
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሚያባርሯቸውን ስደተኞች ለመቀበል ከአሜሪካ ጋር “የመጀመሪያ ደረጃ” ውይይት ላይ መሆኗን ሩዋንዳ አስታወቀች። የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቪየር ንዱንጊሪዬ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም ሩዋንዳ ከዩናይትድ ኪንግደም የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ውይይት ስታደርግ ስለነበር አሁን ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ውይይት እንግዳ ነገር አይደለም ነው ያሉት።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ወር ባደረጉት ንግግር አሜሪካ ሕገ ወጥ ስደተኞችን የምታቆይበት ሀገራት እየፈለገች መሆኗን ተናግረው ነበር። ዩናይትድ ኪንግደም ወደ ሩዋንዳ ስደተኞችን ለመላክ ያደረገችው ሙከራ በፍርድ ቤት ጥያቄ ስለተነሳበት የሰር ኪር ስታርመር ሌበር ፓርቲ ምርጫ ካሸነፈ በኋላ ዕቅዱ ሳይሳካ ቀርቷል።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቪየር ንዱንጊሪዬ በቴሌቪዥን ቀርበው እንዳሉት፤ መንግሥታቸው “በመላው ዓለም ችግር ለሚገጥማቸው ስደተኞች ሁለተኛ ዕድል መስጠት” ይፈልጋል። ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ውይይት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደሆነ እና ውጤቱን ለመተንበይ እንደማይቻል አመልክተዋል። ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቃል እንደገቡት፣ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአሜሪካ ማባረርን ዋነኛ የአስተዳደራቸው ትኩረት አድርገውታል።
ከወራት በፊት ኤል ሳልቫዶር አሜሪካውያን ዜጎችን ጨምሮ ከአሜሪካ የሚባረሩ ወንጀለኞችን በግዙፍ እስር ቤት ለማቆየት ጥያቄ አቅርባ ነበር። የኤል ሳልቫዶር ፕሬዚደንት ናይብ ቡኬሌ እንዳሉት ለዚህ አገልግሎት ሀገራቸው የሚከፈላት ይሆናል። ፓናማ እና ኮስታ ሪካም ከአሜሪካ የተባረሩ ስደተኞችን ተቀብለዋል። ባለፈው ሳምንት ስማቸው ያልተጠቀሰ የሩዋንዳ ባለሥልጣን ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከአንድ ወር በፊት ኢራቃዊ ስደተኛን መቀበላቸው ይታወሳል።
እኚሁ ባለሥልጣን ከአሜሪካ ጋር ውይይት የተጀመረው ትራምፕ ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ መሆኑን ጠቁመዋል። ሩዋንዳ በሠብዓዊ መብት አያያዝ ትችት ይሰነዘርባታል። ወደ ሩዋንዳ የሚወሰዱ ስደተኞች ወደ መጡበት ሀገር በግዳጅ እንደሚመለሱ እና ለእንግልት እንደሚዳረጉም የመብት ተሟጋቾች ሲናገሩ ቆይተዋል። ሩዋንዳ ግን ለስደተኞች ደህንነቷ የተጠበቀ ሀገር መሆኗን በተደጋጋሚ ትገልጻለች ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም