት ጋር ምንም ግንኙነት የላትም” ብለዋል። “በማንኛውም መንገድ፣ ዓይነት ወይም ሁኔታ በኢራን ጥቃት ከደረሰብን፣ የአሜሪካ ጦር ኃይሎች ከዚህ በፊት አይታው በማታውቀው ደረጃ በሙሉ ኃይል እና ጥንካሬ ርምጃ ይወስዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በሌላ በኩል የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አስታውቋል በእሥራኤል ላይ የሚካሄደው ዘመቻ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ እስከምትጠፋ ድረስ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ከእሥራኤል ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ለቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት እንደሚቀጥልና መጠኑም ሊሰፋ እንደሚችል የኢራን ገላጋይ ምክር ቤት ገልጿል።

ኢራን የእሥራኤልን ኤም ኪው-9 ሪፐር ሰው አልባ ወታደራዊ አውሮፕላን በኢራቅ ድንበር አቅራቢያ መትታ ጥላለች። በሃይፋ የሚገኘውን የኃይል ማመንጫ ጨምሮ በርካታ የእሥራኤል ስትራቴጂካዊ ዒላማዎች ወድመዋል።

ኢራን የእሥራኤልን የአየር መከላከያ ሥርዓት ማዛባት የሚያስችሉ “አዲስ ዘዴዎች” ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች። የኢራኑ ፕሬዚዳንት የቀጠለውን የእሥራኤል ጥቃት በጋራ ለመመከት የኢራን ሕዝብ አንድነት እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል። ኢራን ውስጥ የእሥራኤልን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሲያጓጉዙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ በደቡብ ቴህራን የተጠመደ ቦምብም ማክሸፍ ተችሏል። ቴልአቪቭ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በተሰነዘረበት ጥቃት ቀላል ጉዳት ደርሶበታል። በኢራን ጥቃት ዘገባው እስከተጠናከበት እሥራኤል ውስጥ 20 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ 200 ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ከሀገሪቱ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።

የእሥራኤል ጦር በኢራን የኩድስ ኃይል የጦር ማዘዣ ማዕከልን እንዲሁም የሚሳኤል ማስወንጨፊያን ከነተቆጣጣሪ ወታደሮቹ መትቻለሁ ብሏል። ሁለት ተጨማሪ የእሥራኤል የስለላ አገልግሎት (ሞሳድ) ባልደረቦች በኢራን ዋና ከተማ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢራን ፖሊስ ቃል አቀባይ ገልጸዋል። በእሥራኤል ጥቃት ኢራን ውስጥ ከ220 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ 1 ሺህ 500 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

*የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያ ሚን ኔታንያሁ፣ እሥራኤል የኢራንን “ድርብ ስጋት” ለማስወገድ ቆርጣ ተነስታለች ሲሉ መናገራቸውን ቢቢሲና ስፑትኒክ ዘግበዋል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You