
ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ውጤታማ እየሆነች ትገኛለች። ኢንዱስትሪው ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ ይገኛል።
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ኢንዱስትሪው በተለይ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረበት ከ2014 ወዲህ ብዙ ለውጦች እየታየበት ይገኛል። ዓመታዊ የዘርፍ ዕድገት በ2014 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው በ2016 በ8 ነጥብ 4 በመቶ አድጓል፣ በተያዘው የበጀት ዓመት (2017) በ12 በመቶ ያድጋል ተብሎ ተተንብዯል።
ሰሞኑን በተካሄደው ሶስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መክፈቻ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በንቅናቄው ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል። በንቅናቄው 325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም 13ሺህ 800 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ጀምረዋል። የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 46 በመቶ በሶስት ዓመታት ወደ 61 በመቶ ማሳደግ ተችሏል። አምራች ኢንዱስትሪው ለአራቱ የትኩረት ዘርፎች ዕድገት እንደ ድልድይ ሆኖ ማገልገሉንም ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በማምረት ሀገርን ከውጭ ምንዛሬ ወጪ እየታደገ ሲሆን፣ በ2017 በጀት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተኪ ምርቶች በኢንዱስትሪው ተመርተዋል። ኢንዱስትሪው ለዘመናት ከውጪ ይመጣ የነበረን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ችሏል፤ በሲሚንቶ ላይ ይታይ የነበረውን ስር የሰደደ ችግር መፍታትም የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለሌሎች ዘርፎች ማሽነሪዎችን፣ ብረታ ብረቶችን፣ ወዘተ በማምረት እያቀረበ ይገኛል።
መንግሥት ለዘርፉ ያደረጋቸው ድጋፎች ዘርፉ አሁን እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፉ የተደረገው ድጋፍና ክትትል ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው።
ከንቅናቄው በፊት ኢንዱስትሪው የመሠረተ ልማት፣ የመሥሪያ ቦታ፣ የፋይናንስና የመሳሰሉት ስር የሰደዱ ችግሮች ነበሩበት። በእዚህ ላይ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ዓለም አቀፍ ጫናዎች በዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፈውበትም ነበር። በዚህ ሁሉ የተነሳ የማምረት አቅም አጠቃቀም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ እንደነበርም ይታወቃል።
ኢንዱስትሪውን ከእነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች ለማውጣት በመንግሥት በኩል ከተከናወኑ ተግባሮች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ይጠቀሳል። በእዚህ ንቅናቄ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ይጠቀሳሉ። በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዋና ዋና ሥራዎች የእቅድ አፈጻጸሙን አስመልክቶ በቅርቡ መግለጫ በሰጠበት ወቅት የኢንተርፕራይዝ ልማቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ያሲን እንዳሉት፤ ኢንተርፕራይዝ ልማቱ ለዘርፉ ልማት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር፣ የዘርፉን አስፈጻሚና ባለድርሻ አካላት አቅም በመገንባት፣ መሠረተ ልማቶችን በማልማት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራርና ትብብር በማሳደግ እንዲሁም የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍን ማስፋፋትና ተወዳዳሪ በማድረግ ተልኮውን ለመወጣት እየተጋ ይገኛል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የኢንተርፕራይዝ ልማቱን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደጠቆመውም፤ ኢንተርፕራይዝ ልማቱ ውጤታማ አፈጻጸም አስመዝግቧል።
ለአብነትም ሁለት ሺ 875 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም ታቅዶ አንድ ሺ 958 ኢንተርፕራይዞችን ማቋቋም ተችሏል። 733 መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ለመቋቋም ታቅዶ ከእቅድ በላይ 794 ተቋቁመዋል። በገጠር 205 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች መቋቋሙ ተመላክቷል።
የሥራ እድል በመፍጠር በኩልም በገጠር በተቋሙ ኢንተርፕራይዞች ለአንድ ሺህ 525 ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል። አዲስ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋምና ነባሮቹን በማጠናከርም ለ151 ሺህ 726 ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩም ተጠቁሟል። ይህ አፈጻጸም የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ከነበረው 133 ሺ 973 የበለጠ መፈጸም የታቸለበት ነው።
ለኢንተርፕራይዞች ሰፊ የገበያ ትስስር መፍጠርም ተችሏል። የተፈጠረ የገበያ ትስስር በብር ሲሰላም ሰባት ቢሊየን 305 ሚሊየን 425 ሺህ 547 ብር ታቅዶ 10 ቢሊየን 850ሚሊየን 58 ሺህ 258 ብር አፈጻጸም ተመዝግቧል። በተኪ ምርት በኩልም እንዲሁ 902ሚሊየን 191 ቶን ተኪ ምርቶችን ለማምረት ታቅዶ 8 ሚሊየን 435 ሺ 222 ቶን ማምረት ተችሏል። በዚህም 881 ሚሊየን 722 ሺ 924 ዶላር ለማዳን ታቅዶ አንድ ቢሊየን 608 ሚሊየን 933 ሺ 234 ዶላር ማዳን ተችሏል።
ነባር አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማጠናከር፣ በአምራች ኢንተርፕራዞች የደረጃ ሽግግር፣ በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች በቀረበ የሥራ ማስኬጃ ብድር፣ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች በቀረበ የማምረቻ መሳሪያ አቅርቦት በኩልም እንዲሁ ውጤታማ ተግባሮች መከናወናቸው በመግለጫው ተጠቁሟል።
የኢንተርፕራይዝ ልማቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ሮቤል አሕመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳብራሩት፤ የኢንተርፕራይዝ ልማቱ አነስተኛ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ በኩል በርካታ ለውጦችን አስመዝግበዋል።
ቀደም ሲል የአምራች ኢንተርፕራይዝ ዘርፉን የሚደግፉ የመንግሥት ተቋማት አለመኖራቸው እንደ ችግር ይነሳ እንደነበር አስታውሰው፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ችግሩን ከመቅረፍ ባለፈ በትስስር እና በትብብር ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከፋይናንስ ተቋማት፣ ከግብዓት አቅራቢ ተቋማት እንደዚሁም ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በኮሚቴ ደረጃ በመዋቀር ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ በተከናወነው ተግባር ለውጦች ማምጣት ያስቻለ ትልቅ እድል መምጣቱን አቶ ሮቤል ጠቁመዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት ኢንተርፕራይዞች የት ቦታ እንደሚገኙ፣ ምን ዓይነት የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እንዲሁም ከግብዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ካውንስል ተቋቁሞ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች በማድመጥ ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር ተዘርግቷል። ይህም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ እምርታ እንዲያሳይ አስችሎታል።
ወደ ዘርፉ ለመግባት ያለው ፍላጎት ምን ያህል ነው በሚል ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፤ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን ከማቋቋም አኳያ ዘርፉ በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ አቶ ሮቤል ነግረውናል። ከእቅድ አኳያ ሲገመገምም የተሻለ ለውጥ እንደተገኘበትም ጠቅሰው፣ ምን ያህል ነው የሚለው በጥናት ደረጃ ስላልተገለጸ ለመመለስ አዳጋች ነው ብለዋል። እንደ አጠቃላይ ያለፉትን ዓመታት ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ስናየው ግን በጥሩ የለውጥ ቁመና ላይ ይገኛል ሲሉ ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ወደ ዘርፉ ለሚገቡ የሚሰጡ ድጋፎች አነስተኛ እንደነበሩ አስታውሰው፣ ግለሰቦችም ሆኑ ሌሎች ባለሀብቶች ደፍረው መግባት ያልቻሉበትን ሁኔታ እንደነበር ገልጸዋል። አሁን ላይ ችግሮቹ ተቀርፈው ድጋፍ እና መሰል የትብብር አካሄዶች ተፈጥረው ኢንተርፕራይዞች ወደ ሥራ እየገቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ለዚህም ባለሀብቶችን በመጋበዝ የክልል ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት መድረክ በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ሥራ እንደተሠራ አመላክተዋል።
ከዚህ በፊት በሀገር ውስጥ ይመረቱ ያልነበሩ ምርቶች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መመረት እንደጀመሩ ጠቅሰው፣ በኤክስፖርቱም ለውጥ መታየት መጀመሩን አመልክተዋል። ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እስከ ማቅረብ የደረሱበት ሰፊ እድል መፈጠሩን ገልጸው፣ ይህ ግን ሀገራችን ከምትፈልገው እና ካላት እምቅ የማምረት አቅም አኳያ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ አስታውቀዋል።
‹‹በርካታ ወጣቶች አሉን፣ በርካታ ጸጋዎች አሉን፤ እነዚህን ኃይሎች በምንፈልገው ልክ ወደ ሀብትነት በመቀየር በኩል ይቀረናል። ኢንተርፕራይዝ ልማት ከተማ ላይ ብቻ የነበረውን የኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ወደ ገጠር በማስፋት ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ ይገኛል›› ብለዋል።
ለአምራች ዘርፉ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎች፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ገጠር ላይ እንደመገኘታቸው የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን ኢንሼቲቭ በሚል በዚህ ዓመት በተጀመረ የንቅናቄ ፕሮግራም እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። በአንድ ወረዳ ላይ ቢያንስ አንድ ቢበዛ ሶስት ከፍተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
በዘርፉ ለመሰማራት የዜጎች ፍላጎት እስከየት ድረስ ነው? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ጥሩ ፍላጎቶች እንዳሉ ተወካዩ አመላክተዋል። ወደ ዘርፉ ለመሰማራት በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። አብዛኞቹ ኢንተርፕራይዞች ለሥራ ፍቃድ ሲጠይቁ የሥራ ቦታ፣ የማምረቻ መሳሪያ ሌሎች ድጋፎችን አካተው መሆኑን ተናግረው፤ ከጥያቄዎቻቸው ጋር የተመጣጠነ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሌለም አመልክተዋል። ይህን በተመለከተ በተሠራ ሥራ በዚህ ዓመት የተሻለ የፋይናንስ ድጋፍ መፈጠሩን ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በሊዝ ፋይናንስ፣ በማሽን ሊዝ እንዲሁም በመሥሪያ ካፒታል ወደ አስር ቢሊዮን ብር የሚሆን ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ቀርቧል። ይህ ግን ከኢንተርፕራይዝ ፍላጎት አንጻር በቂ ነው ተብሎ አይወሰድም።
በኢንተርፕራይዞች በኩል ከእቅድ በላይ ፍላጎት እንዳለ ጠቅሰው፣ እቅዶች ሲዘጋጁ በአምስት ዓመት እና በአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅዶች ላይ ተመሥርተው፣ የክልሎችን ሀብት መነሻ በማድረግ እንዲሁም ያለፈውን ዘመን የሥራ አፈጻጸም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አብራርተዋል። ከአቅም ውስንነት፣ ከፋይናንስ ችግር፣ ለኢንተርፕራይዞች ከሚቀርብ የማምረቻ ቦታዎች ችግር እና ከመሳሰሉት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ሁሉንም ጥያቄዎች ማስተናገድ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
ኢንተርፕራይዞች ወደሚቀጥለው ደረጃ መሸጋገር አይፈልጉም፤ ባሉበት መቆየትን ይመርጣሉ ይባላል፤ በእነሱ የተያዘው ቦታ ደግሞ ለሌሎች ይፈለጋልና በዚህ ላይስ ምን እየተሠራ ነው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የተባለው ነገር እውነት መሆኑን ገልጸዋል። ለተጀመረው ለውጥ እና በዘርፉ ላይ ለሚታየው ችግር መፍትሔ ይሆን ዘንድ በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ያሉ ኢንተርፕራይዞች ወጥ ወደ ሆነ አሠራር እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል። በተጨማሪም የሽግግር ስትራቴጂ መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
መመሪያው ኢንተርፕራይዞች እንዴት ነው መሸጋገር የሚችሉት፣ ምን ዓይነት ድጋፍ ነው ሊያገኙ የሚገባቸው ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች በኃላፊነት እንዲሠሩ የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በተካሄዱ ጥናቶች የፋይናንስ፣ የማምረቻ ቦታ፣ የግብዓት አቅርቦት ጥያቄዎች የኢንተርፕራይዞች መሠረታዊ ጥያቄዎች በሚል ተነስተዋል። ችግሩን ለመቅረፍ እንደ ብሔራዊ ባንክ ካሉ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው የአምራች ካውንስል ችግሮችን በማቅረብ የኢንተርፕራይዞች ጥያቄ እንዲመለስ እየተሠራ ይገኛል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ሲሠራ እንደነበር ጠቅሰው፣ ይህ ፕሮጀክት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
ተወካዩ እንዳብራሩት፤ ከማምረቻ መሳሪያዎች አኳያ ለሚነሱ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቦታዎችን እንዲገነባ፣ እንዲያስተዳድር ኃላፊነት የተሰጠው ቢሆንም፣ መንግሥት የክላስተር ማዕከላትን እየገነባ እንዲሄድ መደረጉ አዋጪ ሊሆን ስለማይችል የግሉ ዘርፍ ወደዚህ ዘርፍ ገብቶ መገንባት የሚችልበትን ሁኔታ እንዲኖር ጥናት እየተደረገ ነው።
ኢንተርፕራይዞች ለማሽን ሊዝ የወሰዱትን ብድር በመመለስ በኩል ያለው አፈጻጸም ምን እንደሚመስል ጠይቀናቸው በሰጡት ማብራሪያ ማሽን ሊዝ በብድር እንደሚቀርብ ጠቁመው፣ ኢንተርፕራይዞች የክፍያ ውላቸውን ሲጨርሱ ማሽኑን በንብረትነት እንደሚረከቡ አቶ ሮቤል ገልጸዋል። ከአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት ብድራቸውን በአግባቡ እንደሚመልሱም ገልጸዋል።
አቶ ሮቤል እንዳሉት፤ ኢንተርፕራይዝ ልማት በ2017 በጀት ዓመት በቀሪዎቹ ሁለት ወራት ትኩረት የተሰጠባቸውን ጉዳዮች ከግብ ለማድረስ ይሠራል። አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙ፣ አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያገኙ፣ ኤክስፖርት ላይ እንዲያተኩሩ መሥራቱን ይቀጥላል። በዚህ ዓመት የተጀመረው የገጠር ኢንዱስትሪያል ኢንሼቲቭ አመርቂ ውጤት እንዲያመጣ እንዲሁም ለቀጣይ ድሎች መሠረት እንዲጥል ለማድረግ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
አቶ ሮቤል ለውጥ የትስስር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንተርፕራይዝ ዘርፉ ላይ ትልቅ እምርታ እያሳየ መምጣቱን በመጠቆም፣ ማኅበረሰቡ የሀገር ውስጥ አምራቾችን እንዲያበረታታ፣ የራስ ምርትን በመግዛት፣ በማስተዋወቅ አጋርነቱን እንዲያሳይ ጠይቀዋል። አስፈጻሚ አካላትም ከአምራች ዘርፉ ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ዘርፉን እንዲያጠናክሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘላለም ተሾመ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም