ፈተናን ለማለፍ መልፋት

ራሷን ጨምሮ ሶስት ልጆቿን በወጉ ለማሳደር ጠዋት ማታ እረፍት አታውቅም፡፡ የኑሮ መክበድ ከአቅም ማነስ ጋር ታክሎ ብዙ ፈትኗታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ለችግር እጅ አትሰጥም፡፡ እስካሁን ስለ ልጆቿ ስትል ብዙ ታግላለች፤ ከትምህርታቸው እንዳይሰናከሉ ስትል ወጥታ ወርዳለች፤ ለፍታለች። ለመኖር ስትል ገንዘብ በሚያስገኝ ሥራ ሁሉ አለሁ ትላለች፡፡ የኮንስትራክሽን ሥራ ባለባቸው ቦታዎች ሁሉ ለጭነት የምትገለገልባቸውን አህዮች ይዛ ትገኛለች፤ የተገኘውን ሁሉ ጭና ታደርሳለች። ታማኝነቷን ብዙዎች ይመሰክሩሏታል።

ሲሚንቶ፣ አሸዋ፣ ብሎኬትና ብረት ነጋዴዎች ታታሪነቷን ስለሚያዩ ያዝኑላታል። በተቻላቸው ያግዟታል። እሷ በቦታው ላይ ባትገኝም የጭነት ሥራ ከመጣ ደውለው ይጠሯታል። ሁሌ ሳቂታ ተጫዋች ናት፤ መሽቶ በነጋ ቁጥር ጉልበቷ እንደ አዲስ ነው፡፡ የዕለት ጉርሷን ሞልታ ፣ የልጆቿን ፍላጎት ለማድረስ መሮጥና መድከም ግዴታዋ ነውና የቤቱን የምግብ ዝግጅት ሌሊቱን ከውና ጸሀይ ስትወጣ ደግሞ ሥራ ባለበት ቦታ ሁሉ ትገኛለች – ጠንካራዋ ብርቄ ሞላ።

ወይዘሮ ብርቄ ዛሬ ኑሮዋ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ጎሮ ወረዳ 9 አካባቢ ሲሆን ልጅነቷን ያሳለፈችው በገጠር ነው። እድሜዋ ከፍ ሲል እንደ እኩዮቿ መሮጥና መጫወትን አሳልፋለች፡፡ ባደገችበት የገጠር አካባቢ ከብቶች ጠብቃለች። በቤት ውስጥ ቤተሰቦቿን በአቅሟ የጉልበት ሥራ በመሥራት አግዛለች። ከምንጭ ውሃ መቅዳት፣ እንጨት ከዱር መልቀም ፣ ሌሎች በቤት ውስጥ እናቷን ማገዝ ግዴታዋ ነበር። ይሄንን ግዴታዋን መወጣቷን ትናገራለች። ሆኖም ግን እንደ እኩዮቻ የፊደል ገበታ አልጨበጠችም።

የመማር ፍላጎት ቢኖራትም እድሉን ግን አላገኘችም። ይህንን ቤተሰቦቿ አለማድረጋቸውን በቁጭት ታነሳለች። ቤተሰቦቿ አንድም በአካባቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ፤ ሌላውም ለትምህርት የነበራቸው እሳቤ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። በክፋት ሳይሆን ባለማወቃቸው ነው ፤ በጨዋታ እንኳን የትምህርት ነገር በዛ ቤተሰብ መካከል አይነሳም። አልፎ አልፎ ወንዶች ከአጥቢያቸው መማራቸውን የምታውቀው እሷ ግን ሁሌም እንደእነሱ ብሆን ስትል መመኘቷ አልቀረም፤ ሆኖም ግን ምኞቷ ከምኞት የዘለለ አይደለምና እስካሁን የማንበብም ሆነ የመጻፍ እድል አልገጠማትም። ይሄንን ቁጭቷን ታዲያ ልጆቿን በማስተማር መወጣት ትሻለች።

እሷ ሳትበላ ልጆቿን እየመገበች፤ እሷ ሳትለብስ ልጆቿን እያለበሰች ታስተምራለች። ምንም የሥራ ጫና ቢገጥማት፣ የጤና መታወክ ቢፈትናትና ድካም ቢጫጫናት ልጆቿን ከትምህርት ቤት እንዲቀሩና እንዲያግዟት አታደርግም። ወገቧን በነጠላዋ ሸብ አድርጋ አህዮቿን እየነዳች ጭነት ወደሚገኘበት ቦታ ታቀናለች።

ወይዘሮ ብርቄ አዲስ አበባን የረገጠችው በአጋጣሚ ነው። ከአዲስ አበባ የመጡ ሰዎች ልብሳቸው ነጭ፣ እግራቸው በጫማ፣ አነጋገራቸው ያማረ ብላ በማስላት ከእነሱ ጋር እሄዳለሁ ብላ ከጠያቂ ዘመዶቿ ጋር ፊቷን ወደ አዲስ አበባ አደረገች። ያም ሆኖ ግን የተመኘችውን ትምህርት ሊያስተምሯት አልፈቀዱም። ይልቁንም የቤት ሠራተኛ አደረጓት። ገንዘብም አይከፍሏትም፤ ይሄ ሁኔታ እሷን አላስደሰታትም።

ስለዚህ ሠርቼ ገንዘብ ማግኘት አለብኝ ብላ ወሰነች። ውሳኔዋንም ተገበረችውና በትንሽ ደመወዝ በቤት ሠራተኛነት ተቀጠረች። አንድ ሁለት… እያለች የሥራ ቦታዎችንም ቀያየረች። ሆኖም ግን በአጋጣሚ በተፈጠረ ግንኙነት ጸነሰችና ከቤት ሠራተኛነት ሥራዋ ጋር ተቆራረጠች። አነስተኛ ይሉት ቤት ተከራይታም ኑሮን ተያያዘችው። በራሷ ልዩ ልዩ ሥራዎችን እየሠራ ልጆቿን ማሳደጉን ቀጠለች። ልጆቿን ከተለያዩ ወንዶች ነው የወለደቻቸው፤ እናም አባት ነኝ ብሎ የሚደግፋት፣ ከጎኗ የሚቆምላት ማንም አጋር የላትም። ስለዚህ የእናትነት የአባትነት ሃላፊነቶችን ሁሉ ጥርሷን ነክሳ የምትወጣው እሷ ናት። ጠጋ ብሎ ላጫወታት ሰው ኑሮ እንደከበዳት ታወራለች።

ልጅ ማሳደግ ከባድ ፈተና መሆኑን ትናገራለች። ግን ደግሞ «ልጆቼንማ እኔ የኖርኩትን ኑሮ እንዲደግሙ አልፈልግም፤ ልጆቼን አስተምሬ ትልቅ ደረጃ አደርሳለሁ። የዛሬን ልፋቴን የሚክሱኝ ልጆቼ ናቸው» በማለት በልጆቿ ትመካለች። አምላክም አግዟት ልጆቿ በጥሩ መልኩ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ናቸው። እንዳሰበችውም አይዞሽ እናታችን እስካሁን አንቺ ለፋሽ አሁን እኛ ደርሰናል ከጎንሽ ነን እንደሚላት ተስፋ አላት።

ወይዘሮ ብርቄ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመኖሪያ አካባቢዋ ጨረቃ ሰፈር በሚባለው ወንዝ ዳር ነበር። አሁን አካባቢው በወንዝ ዳር ፕሮጀክት እየለማ ይገኛል። እሷም የመኖሪያ ሠፈሯ ከእዛ ርቋል። በመንገድ ዳር ዳር የነበሩ የሲሚንቶ ፣ ብረት እና የመሳሰሉት የንግድ ቦታዎችም አካባቢያቸውን በመቀየራቸው ምክንያት እንደ ቀድሞ ሥራው በምትፈልገው ልክ አልሆነላትም። ሥራውን ለማግኘትም ርቃ መሄድ ግዴታዋ ሆኗል። ያውቋት ይረዷት የነበሩ ነጋዴዎችም አሁን በቅርበት ስለማታገኛቸው አይዞሽ ሥራ ሲመጣ እንደውልልሻለን የሚላት ማጣቷን ትናገራለች።

« አሁን ነገሮች እየከበዱኝ መጡ። ጉልበቴን ይዤ መሥራት እየፈለኩ የምሠራው እያጣሁ ነው» ትላለች። ያም ሆኖ ብርቄ እጇን አጣጥፋ ፣ ጉልበቷን ታቅፋ አልተቀመጠችም። ሥራ ይሉት ገንዘብ አምጪ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ታስሳለች። በየመንደሩ እየዞሩ መማረርና ማማረርን ሥራዋ አላደረገችም።

«ልጆቼን ሳላስተምርማ» የሚለውን ቁጭቷን ከግቡ ልታደርስ አሁንም ቃሏን አላጠፈችም። የሥራዋን አይነት ቀይራ ትሠራለች። «የሚታጠብ ልብስ አላችሁ? አሻሮ የሚያስቆላ ሰው ሲኖር ጠቁሙኝ ፤ ባልትናም አዘጋጃለሁ» እያለች በየሠፈሩ በሚያውቋት አካባቢ ራሷን ለሥራ ታመቻቻለች። ያገኘችውን ሥራ እየሠራችም የሕይወትን ውጣውረድ ፣ የኑሮን ፈተና ተቋቁማለች።

የእሷንና የልጆቿን ጉሮሮ ሳትደፍን አትውልም ፤ለነገ የሚሉ አርቆ አሳቢነት ከእሷ አይለይም ፤ ከምታገኘው ትቆጥባለች። አሁን የገጠማትን ትልቅ ፈተና ያለፈችውም በዚሁ አርቆ አሳቢነቷ ነው። ነገሮች ተስተካክለው ሥራ ፍለጋ እስክትወጣ ልጆቿ የሚልሱት የሚቀምሱት አላጡም። ከቆጠበችው ወጣ አድርጋ የልጆቿን ጉሮሮ ደፍናለች።

ወይዘሮ ብርቄ አሁን በገባችበት ሰፈር በቤት ኪራይ ተሰቃይታለች፡፡ በኪራይ ያሳለፈቻቸው ጥቂት ወራት ምቹ ይሏቸው አልነበሩም፡፡ አህዮቿን በአጠገቧ ታስራለች። የአህዮቹ እና ከእነሱ የሚወድቀው እዳሪም አካባቢውን በሽታ የሚረብሽ በመሆኑ በአካባቢው ሰዎች ሁሌም ጉንፋን አስያዝሽን የሚሉ ስሞታዎች ይቀርቡባታል። አህዮቹ አትክልት በሉ የሚሉ ቅሬታዎች ይመጡባታል፤ አለፍ ሲልም ከፍ ዝቅ አድርገው ይናገሯታል። ይሄም ሆኖ የሆዷን በሆዷ ችላ አይከፋሽ ሆና ነው የምታሳልፈው። አሁን ግን ብዙ ነገር እንደፈተናት ትናገራለች። ቢሆንም ግን «እጅ አልሰጥም ፈጣሪም ይረዳኛል ለልጆቼማ ሳልሆን አልቀርም» ማለቷን አላቋረጠችም።

አልማዝ አያሌው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You