ጋብቻ በሕይወት ውስጥ ካሉ ጥልቅ ቁርጠኝነቶች መካከል አንዱ ነው። ትዳር ፍቅርን፣ ጓደኝነትን እና መረጋጋትን የሚያጠቃልል ሕብረት ነው። ሁለት ግለሰቦችን የሚያገናኝ፣ የጋራ ሕልሞችን፣ የጋራ እድገትን እና ዘላቂ አጋርነትን የሚሰጥ የተቀደሰ ትስስር ነው። ሆኖም ልክ እንደ ማንኛውም ትርጉም ያለው ጉዞ ትዳርም ከፈተና የጸዳ አይደለም። ብዙ ባለትዳሮች ወደ ጋብቻ የሚገቡት ከፍተኛ ተስፋ እና የፍቅር እሳቤዎች ይዘው ነው። ይሁን እንጂ አንዳንዴ እውነታው ከዚያ የተለየ የሚሆንበት ግዜ አለ። ብዙውን ጊዜ የተግባቦት ችግር፣ የገንዘብ ማጣት እና ልጆችን በንፁህ የወላጅነት ፍቅር ተግባብቶና ተመካክሮ ለማሳደግ ላይ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።
እነዚህ ተግዳሮቶች ካልተፈቱ በጣም ጠንካራ የሆኑትን ግንኙነቶች ጭምር ሊያበላሹ ይችላሉ። አንዳንድ በዚህ ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ የተሰሩ ጥናቶች እና ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በትዳር ውስጥ የሚያጋጥም ፈተናን በትዕግስት እና በብስለት ማሸነፍ ይቻላል።
ጋብቻ በመግባባት፣ በፍቅር እና በማያቋርጥ ጥረት ላይ ተመስርቶ የሚያድግ የቤተሰብ ሽርክና ነው። ፍቅር ሁለት ሰዎችን አንድ ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ግን ግንኙነቱ በጊዜ ሂደት ውስጥም የሚቀጥል እንዲሆን የሁለቱም ሰዎች ጠንክሮ መሥራት አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ሀገራት ባሉ ባሕሎች ጋብቻ የሁለት ግለሰቦች ጥምረት ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ፣ የማሕበረሰብ ወግ እና እሴቶች የሚንፀባረቁበት አብሮነት ነው።
ጥንዶች ከሚያጋጥሟቸው በጣም የተለመዱ ጉዳዮች አንዱ የግንኙነት መቋረጥ ነው። አለመግባባቶችን ተከትሎ ለረጅም ግዜ የሚቆዩ ያልተፈቱ ግጭቶች በባልና ሚስት መካከል ስሜታዊ ርቀት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ይህንን ክፍተት ለማስተካከል ውጤታማ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ (መደማመጥ)፣ እርስ በእርስ ርሕራሄ እና ሐቀኛ ስሜትን ለማሳየት መሞከር አስፈላጊ ነው። ጋብቻ ፍቅርን፣ ወዳጅነትን እና መረጋጋትን የሚሰጥ ከሕይወት ቃል ኪዳኖች መካከል አንዱ ነው። ሆኖም እንደ ማንኛውም ትርጉም ያለው ጉዞ፣ ትጋትን፣ ትዕግስት እና የማያቋርጥ ጥረትን ይጠይቃል። ብዙ ባለትዳሮች ወደ ጋብቻ የሚገቡት ከፍተኛ ተስፋ ይዘው ቢሆንም እውነታው ግን ከዚያ የተለየ ሊሆን ይችላል። ማንኛውም ሰው ይህንን አውነታ ታሳቢ ማድረገ ይኖርበታል።
እነዚህ ችግሮች በአብዛኛው በሁሉም ትዳር ውስጥ ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ሆኖም ችግሩን መፍታት የቻሉና የተሳካላቸው ትዳሮች በችግሮች አለመኖር ሳይሆን እንዴት በጋራ መፍትሄዎችን ለማምጣት እንደሚሠሩ የሚያሳይ ነው።
በግንኙነት ላይ የተደረጉ የሥነ ልቦና ጥናቶች በትዳር ውስጥ ብስለት፣ ጥበብ፣ እውቀትን፣ የግጭት አፈታት ችሎታዎች እና መከባበርን በእጅጉ አስፈላጊነት እንደሆኑ ይጠቁማሉ። ባለትዳሮች ለራሳቸው ጥራት ያለው ጊዜ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው። ድርጊታቸው ቅርበታቸውን የሚያጠናክሩ እና አንዳቸው የሌላኛቸውን የግል እድገት የሚደግፉ መሆን አለበት። ይህንን ማድረጋቸው ትዳራቸው ዘላቂና ጥብቅ እንዲሆን አንደሚያደርግ ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ያሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ባለትዳሮች ንሰሀ አባት የመያዝ ሀይማኖታዊ ሕግ አላቸው። የሌሎች እምነት ተከታዮችም እንዲሁ መሰል አማካሪና አባቶች አሏቸው። ይህንን መሰል ሥርዓት የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ ችግር በሚገጥም ወቅት ከሀይማኖት መሪዎች ምክርንና ተግሳፅን መቀበል በትዳር ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት፣ ለመፈተሽ እንዲሁም ጠቃሚ አመለካከቶችን ለመያዝ እንደሚረዳ ይናገራሉ።
ጋብቻ የሰው ልጆች የእድገት እና የመኖር ትርጉምን የያዘ ቤተሰባዊ ጉዞ ነው። እንደ ግለሰብ እና እንደ ትዳር አጋር የሚገጥሙ መሰናክሎች ሁሉ የውድቀት ምልክቶች አይደሉም። ይልቁኑ መተማመንን ለማጠናከር፣ ግንኙነትን ዘላቂ ለማድረግ የሚረዱ ናቸው። ለዚህ ነው ‹‹ትዳርን በትዕግስት፣ በግል ጥረት እና እርስ በእርስ ለመላመድ ፍፁም ፈቃደኝነት በማሳየትና መገንባት ይቻላል›› የሚባለው። ጥንዶች የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ወደ ፍቅር እና ስምምነት ወዳለው ግንኙነት ሊለውጡት ይችላሉ።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው መጋቢ አዕምሮ ዓምድ ላይ በትዳር ውስጥ ያሉ የተለመዱ ተግዳሮቶችን ለመዳሰስ የፈለገውም በዚህ ምክንያት ነው። በመሆኑም በዳሰሳው ችግሮቹን ማንሳት ብቻ ሳይሆን ጥንዶች እንዴት ፈተናዎቹን ማሸነፍ እንደሚችሉ በሚከተሉት ነጥቦች ይመለከታል። ግንዛቤ የሚያስጨብጡ የጥናት ውጤቶቸን ያቀርባል።
በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን መረዳት
እያንዳንዱ ጋብቻ ችግሮች ያጋጥሙታል። ነገር ግን ችግሩን መለየት ወደ መፍትሄው ለመሄድ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ለምሳሌ በባለትዳሮች መካከል ደካማ የሀሳብ ልውውጥ (የተግባቦት ችግር) ብዙውን ጊዜ አለመግባባት ከሚፈጥሩ ምክንያቶች መካከል ይነሳል። አለመግባባቶች በንግግር ሳይፈቱ ሲቆዩ ወደ ቅሬታ አዘንብለው በጥንዶቹ መካከል ስሜታዊ መራራቅን ይፈጥራሉ።
በሌላ በኩል በትዳር ውስጥ የተለያዩ ከቤት ውጪ የሚደረጉ ልማዶች ወይም የገንዘብ ዕዳ ትዳር ውስጥ ውጥረት ሊፈጥር ይችላል። አለመተማመን እና ከፍተኛ ፀብን በመፍጠር ረገድ ፋይናንስ በትዳር ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛል። ሌላው በትዳር ውስጥ አሉታዊ ነገር ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል ያደሩ አለመግባባቶች ይጠቀሳሉ። ችግሮችን ወዲያው መፍታት አስፈላጊ ነው። ግጭቶቸን ወዲያው እልባት አለመስጠት መቀራረብ በጊዜ ሂደት እየቀነሰ ይሄዳል።
ስኬታማ ትዳር ለመገንባት
ስኬታማ ትዳር ውስጥ ጥብቅ መግባባትና መረዳዳት ይታያል። ትዳርን ውጤታማ ለማድረግ የመግባባት ችሎታ ማዳበር አስፈላጊ ነው። የትዳር አጋርን በውይይት ወቅት ንቁ ሆኖ ማዳመጥ የሚያስቀና ትዳር ለመገንባት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። አለመግባባት ሲፈጠር ለመናገር ብቻ ከማኮብኮብ (ከመጠበቅ) ይልቅ የባልሽን/የሚስትህን አመለካከት በመረዳት፣ ለስሜታችሁ እርስ በእርስ በመጨነቅ እና በጥንቃቄ ምላሽ በመስጠት ላይ ማተኮር ይገባል። ይህንን የውይይት መስፈርት የሚተገብር ትዳር ውጤታማና ደስተኛ ቤተሰብ መመስረት ይችላል።
ከዚህም በላይ ለውይይት የተወሰነ ጊዜ መመደብ በዕለት ተዕለት ኃላፊነቶች ላይ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግና ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ይረዳል። ጋሪ ቻፕማን (ዶ/ር) የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላኛቸው “የፍቅር ቋንቋ” መጠቀም፤ አጋርነትን የሚያሳዩ ማረጋገጫ ቃላት መለዋወጥ ይኖርባቸዋል። ይህንን ማድረጋቸው እርስ በእርስ እንደሚተሳሰቡና በመካከላቸው ፍቅር መኖሩን ያመለክታል። ችግር በሚገጥማቸው ግዜው በእርጋታና በጥሞና መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ ይሆናል።
ወላጅነት የጋራ ኃላፊነት
በትዳር ውስጥ አንዱና ዋንኛው ጉዳይ ልጆችን ማፍራት ነው። እርሱም ደግሞ በጥንዶች መካከል አለመግባባትን ሊፈጥር ይችላል። ልጆችን ማሳደግ ደስታን እና ፈተናዎችን በአንድነት ይዞ የሚመጣ ነው። ውጤታማ የልጅ አስተዳደግን ለመከተል በትዳር ጓደኞች መካከል አንድነት እና ትብብር ይጠይቃል። በወላጅነት መንገዶችና የአስተዳደግ ስልቶች ላይ ቀደም ብሎ መስማማት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ግጭቶችን አስቀድሞ ይከላከላል። ምክንያቱም ወጥነት ያለው የባህሪ ቀረፃና እንክብካቤ መከተል ለልጆች ደህንነትና ጤናማነት ወሳኝ ነው። በልጆች አስተዳደግ ላይ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም እነሱን በውይይት መፍታት እና መተባበር ለቤተሰቡ መረጋጋትን ይፈጥራል።
በምሳሌ ልጆችን መምራት በወላጅነት ውስጥ በጣም አስፈላጊ ከሆኑ ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ነው። ልጆች የወላጆቻቸውን ባሕርይ ያስተውላሉ፤ እርሱንም እንዲሁም ይኮርጃሉ። በመሆኑም ባለትዳሮች ደግነትን፣ አክብሮትንና ትዕግሥትን እርስ በእርስ ማሳየት አለባቸው። ይህንን መሰል ጤናማ ቤተሰብ ለመገንባት በጋራ መዝናኛ ሥፍራዎች መሄድ፣ በጋራ መመገብ ወይም የቤተሰብ ሥርዓቶች መጠበቅ ይበልጥ የቤተሰቡን ትስስር ያጠናክራሉ። ስለዚህ ዘላቂ፣ ሰላማዊና ፍፁም ጤናማ ቤተሰብ ለመገንባት በልጆቻችን ላይ ለማስረፅ በቅድሚያ እራሳችን ላይ መተግበር አለብን።
በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናቶች እንደሚያሳየው የመናገርና ሀሳባቸውን የመግለፅ መብት የሚሰጣቸው እና ድምፃቸው እንዲሰማ የሚበረታቱ (በመሰል ከባቢ የሚያድጉ) ልጆች ጠንካራ ይሆናሉ፤ በራስ መተማመናቸው የጎለበተና ችግሮችን የመቋቋም ችሎታን የሚያዳብሩ ይሆናሉ ይላል።
ግጭቶችን በጥበብ መፍታት
በትዳር ውስጥ ግጭት አይኑር ማለት አይቻልም። የሰው ልጆች መካከል ግጭት ሁሌም ይፈጠራል። በማንኛውም ጋብቻ ውስጥ አለመግባባቶች የማይቀሩ ናቸው። ነገር ግን ግጭቱን (አለመግባባቱን) የምንፈታበት መንገድ የቤተሰባዊ ግንኙነቱን ጤንነት ይወስናል። በግጭቶች ጊዜ መረጋጋት የሰፈነበት ከባቢ መፍጠር ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። ይህም በባለትዳሮች መካከል የበለጠ ውጤታማ ውይይት ለማድረግ ያስችላል። አካላዊ ጥቃትን ከሚያበረታቱ ድርጊቶች ይልቅ በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ መፍቀድ፣ መከባበርን እና አለመግባባትን ዝግጁ መሆን ችግሩ በፍጥነት መፍትሄ እንዲያገኝ ይረዳል።
ለመግባባት ብዙ እርቀት መሄድ በትዳር ውስጥ የሚከሰትን ግጭት ለመፍታት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ስኬታማ የትዳር ሕይወት ያላቸው ጥንዶች ከግለሰባዊ ፍላጎቶቻቸው ይልቅ ለቤተሰባዊ መልካም ግንኙነት ቅድሚያ ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆን አለመግባባቶችን ወዲያው ይፈታሉ። አንዱ ሲያጠፋ የሚጠይቀው ይቅርታ ከልብ ከሆነ ቁስሎችን ለመጠገን እና መተማመንን እንደገና ለመገንባት ያስችላል።
ለቀጣይ የጋራ የቤተሰብ ጉዳዮች ስኬታማነት የትዳር ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎችን ማማከር ጠቃሚ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። በተለይ በሥነ ልቦና የትዳር ምክር ውስጥ ችግር ከመፈጠሩ አስቀድሞ የሚሳተፉ ጥንዶች ብዙውን ጊዜ የበለጠ ውጤታማ ቤተሰብ ይኖራቸዋል።
ዓለም አቀፍ ዕይታ
ዓለም አቀፍ ጥናቶች ትዳር ወጤታማ እንዲሆን በሚያደርጉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጣሉ። በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው ለትዳር አጋራቸው ለሚደረግላቸው እያንዳንዱ ፍቅርና ድጋፍ ምስጋናቸውን አዘውትረው የሚገልጹ ጥንዶች ጠንካራ ቤተሰባዊ ግንኙነት አላቸው። በጀርመን ሀገር በተካሄደ አንድ ጥናት ደግሞ ጥንዶች ችግር በሚገጥማቸው ወቅት ሁለቱም በጋራ ችግሮቻቸውን ሆነ ጭንቀታቸውን የሚጋፈጡ ከሆነ፤ ይበልጥ ደስተኛ ሕይወትን ይመራሉ። ሌላው ጥናት ወደ ጃፓን ይወስደናል። ጥናቱ ጥንዶች ወይም የትዳር አጋሮች ደግነትንና ፍቅርን የሚያሳዩ ቃላት የሚለዋወጡ ከሆነ፣ በፍቅር ወይም ረጋ ያለ አካላዊ ንክኪ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው ከተገበሩ ግንኙነታቸው ውጤታማ እንዲሆን ይረዳቸዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የጎትማን ኢንስቲትዩት ለትዳር ስኬት ቁልፉ ለእያንዳንዱ አሉታዊ ነገር አምስት አዎንታዊ የሆኑ ምላሾችን መስጠት ያስፈልጋል ይላል። በመሆኑም ጥንዶች በቀን ውስጥ አንድ አሉታዊ አለመግባባት ቢፈጥሩ ቢያንስ በአምስት ጉዳዮች ላይ ፍቅር በተሞላበትና ቅንነትን በሚያስቀድም ድርጊት ውስጥ እራሳቸውን ማቆየት አለባቸው። ትዳርን በጊዜ ሂደት የሚያጠናክሩት በቋሚነት የሚከወኑ ትንንሽ የፍቅር እና የመከባበር ተግባራት መሆናቸውንም ጥናቱ ያመለክታል።
በመጨረሻም ይህንን መልዕክት በማንሳት እንሰነባበት። የተሳካ ትዳር መመስረት የችግሮች አለመኖር ማለት አይደለም። ይልቁኑ ችግር ሲያጋጥሙ ፈተናውን በፍቅር፣ በትዕግስት እና በጥበብ የመዳኘት ችሎታ መፍጠር ነው። ለውይይት (የሀሳብ ልውውጥ) ቅድሚያ በመስጠት፣ ከሀይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች ጋር በመምከር፤ ዓለም አቀፍ ምርምርና ጥናቶችን በማንበብና ትዳራችንን፣ የወለድናቸው ልጆች እንዲሁም አጠቃላይ ቤተሰባችንን መጠበቅና ደስተኛ መሆን እንችላለን። ሰላም!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም