
የኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደገ ይገኛል፡፡ ዓመታዊ የዘርፉ ዕድገት በ2014 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 8 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በ2016 ደግሞ በ8 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል፣ በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ በ12 በመቶ ያድጋል ተብሎ ተተንብዮዋል፡፡
ዘርፉ ሀገሪቱ የሚያስፈልጓትን ምርቶች በማምረት፣ በተኪ ምርቶቹም ሀገርን ከውጭ ምንዛሬ ወጪ በመታደግ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ እያሳያቸው ከሚገኙ ለውጦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ባለፈው ዓመት አምራች ኢንዱስትሪው ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በተኪነት ማምረት ችሏል፤ በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን አምርቷል፡፡ ይህ አሀዝ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡
ለውጡ ይህ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ነው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሶስተኛው ኢግዚቢሽን ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮኔቬንሽን ማዕከል በተጀመረበት ወቅት የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ አምራች ኢንዱስትሪው በሌሎች አራት ዘርፎ ች ለመጣው ለውጥም ከፍተኛ አስ ተዋጽኦ አድርጓል፡፡
325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ ከ13ሺህ 800 በላይ መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቅሰው፣ በንቅናቄው ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን አስታውቀዋል።
የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ በሦስት ዓመታት ወደ 61 በመቶ ማሳደግ መቻሉን፣ አምራች ኢንዱስትሪው ለአራቱ የትኩረት ዘርፎች ዕድገት እንደ ድልድይ ሆኖ ማገልገሉንም ተናግረዋል።
በማዕድን፣ በራሱ በኢንዱስትሪው፣ በግብርናው፣ በዲጂታል፣ በቱሪዝም ዘርፎች ላይ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችን፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታና ለመሳሰሉት የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችን፣ እንደ ኤሌክትሪክ ምሰሶ፣ ብረታብረት ሥራዎች ያሉትን በማምረት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡
በተለይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጓቸውን ማሽኖች በማምረት ለራሱ ለኢንዱስትሪው፣ እንዲሁም ለግብርናው ዘርፍ ሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚያስፈልጉ ማሽኖችን እያመረቱ ያለበት ሁኔታ ሲታይ የዘርፉ ለውጥ ከሚገለጸውም በላይ ስለመሆኑ ይመሰክራል፡፡
በኮቪድ 19፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በዓለም አቀፍ ጫና ሳቢያ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዞ የነበረው ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቃ መጥቶ ለሀገር አለኝታ መሆኑን እያሳየ ይገኛል፡፡
እንደ ሲሚንቶ እጥረት ያሉትን ችግሮች በመፍታት ያበረከተው አስተዋጽኦ በአብነት ሊጠቅስ ይችላል፤ በዘርፉ ባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት በቅርበት ባከናወነው ተግባር አንድ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ወደ ማምረት ሥራ ተሸጋግሯል፤ በዚህም የሲሚንቶ እጥረቱን እና የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት ተችሏል፡፡
ሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስመጣት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታወጣ ከነበረበት ሁኔታ እየተላቀቀች ያለችበት ሁኔታም ለዚህ በአብነት ሊጠቀስ ይገባል፡፡ ይህን ምርት የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎችን በመገንባት በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል፡፡
ይህ ሁሉ ለውጥ የተገኘው መንግሥት ዘርፉ ከገባበት መቀዛቀዝ ወጥቶ ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መተግበር ከጀመረ ከ2014 አንስቶ ነው፡፡ በንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በመለየት ለመፍታት ብዙ ተሠርቷል፡፡ በተለይ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ከጉምሩክ፣ ከቦታ፣ ከገበያ ፣ ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት አንጻር የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት በትኩረትና በቅርበት ተሠርቷል፡፡ ብዙም ለውጥ ተመዝግቧል፡፡
ለውጡ የመጣው ለኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ መሠረተ ልማቶች፣ ወዘተ የሚመለከታቸው ተቋማት የሚሳተፉበት የኢንዱስትሪ ካውንስል በማቋቋም ፣ ሥራውን በቅርበት በመከታተልና ለተግዳሮቶች መፍትሄ በማስቀመጥ በተደረገ ርብርብ ነው፡፡
ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የኢንዱስትሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፤ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይህ የተቀናጀ ተግባርና የተገኘ ውጤት በእጅጉ ሊደነቅ ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው ከአምራች ኢንዱስትሪው አሁንም ብዙ ይጠበቃል፤ አምራች ኢንዱስትሪው ተነቃቃ እንጂ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ይቀረዋል፡፡
ሀገሪቱ ለመልማት ያላት ፍላጎት፣ አያሌ የኢንዱስትሪ ውጤቶች አሁንም ከውጭ እየገቡ ያሉበት እንዲሁም የዘርፉ ችግሮች እየተፈቱ ያለበት ሁኔታ ሲታሰብ ኢንዱስትሪው ላይ በተጠናከረ መልኩ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተኪ ምርት እየታየ ያለውን ለውጥ በእጥፍም ከእጥፍም በላይ ለማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉትንም ማምረት ላይ መሠራት ይኖርበታል፡፡
ለእዚህ ደግሞ አሁንም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትልቅ ስፍራ ይኖረዋል፡፡ ለውጡን እንደ ትልቅ አቅም በመጠቀም የሀገር ፍላጎትና ራዕይን ለማሳካት መንግሥት በዚህ ንቅናቄ እያደረገ ያለው ድጋፍና ክትትል በርግጥም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡
ንቅናቄው ለአስር ዓመት የሚተገበር እንደመሆኑ በቀጣይም እንደሚሠራበት ይታወቃል፡፡ በዘርፉ የተገኘው ለውጥ ለንቅናቄው ሥራ ሌላ አቅም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ለውጡን እያደነቁ ለዘርፉ የላቀ ለውጥ መሥራት ቀጣዩ ተግባር መሆን ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም