‹‹2018 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የዓባይ ግድብ ሪቫንን እንቆርጣለን›› – ወይዘሮ ፍቅርተ ተዓምር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጊዜያዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራቸው የልማት ሥራዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰውን የሕዳሴ ግድብ ነው። ይህ ግድብ እንደ ጅማሬው ሁሉ ፍጻሜውም ያምር ዘንድ ደግሞ ሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል። የሕዳሴው ግድብ የሀገሪቱ ተስፋ መሆኑን ከሕፃን እስከ አዋቂ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ስላመነበት አሁን ላይ ሥራው እንዲጠናቀቅ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።

ሕዝቡ በጉልበቱ፣ በእውቀቱ እና ባለው ሁሉ የግድቡን ሥራ እያገዘ ሲሆን በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም እንደቀጠሉ ናቸው። በእነዚህ ጥረቶችም ከፍተኛ ድሎችም ተመዝግበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በነበሩባት የውስጥ የቤት ሥራዎቿ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ በገዛ ውሃዋ ሳትጠቀም የቆየች ቢሆንም አሁን ደግሞ ጊዜው ደርሶ አልምታ ለመጠቀም ከዳር ደርሳለች።

ሕዝቡ ከዚህ በፊትም ቢሆን በዓባይ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቁጭት ነበረበት፤ “….ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” በማለትም ቁጭቱን በዘፈን ሲገልጽ ኖሯል። ይህንን ቁጭት አሰናስሎ ወደተግባር ለመግባት ግን የሚያደራጀው አካል ባለማግኘቱ ለዘመናት ያህል ውሃው በከንቱ ሲፈስ ኖሯል፤ ይህንን ቁጭቱን ወደ ተግባር የሚቀይርለት መሪ ባገኘ ጊዜ ግን ራሴን ችዬ የማንንም ርዳታ ሳልጠብቅ እገድበዋለሁ ለማለትም ጊዜ አልወሰደበትም።

ይህንን ሕዝብ ደግሞ አደራጅቶና ወደ አንድ አመጥቶዋ ሕብረት ጥንካሬ አድርጎ ወደ ሥራ ለማስገባት መንግሥት ትልቅ ኃላፊነት ወስዶም ተንቀሳቅሷል። ሕዝብን አስተባብሮ ሁሉም የድርሻውን በግድቡ ግንባታ ላይ አስተዋፅኦ ያደርግ ዘንድም ራሱን የቻለ ሕዝብን የሚያስተባብር ጽሕፈት ቤት አቋቁሞ ላለፉት 14 ዓመታት የግድቡን ግንባታ ሲደግፍ ቆይቷል። በዚህ ጉዞም ትንሽ የማይባል ውጤት ቢገኝም ጉዞውና ሥራው ግን ቀላል ነበር ለማለት አያስደፍርም።

እኛም የግድቡ አሁናዊ ቁመና እንዲሁም የሕዝቡን ተሳትፎ በተመለከተ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጊዜያዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከወይዘሮ ፍቅርተ ተዓምር ጋር ቆይታን አድርገናል።

አዲስ ዘመን፡- ወደ ኋላ መለስ ብለን የግድቡ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል የነበረውን ስሜት እንዴት ያስታውሱታል ?

ወይዘሮ ፍቅርተ፡– ዓባይ ሁሉንም በጋራ አንድ አድርጎ በማሰለፉ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል፣ ሀብታም ድሃ ሳይል፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካ፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ ልዩነት ሳያግደው ለግድቡ ድጋፍ ለማበርከት ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ያሰለፈ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

የሕዳሴው ግድብ የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሕዝቡ በደስታ ገንፍሎ ወጣ። ሠራተኛው ከወር ደመወዙ፣ አርሶ አደሩ ከምርቱ፣ አርብቶ አደሩ ከሚያረባቸው እንሰሳቱ፣ ነጋዴው ከንግዱ፣ ባለሀብቱ ከጥሪቱ፣ ምሁሩ በእውቀቱ፣ የኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ባለሙያው በሙያው፣ ተማሪው ከወር ቀለቡ፣ የቀን ሠራተኛ ከእለታዊ ገቢው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት መስክ ከሚያገኘው ቆጥቦ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በመደገፍ ግንባታውን ጀምሮ ለመጨረስ ተነሳ።

በመላው ሀገሪቱ ያለ ምንም የውጭ ሀገራት ብድርና ዕርዳታ በራሳችን አቅም ግድባችንን መገንባት እንችላለን ሲል ለግድቡ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በሙያና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። በዓባይ ወንዝ ላይ በራስ አቅም ግድብ መሥራት የልማት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነትና የማንነት ጉዳይ መሆኑን ሕዝቡ በተጨባጭ ድጋፍ አረጋገጠ።

የሀገር ውስጡን የሕዝብ የድጋፍ ማዕበል ተከትሎ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እና በትውልድ ኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሩ ልማት በጋራ በመነሳት ታላቁ የሕዳሴ ግድብን መገንባት ሀገራዊ ግዴታ ነው ሲል፣ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱ እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲው መስክ ለሀገሩ አምባሳደር በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። ዲያስፖራው ለሀገሩ ግድብ ውጭ ምንዛሬ ቦንድ በመግዛትም ሆነ በስጦታ ሲያበረክት ርቀትም ሆነ ድንበር አልገደበውም።

መላው ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚገኙት ለግድቡ ያሳዩት የድጋፍ መነሳሳት ሰፊና ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ይህን ድጋፍ ለማስተባበር የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የሆነ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ተቋቋመ። በምክር ቤቱ በተቻለ መጠን በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሲቪል ማህበራት እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ ሙያ ማህበራት እና ታዋቂ የሀገራችን ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወዘተ… የተካተቱ ሲሆን የምክር ቤቱንም ተግባር ለማከናወን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት በደንብ ቁጥር 244/2003 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ተግባር ተገባ።

የኅብረተሰቡ ድጋፍ በዓይነትም ሆነ በብዛት ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ተሳትፎውን በዘላቂነት ለማስቀጠል እና በትክክል ለታለመለት ግብ እንዲውል ለማስቻል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ በተግባር ላይ በማዋል ለግድቡ በየወሩ ከደመወዝ ላይ እስከ አስር በመቶ እየቆረጡ በመደገፍ እግረ መንገድም የዜጎችን የቁጠባ ባሕል ማሳደግ ተቻለ።

ለታላቁ ሕዳሴ ግደብ በብሔራዊ ደረጃ እና በክልሎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በሚከናወኑ የንቅናቄ እና ሀብት ማሰባሰቢያ ሁነቶች ከሕዝብ በስጦታ የሚመጡ ልዩ ልዩ ድጋፎችን (የቀንድ ከብት ግመሎች፣ ሌሎች እንሰሳት፣ አዝርዕቶች፣ የቅባት እህሎች፣ ማዕድናት፣ ቁሳቁሶች፣ ወዘተ…) በገንዘብ ተለውጠው በልገሳ እንዲገቡ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ቀጠለ። እስካለፈው ጥር ወር ድረስ በቦንድ ግዢ እና በስጦታ ባለፉት ዓመታት በአጠቃላይ ከሀገር ውስጥ 17 ቢሊዮን 994 ሚሊዮን 511ሺህ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ዲያስፖራውም ከተለያዩ ዓለማት 1ቢሊዮን 502 ሚሊዮን 390 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

ኅብረተሰቡ በቦንድ ግዢ እና ልገሳ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ እና ንቅናቄ መፍጠሪያ ሁነቶች በስፋት የተካሄዱ ሲሆን በተለይም በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ወገኖችን በቀላሉ ማሳተፍ እንዲቻል የ8100 -A የሞባይል አጭር መልዕክት ዕጣ ተዘጋጅቶ ለሶስተኛ ዙር በአየር ላይ በማዋል በአንድ መልዕክት ሶስት ብር በመላክ በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር ወደ 140 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል። ለ8100 A እና ለተለያዩ ሕዝብ ተሳትፎ እንዲውሉ ከተለያዩ ድርጅቶችና ባለሀብቶች በልገሳ የተሰበሰቡ ከመኖሪያ ቤት እና ከዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ጀምሮ በርካታ ዕጣዎችን ለደረሳቸው ዕድለኞች በመሸለም በርካቶች በሕዳሴ ግድብ ገጸ-በረከት ተንበሽብሸዋል። ዕጣ ያልደረሳቸውም ቢሆኑ በግድቡ ላይ የጣት ዐሻራቸውን በማሳረፍ የታሪክ ባለቤት ሆነዋል።

በዓለማችን የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽን በሀገራችንም ስጋት በደቀነ ጊዜ ኅብረተሰቡን በማሰባሰብ የሚከናወኑ ሁነቶችን እና መድረኮችን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ከኮቪድ ስጋት ነፃ ሆኖ በጣቱ ሞባይሉን በመጫን በ8100-A ለግድቡ ቤተሰብ በመሆን 1 ብር ድጋፍ የሚያደርግበት አሠራር በሥራ ላይ በማዋል ሶስተኛው ዙር ከተጀመረበት የካቲት 2012 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 2017 ድረስ) በዘላቂነት በመቀጠል ከፍተኛ ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል። በዚህም ባለፉት ዓመታት የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ እያንዳንዱ ሞባይል ተጠቃሚ በየዕለቱ የሚያስታውሰው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል።

ባለፉት ዓመታት የሀገራችን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጠቀሜታ በመረዳት ግድቡ ከተያዘለት የአገልግሎት ዘመን በላይ ተሻጋሪ እንዲሆን ግድቡን በደለል እንዳይሞላ በማለት በመላው ሀገሪቱ የተፋሰስ ልማት (የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ) ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ሕዝብና መንግሥት ለተፋሰስ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ተችለዋል።

ከግብርና ሚኒስቴር በመጣ መረጃ መሠረት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በማለት በየዓመቱ በአማካኝ 30 ቀናት በተፋሰስ ሥራ ላይ ያዋለው ጉልበት በገንዘብ ሲተመን ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ግድቡ በሀገሪቱ ዕድገት ላይ ምን ያህል የለውጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረ ማሳያ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚቃወሙት አካላት የሚነሱ ክሶች ስም ማጥፋቶችና አሉታዊ መረጃዎችን በመመከትና በመድፈቅ ኢትዮጵያውያን፣ በትውልደ ኢትዮጵያውን እና ወዳጆቻችን የሆኑትን በዓለም ዙሪያ በማስተባበር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጫና በማሳደር የተሠራው ሥራም ለመደበኛ ዲፕሎማሲው ቀላል የማይባል እገዛ አድርጓል። “አንድ ድምጽ ለግድባችን!” “One Voice for Our Dam!” በሚል በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያውን ለግድባቸው ድጋፋቸውን እንዲገልጹ በማድረግና ፒቲሽን ፊርማ በማሰባሰብ እንዲሁም ለግድቡ የድጋፍ ሰልፍ በማድረግ የምዕራባውያን ሀገራትን ከተሞች በማጨናነቅ ዲያስፖራው የሠራው በውጭ ሀገር ሆኖ ለሀገሩ የመቆም ተግባር በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር፣ ትውልድን የሚያኮራ ታላቅ ገድል ነው። ለዚህም ነው እስከ የተ.መ.ድ ፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ተከሰን በድል የወጣነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያዊ “ዓባይ የኔ ነው!” በሚል በባለቤትነት እየገነባው ያለ የግንባታውን ሂደት ለማየት የሚመኘው ግድብ ነው። በዚህ የተነሳ ቦታው ከመሃል ሀገር እጅግ ርቀት ቢኖረውም ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ እና ምስራቅ ጫፍ ተነስተው በርካታ ዜጎች በቡድን እና በግል ጭምር ግድቡን ጎብኝተውታል። ዲያስፖራዎችም ባገኙት አጋጣሚ በቡድን ሆነው ግድቡን ጎብኝተዋል።

ከኢትዮጵያውያንም በዘለለ የግድቡ ዜና በመላው ዓለም የተናኘ በመሆኑ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ የልዑካን ብድኖች እና መሪዎች ግድቡ ድረስ በመሄድ አይተዋል፣ ተደንቀዋል፣ ከመደነቅም በላይ ግድቡ የማይቀለበስ እና ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የተሰለፉበት፣ ለሀገሪቱ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል። በዚህም ያለ ምንም ዓለም አቀፍ ድጋፍ ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ እና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ማደግ እንደምትችል ግድቡ ራሱ መስክሯል።

አዲስ ዘመን፦ የሕዳሴው ግድብ ከጅምሩ ጀምሮ አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ የነበሩ ውጣውረዶችን እንዴት ይገልጿቸዋል?

ወይዘሮ ፍቅርተ፦ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከመጀመሩ በፊትም ከተጀመረ በኋላም አሁን ላይ ሆኖም ብዙ ውጣውረዶች ይገጥማሉ፤ በተለይም ግድቡ የብዙ አካላት ትኩረት ያለበት በመሆኑ ችግሮቹም በዚያው ልክ በርካታ ናቸው ማለት ይቻላል። ከውጣ ውረዶቹ መካከልም አንዱ የፕሮጀክት ግንባታው ሲሆን ሌላው ደግሞ የሕዝበ ተሳትፎ ነው። ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱም ብዙ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው የሕዝብ ተሳትፎው ላይ በመሆኑ እሱን መናገር ይቻላል።

እንግዲህ በሕዝብ ተሳትፎው በኩል የነበሩ ችግሮች በተለይም የግድቡ ሥራ ተጓቶ በነበረባቸው ጊዜያቶች ከፍተኛ የሆነ የእምነት መሸርሸር በኅብረተሰቡ ውስጥ ተከስቶ ነበር። በሚገርም ሁኔታ ግን እንዲህ ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙም ሕዝቡ ተስፋ ሳይቆርጥ ድጋፉን ያደርግ ነበር።

የግድቡ ግንባታ በሚያጋጥሙት ውጣውረዶች ላይ በተለያየ ጊዜ ግምገማዎች ይደረጋሉ? ምን አጋጠመ? እንዴትስ ነው ሊፈታ የሚገባው? የትኞቹስ ጠንካራ ጎን ነበሩ? በምን መልክስ ቢቀጥሉ ይሻላል? የሚለውም ሲታይ ቆይቷል። የሚተላለፉ ውሳኔዎችም በአግባቡ ታይተው ወደ ትክክለኛ መንገዳቸው እስከሚመጡ ድረስም በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። እኛ እንደ ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት እስከ አሁን ድረስ ምን ተሠራ? ምን ዓይነት መሰናክሎች አጋጥመው እንዴት ታለፉ? ብሎም የትኞቹ ጠንካራ ጎን ነበሩ? የሚለውን የመረጃ ማጥራት ሥራዎችን ስንሠራ ቆይተናል።

ይህንን የመረጃ ማጠናቀር ሥራ ሠርተን ከአጠናቀቅን በኋላም የሚመለከታቸው አካላት በአንድነት ሆነን በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን በመጥራት ሕዝቡ ጥርት ያለ መረጃን ከምንጩ ያገኝ ዘንድ መግለጫ የተሰጠበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህ ደግሞ በመላው ሀገሪቱ ላሉ ኢትዮጵያውያን ተደራሽ ይሆን ዘንድ በሁሉም ቋንቋዎች እንዲሠራ ሆኖም ተሠራጭቷል።

አዲስ ዘመን፦ ሕዳሴ ግድብ በሀገር ውስጥም በውጭም የተለያዩ ጫናዎች የነበሩበት እንደሆነ ይታወቃልና፤ እንደው እነዚህ ጫናዎች የታለፉበት መንገድ ምን መልክ አለው?

ወይዘሮ ፍቅርተ፦ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ያለው የውጭ ጫና ከመጀመሩም በፊት እየተሠራም አሁንም ወደ መጠናቀቁ ላይ ደርሶ እንኳን የቆመ አይደለም። በተለያዩ መንገዶችና ሁኔታዎች ጫናዎች ይደረጋሉ። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተፈጥሮ ሀብቷን ተጠቅማ በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ካሉ ወንድሞቻችን እኩል ድምጻችን እንዲሰማና አቅማችን የጠነከረ እንዲሆን የማይፈልጉ አካላት ስላሉ ነው። እነዚህ አካላት ደግሞ ሥራውን በሚችሉት ሁሉ አደናቅፈው ሀገራችን ሁሌም በረሃብ በችግርና በድርቅ በልመና ብቻ እንድትኖርም ይፈልጋሉ።

ነገር ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ እነዚህ ኃይላት ግድቡን በምን አቅማቸው ይጀምሩታል ብለው ሲያስቡ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ግድቡ መገንባት በማንም ላይ ችግር እንደማያመጣ እንደውም ተያይዞ ለማደግ በር ከፋች መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ለማረጋገጥ ሞክሯል።

እነዚህ አካላት አሉን ብለው ከሚሏቸው ቅሬታዎች መካከል ደግሞ መሬቱ ይሸረሸራል፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰት ግድቡ ሊደረመስ ይችላል፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ የውሃ መጥለቅለቅ ያጋጥመናል እያሉ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮችን ያነሳሉ፤ ውሃውን ገድባችሁ ድርቅ ልታመጡብን ነው ይላሉ፤ ይህንን ግን እንደ ሀገር በባለሙያ እያስተነተንን ውሃው ኤሌክትሪክ ካመነጨ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደማይቀር በማስረዳት ብዙ መንገዶች ታልፈዋል።

ይህም ቢሆን ግን ሥራውን የማደናቀፉ ሂደት መሻሻልን ከማሳየት ይልቅ እየተባባሰ ነበር የሄደው፤ የተፈጥሮ ሀብቴን ላልማ ማለት እንደ ትልቅ ወንጀል ተቆጥሮ እስከ ጸጥታው ምክር ቤት ድረስ የደረሰም ጉዳይ ሆኗል። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን በጣም የሚገርመው የሕዝቡ ምላሽ አለመቀነሱ ነው። እንደውም እንደዚህ ዓይነት ክሶች ሲበዙ ጫጫታዎች ሲመጡ ሕዝቡ አንድነቱን እያጠናከረ ለግድቡ ግንባታም የሚሰጠውን ድጋፍና ትኩረት ከነበረው እየጨመረ ሲሄድ ነው ያየነው።

በመሆኑም ሕዝብና መንግሥት በሕብረትና በአንድነት በመቆማቸው ዛሬ ላይ ያለበት ደረጃ ለመድረስ ችሏል። እዚህ ላይ ግን የግድብ ግንባታው የውጭ ኃይላት ተጽዕኖ ብቻ ሳይሆን ያለበት አንዳንድ በሀገር ውስጥ ያሉ ቡድኖች የፖለቲካቸው መጠቀሚያም ሲያደርጉት ይስተዋላል። ይህም ቢሆን ግን ሰፊው ሕዝብ መሐረቡን ፈቶ ኪሱን አራቁቶ እዚህ ያደረሰው በመሆኑ እስከ አሁን ለችግር አልተበገረም። ወደፊትም የሚቀጥለው ይሄው ነው።

አዲስ ዘመን፦ የዓባይ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዐሻራ ያረፈበት የጋራ ውጤት እንደመሆኑ በቀጣይ ሕብረ ብሔራዊነትን ከማጠናከር አንጻር እንዴት ይታያል?

ወይዘሮ ፍቅርተ፦ በመሠረቱ ኅብረተሰብ ያልተሳተፈበት የልማት ሥራ ውጤታማ ይሆናል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። ይብዛም ይነስም ኅብረተሰቡ ዐሻራውን ያኖረበት የእኔ ነው ብሎ ያመነበት የልማት ሥራ ውጤቱ አመርቂ ነው። እንደ አጋጣሚ ወይም ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ የሕዳሴው ግድብ በራሳችን አቅም የሠራነው ከሕፃን እስከ አዋቂ ከደሃ እስከ ሀብታም ከምሁራን እስከ ነጋዴ እንዲሁም ሰፊ አርሶ አደር ጭምር የአቅሙን የዋጣበት፤ ያዋጣበት ብቻም ሳይሆን በትኩረት የሚጠብቀው ሥራ ነው።

እንደ ሀገርም ይህ ፕሮጀክት የይቻላል መንፈስን የፈጠረ እና አቅምን ካሰባሰቡ ብዙ ነገሮችን መሥራት እንደሚቻል ያሳየ ብሎም ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎችን ለመሥራት መነሳሳትን የፈጠረም ነው።

በመሆኑም ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ እስኪመረቅ ድረስ የነበረው አንድነት እና ሕብረ ብሔራዊነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ለወዳጆቻችን ጥንካሬና ውጤታችንን ማሳየት ፤ በጎ ሳይመኙለን ለቆዩትም አንድ ከሆንን ምንም የሚያሸንፈን ነገር እንደሌለ ማሳያ ይሆነናል።

አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ የግድብ ግንባታ ሥራው በምን ያህል መቶኛ ተጠናቅቋል ማለት ይቻላል?

ወይዘሮ ፍቅርተ፦ አሁን ላይ የግድብ ግንባታ ሥራ 98 በመቶ ገደማ ተጠናቋል። እንግዲህ የግድቡ ግንባታ ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ የነቃ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ታክሎበት በከፍተኛ የመንግሥት ትኩረት ተሠርቶ የኮንስትራክሽን ሥራው ተጠናቋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የኮርቻሰ ግድቡና የዋናው ግድብ ግንባታም ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል። በሚቀጥለው አዲስ ዓመት 2018 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ መንግሥትና ሕዝብ በጋራ ሪቫን እንቆርጣለን ብለን እየጠበቅን ነው።

ከዚህ ቀጥሎ የሚሆነው የተርባይንና የጀነሬተሮች ተከላ ሥራ ይሆናል ማለት ነው። ይህም ቢሆን ግን የእኛ የትኩረት አቅጣጫ የግድቡ ግንባታ መጠናቀቁ ላይ ነው። ምክንያቱም እኛ የሚያሳስበን ወይም የሚያስፈልገን ለኤሌክትሪክ ማመንጫው የምንይዘው ውሃ ነው። ይህንን ውሃ በሚፈለገው ልክ መያዝ የሚያስችል የግድብ ግንባታ ሥራ አጠናቀናል። ይህንን በዚህ ከቋጨን ከስር ከስር የሚሠሩ የሚጠናቀቁ ሥራዎችም ደረጃ በደረጃ የሚከናወኑ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ የግድብ ሥራው ተጠናቆም በቀጣይ ዓመትም ሪቫን እንቆርጣለን ተብሏልና፤ እስከዚያው ድረስ የሕዝቡ ተሳትፎ ምን መምሰል አለበት ይላሉ?

ወይዘሮ ፍቅርተ፦ አሁን ላይ በመላው ሀገሪቱ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ባሉባቸው የዓለም ሀገራት በሙሉ በኅብረተሰብ ተሳትፎ ዙሪያ ትልቅ ንቅናቄ ተደርጎ እየተሠራ ነው። ባሳለፍነው ዘጠኝ ወር ወደ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ሕዝቡ ለግድቡ አዋጥቷል። ይህ ቀላል ነገር አይደለም። ሕዝቡ አሁንም ለግድቡ ያለው ስሜት የጋለ ነው። የጀመረውንም ለመጨረስ ከፍተኛ ቁርጠኝነት እያሳየ ነው። ለልጆቹ ለልጅ ልጆቹ ታሪክ አስቀምጦ ለማለፍ በብዙ መጠን የቦንድ ግዢ እያደረገ ነው። ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱም በከፍተኛ ትኩረት እየሠራ ያለው ይህንኑ ነው። መገናኛ ብዙሃኖችም ጉዳዩን ቅድሚያ እየሰጡ በብዙ እያገዙ ነው። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

አዲስ ዘመን ፦ በመጨረሻም ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለዎት?

ወይዘሮ ፍቅርተ፦ እንግዲህ ይህ ግድብ ከሰንደቅ ዓላማችን ቀጥሎ መጠሪያችን ነው። ይህ እንዲሆን ያደረገ መንግሥት ምስጋና ይገባዋል። ምክንያቱም በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የነበሩ መሰናክሎች ቀላል አልነበሩም። ለዚህ በመብቃታችን ምስጋና ያስፈልጋል።

ከሁሉ በላይ ግን ሕዝቡ ካለው ሳይሆን ከሌለው ላይ ነገ ልጆቼ የልጅ ልጆቼ ብርሃን ይዩ ሀገሬ ከምትታወቅበት የድህነት ስሟ ትላቀቅ ብሎ ላለፉት 14 ዓመታት ቦንድ በመግዛት በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን በማድረግ ላሳየው ትብብር በፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ስም ማመስገን ይገባል።

ሚዲያውም ቢሆን ያለፉትን 14 ዓመታት ሳይሰለች አጀንዳ አድርጎ ከፊት አስቀድሞ ሕዝቡ ስለ ግድቡ በዓይኑ እንዲያይ፣ በጆሮው እንዲሰማ፣ ተጽፎለትም ለነገ ታሪክ እንዲያቆይ ያደረገው ጥረት ቀላል አይደለም። ለዚህም ምስጋና ያስፈልጋል።

በፕሮጀክቱ ላይ ሌሊት ተቀን የሚለፉ ለመደራደር ሀገር ከሀገር ሲሄዱ ለነበሩ በጠቅላላው ይህ ፕሮጀክት ተጀምሮ እዚህ እስኪደርስ ድረስ በተለያዩ መንገዶች ድጋፋቸውን ያሳዩ ሁሉ ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል።

ይህ ድጋፍ ግን አሁንም ግድቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብቶ የምንፈልገውን ውጤት እስከምናገኝ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ

ወይዘሮ ፍቅርተ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You