የመደጋገፍ እሴትን በማጠናከር የቤተሰብ ገቢን ለማሳደግና ለማስፋት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡– ቤተሰብ እንደ አንድ ወሳኝ ተቋም በመመልከት በማህበረሰቡ ያለውን የመደጋገፍ እሴትን በማጠናከር የቤተሰብ ገቢን ለማሳደግና ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ፡፡

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊ የቤተሰብ ኑሮ እና የሥራ ሁኔታ በማሻሻል ጠንካራ ማህበረሰብ መፍጠር በሚል ርእሰ ጉዳይ ላይ ውይይት ሲካሄድ እንዳሉት፤ የተሻሻለ የቤተሰብ ሥራና ገቢ በመፍጠር የሀገር ኢኮኖሚ ማሳደግ እና በሁለንተናዋ የፀናች ሀገር ለመገንባት መዋቅር በመዘርጋት እና የሰው ኃይል በመመደብ እየተሠራ ነው፡፡

የቤተሰብ ኑሮ ለማሻሻል እና ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው ንቅናቄ መሆኑን የገለፁት ኃላፊዋ፤ አዲስ መዋቅር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከክልሎች ጋር በቀጥታ እየሠራን ነው፤ በአረጋውያን፣ ከስደት ተመላሾች እና አጠቃላይ ቤተሰባዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ ቤተሰብን እንደ አንድ ተቋም በመመልከት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ቤተሰብ ለመገንባት በክልሎች የተሠራው ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቁመው፤ ለአብነትም በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በአፋርና በሀረሪ ክልሎች አበረታች ጅምር ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የፀና ቤተሰብ እና ሀገር እንዲኖረን የተሻሻለ የቤተሰብ ሥራና ገቢ ሊኖር ይገባል ያሉት ሚንስትር ዲኤታዋ፤ ይህም የተሳካ ለማድረግ በመልካም ተሞክሮ እና በኢኮኖሚ ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኙ ቤተሰቦች ሀብት በማሰባሰብ የቆየውን የመደጋገፍ እሴት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልሎች የቀረቡ የበጀትና ሌሎች ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ መልኩ ምላሽ እንደሚሰጥ በመጠቆም፤ በተለይ ህብረተሰቡ እርስ በራስ በሥነ ልቦና እና በገቢ እንዲደጋገፍ የማስተሳሰር ሥራ ዋነኛ የትኩረት ሥራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ማህበረሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ ራሱን ወደ ተሻለ ኑሮ ለውጦ ለሌላው አርአያ እንዲሆን በትኩረት መሥራትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ አመልክተው፤ የቤተሰብ ገቢን ለማሳደግ የእርስ በዕርስ መደጋገፍን ባህል ለማጎልበት በትኩረት መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአረጋውያን እና የቤተሰብ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሮበሌ በበኩላቸው፤ ቤተሰብ አምራች ሲሆን ሀገር ምርታማ እና በኢኮኖሚ ያደገች ትሆናለች፤ የቤተሰብ ሁለንተናዊ ብልፅግና እንዲሁም ደህንነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ በቀጣይ ሥራዎች ላይ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን፤ ቤተሰብ ወሳኝ ተቋም መሆኑን በመገንዘብ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን በማስመልከትም ለችግር የተጋለጡ፣ በስደት ምክንያት ችግር ውስጥ የገቡ የማህበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍ እና ማህበረ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተገቢውን ሚናቸው እንዲወጡ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You