
አዲስ አበባ፡ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እየተገነባ የሚገኘው የሐረር ፌዴራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ፕሮጀክት ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የግንባታው ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኃይሌ ገብረዋህድ አስታወቁ።
ኢንጂነር ኃይሌ ገብረዋህድ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እየተገነባ የሚገኘው የሐረር ፌዴራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ፕሮጀክት ግንባታ በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ ነው። በአሁኑ ጊዜ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የግንባታ አፈፃፀምም 69 ነጥብ 03 በመቶ ደርሷል ብለዋል።
የፕሮጀክቱ የግንባታ አፈጻጸም የሆስፒታሉ ሕንጻ እንዲሁም የሐኪሞች መኖሪያ ሕንጻ የመሬት ቆረጣ፣ የስትራክቸር፣ ብሎኬት ግንባታ ሥራዎች መቶ በመቶ መጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ የሆስፒታሉ ሕንጻ ለብቻው ሲታይ ደግሞ የውስጥና የውጭ ልስን ሥራ 95 በመቶ፣ የእምነበረድ ሥራ (የወለል፣ የደረጃ፣ የመስኮት) 72 በመቶ፣ የጅፕሰም ቻክ ሥራ 82 በመቶ፣ የደረጃ እና የጣራ ብረት ሥራ 78 በመቶ፣ የመሬት ሴራሚክ ሥራ 61 በመቶ እንዲሁም የግድግዳ ሴራሚክ ሥራ 32 በመቶ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የሐኪሞች መኖሪያ ሕንጻ በተመለከተ ደግሞ ተነጥሎ ለብቻው ሲታይ የውስጥና የውጭ ልስን ሥራ 98 በመቶ፣ የእምነበረድ ሥራ (የወለል፣ የደረጃ፣ የመስኮት) 95 በመቶ፣ የጅፕሰም ቻክ ሥራ 93 በመቶ፣ የደረጃ እና የጣራ ብረት ሥራ 79 በመቶ፣ የአሉሚኒየም ሥራ 81 በመቶ፣ የመሬት ሴራሚክ ሥራ 79 በመቶ እንዲሁም የግድግዳ ሴራሚክ ሥራ 28 በመቶ እንደተከናወነ አመልክተዋል።
የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የግንባታ ውል ወስዶ በሐረር ከተማ እየገነባ የሚገኘው የሐረር ፌዴራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ፕሮጀክት ባለቤት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ አንድ ባለ 8 ወለል ሕንጻ የሆስፒታሉ ሲሆን፣ አንድ ባለ 8 ወለል ሕንጻ ደግሞ የሐኪሞች የመኖሪያ ሕንፃ ማካተቱንና ሁለቱም ሕንጻዎች ዘመናዊ የግንባታ ሥራዎች የሚከናወኑባቸው ናቸው ብለዋል።
የፕሮጀክት የግንባታ ውል እኤአ ሰኔ 01 ቀን 2022 በኢንተርፕራይዙ እና በባለቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከተፈጸመ በኋላ የሳይት ርክክብ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 07 ቀን 2022 መካሄዱን አውስተዋል።
ግንባታው እ.ኤ.አ. ነሐሴ 05 ቀን 2022 መጀመሩንና በውሉ መሠረትም ግንባታው እ.ኤ.አ. ሐምሌ 21 ቀን 2025 እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የፕሮጀክቱ የግንባታ ወጪ ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ አንድ ቢሊዮን 058 ሚሊዮን 849 ሺህ423 ብር መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ አሁን የተሠራው ሥራ አፈጻጸም በፋይናንስ 50 ነጥብ 19 በመቶ ሲሆን በግንባታ ደግሞ 69 ነጥብ 03 በመቶ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ኢንጂነር ኃይሌ እንደሚሉት ፕሮጀክቱ ሲጀመር የነበሩ ተግዳሮቶች መካከል አንደኛው ተጠቃሽ ክረምት ወቅት መሆኑ፤ የዲዛይን መቀያየር፣ አስፈላጊ የሆኑ የግንባታ ማሽነሪዎች እና ማቴሪያሎች እጥረት፣ በቁፋሮ የሚወገደውን አፈር መድፊያ ቦታ ማጣት፣ ብቃት ያለው የኮንስትራክሽን ሙያተኛ በበቂ ሁኔታ በአካባቢው አለማግኘት፣ የተመረጠ አፈር (Selected Material) በቅርበት አለማግኘት፣ ከፍተኛ የሆነ የአለት ድንጋይ ሆስፒታሉ በሚገነባበት ሕንፃ ስፍራ ማጋጠሙ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ግንባታው ከተጀመረ በኋላ የነበሩ መልካም አጋጣሚዎች የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ሲያስረዱ በሚመለከታቸው አካላት ልዩ ትኩረት መሰጠቱ ማለትም በግንባታው ባለቤትና በሐረሪ ክልል ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቢሮዎች አስፈላጊው ድጋፎች መደረጋቸው ተጠቃሽ እንደሆኑ ተናግረዋል። ኢንተርፕራይዙም ልዩ ትኩረት በመስጠት በጀት፣ የሰው ኃይል፣ ማቴሪያል እና ማሽነሪዎች አሟልቷል ብለዋል።
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም