
ዜና ሐተታ
አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ በእያንዳንዱ ዘርፍ ቴክኖሎጂ የምርት ሂደትን በማፋጠን፤ ጥራትን በመቆጣጠር እና ምርታማነትን በማሳደግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ከዓለም ጋር አብሮ ለመጓዝ፣ የአገልግሎትና ምርትን ለማቀላጠፍ ቴክኖሎጂን አሟጦ መጠቀም ይደር የሚባል ጉዳይ ነው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍም አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮቶች የቴክኖሎጂ ፍሬ የሆኑትን እንደ አቶሜሽን፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎት፤ በይነመረብ፤ ሮቦት እና አዳዲስ ፈጠራዎችን አዋሕዶ በመጠቀም መረጃን በስፋት ሰብስቦ በመተንተን እና ቁሳዊውን የፋብሪካ አካል ከዲጂታሉ ጋር በማስተሳሰር ምርትን እና የማምረት ሂደትን ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
እንደ ሀገር ኢትዮጵያም አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ወደ ተግባር በማስገባት የዘመኑን ቴክኖሎጂ የጀርባ አጥንት ያደረገና ውጤታማ እና ጥራቱን የጠበቀ ምርት የሚያመርት ኢንዱስትሪ እንዲኖር እየተንደረደረች ትገኛለች።
የካይዘን ልህቀት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ምንዳዬ ይርጋ እንደሚናገሩት፤ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያ ወሳኝ በሆነ የለውጥ ሂደት ላይ ነው ያለችው። ይህን የኢንዱስትሪ ሂደት ከማሳለጥ አንጻር ቴክኖሎጂ ዋናውን ድርሻ እንደሚይዝ ይናገራሉ።
የኮምፒውተር፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሮቦቲክስ ጨምሮ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የኢንዱስትሪውን የማምረት ቅልጥፍና፤ ጥራት የተሻለ ደረጃ እያደረሱ መጥተዋል የሚሉት ኢንጂነር ምንዳዬ፤ አራተኛው ኢንዱስትሪ አብዮት ይህንን መሠረት አድርጎ የተጀመረ የኢንዱስትሪ ንቅናቄ ነው ይላሉ።
አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት (ኢንዱስትሪ 4.0) የነበሩ ቴክኖሎጂዎችን ዘመኑ በሚጠይቀው መንገድ እንዲቃኙ በማድረግ፤ አስፈላጊውን መረጃ ተንተርሶ እውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲኖር እያደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።
ስለ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በቅጡ ለመረዳት የመጀመሪያው ወሳኝ ነገር ሰው ሠራሽ አስተውሎት ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለምርት ሂደት የሚውሉት የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት ያካተቱ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ኢንዱስትሪዎች ከማምረት ባሻገር የምርምር እና የሙከራ ማዕከላት እንዲሆኑ ይፈለጋል። ከዚህ አኳያም በሁለተኛ ደረጃ የኩባንያዎች መረጃ የማደራጀት አቅም ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ አንዳንዴ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሆነ ሌሎች አጋር አካላት፤ ለተፈለገ ዓላማ ከኢንዱስትሪ ተቋማት መረጃ ሲፈልጉ የማያገኙበት ሁኔታ ይስተዋላል። ይህን ችግር ለመፍታት አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ተግባር ላይ ማዋል መፍትሔ እንደሆነ ነው ያብራሩት።
ሌላኛው ጉዳይ የአውታር ትስስር ሲሆን፤ በበየነ መረብ አማካኝነት መረጃዎችን በማስተሳሰር፤ መረጃዎችን በተናጠል ከማስቀመጥ ይልቅ በሚፈለገው የሥራ ሂደት እና ከውሳኔ ሰጪ አካላት ጋር በማስተሳሰር የምርት ሂደት እንዲሳለጥ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ያስረዳሉ።
ኢንጅነር ምንዳዬ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ጉዳይ ያደረገችው የመጀመሪያው ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ነው። ምክንያቱም የሀገር ውስጥ ምርት ለመጠቀም ከጥራት አንጻር ኢትዮጵያዊ የሆነ ዜጋ እንኳን ጥርጣሬ አለበት። ከዚህ መነሻነት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ያሉትን ችግሮች ማለፍ ግድ ይላል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ገበያው፤ እየመጡ ያሉት ተመራማሪዎች፤ ባለሙያዎች እና እንደ አጠቃላይ ያሉት ስልታዊ ጉዳዮች አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ጥቅም ላይ ለማዋል ያስገድዳሉ። ለዚህም ብዙ መቸገር ሳይኖር የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎች በዓለም ገበያ ላይ ስላሉ እነሱን በማምጣት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች እድሜ ጠገቦች እንደመሆናቸው አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖች ከጊዜው ጋር የሚሄዱ ላይሆን ይችላል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት በሥራ ላይ ከማዋል አንጻር በተለያዩ ተቋማት የሚሠሩ ምርምሮችን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ልምምዱን መጀመር እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
ወደ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ለመግባት አሁን ላይ ያሉትን ዕድሎች የሚያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለአብነትም ስለ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሥልጠና ለወጣቶች እየተሰጠ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት 250 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተሳታፊ ናቸው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኩልም ከልማት አጋሮች ጋር ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በተጨማሪም በዲጂታል 2025 የተሠሩ ሥራዎችም ይህን የሚደግፉ መሆናቸውን ያነሳሉ። አራተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት ውጤታማ ለማድረግ ግንዛቤ መፍጠር፤ የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሥራት፤ እና ሥነ ምሕዳሩን ምቹ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያስቀምጣሉ።
የአይኮ ግላቭ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት አሰፋ እንደሚናገሩት፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን በጥልቀት ከመረዳት እና ከመጠቀም አንጻር እንደ ሀገር በጣም ወደ ኋላ የመቅረት ነገር ይስተዋላል። ጥራቱን ለጠበቀ እና ውጤታማ ለሆነ የምርት ሂደት እና የገበያ ሥርዓት ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተረድቶ ጥቅም ላይ ማዋል ለሁሉም ኢንዱስትሪዎች የሕልውና ጉዳይ ነው ይላሉ።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጠቅመው ኢንዱስትሪያቸውን በሚመሩ ተቋማት እና በማይጠቀሙ ተቋማት መካከል ያለው ልዩነት ትራክተር የማረስ እና በዶማ የመቆፈር ያህል ልዩነት እንዳለው በመግለጽ፤ የኢንዱስትሪዎች የሰው ሠራሽ አስተውሎት የመጠቀም ጉዳይ ለምርጫ የሚተው እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ከዚህ አንጻር የግሉን ዘርፍ ያካተተ ሥራ መሥራት፤ በተለይም በዓለማችን ላይ ያሉት ጎግልን ጨምሮ ትልልቅ ፈጠራዎች እና ኩባንያዎች የተመሠረቱት ከዩኒቨርሲቲ በወጡ ሃሳቦች እንደመሆኑ፤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ።
የቢጂአይ ኢትዮ ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኢንዱስትሪያል ሶሊዩሽን ባለቤት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቢጂአይ ናይከር በበኩላቸው የላሊበላን፤ የፋሲልን እና የአክሱም ግንቦች ከተገነቡ በኋላ፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለማድረስ ያልተቻለው ማኅበረሰቡ አዲስ ነገሮችን ፈጥኖ የመቀበል ነገሩ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው። አሁንም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን ላይ ስንደርስ በሚፈለገው መልኩ ሊሰፋ ያልቻለው፤ በሁሉም ዘርፍ ተመሳሳይ እና ዘመኑን የዋጀ ፖሊሲ ባለመኖሩ መሆኑን በመጠቆም፤ የተጀመረውን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ የተሳሰረ እና አንድ ግብ ያለው ፖሊሲ ያስፈልጋል ሲሉ ሃሳባቸው ሰንዝረዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም