የሀገር ውስጥ ቡና ዋጋ እንዴት ይረጋጋ?

ናን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊና ተወዳዳሪ የሆነውን አረቢካ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ትታወቃለች:: ኢትዮጵያ በዚህ ቡናዋ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት በቡና ምርቷ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ተፈላጊ ሆናለች::

በርካታ የዓለም ሀገራትም የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም አረቢካ ቡና እንደማጣፈጫ ቅመም ይጠቀሙታል:: ይህንኑ ቡና ከሌሎች ቡናዎች ጋር ቀላቅለው በስማቸው ለገበያ እያቀረቡ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ::

በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያ እጅግ ተፈላጊና ተወዳዳሪ የሆነው የኢትዮጵያ አረቢካ ቡና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነ ይታወቃል፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ቡና በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በጥራት የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ ይጠቁማል::

መረጃው እንደሚያመላክተው፤ በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ጊዜ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ የሚለውን የዓለም የቡና ዋጋን በመቋቋም ዓለም አቀፉ ገበያ በሚፈልገው መጠንና ጥራት ቡና ለማቅረብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ትገኛለች::

ከሀገር ውስጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭና ተፈላጊ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ዋልታነቱን እያረጋገጠ ለመሆኑም በርካታ ማሳያዎች አሉ:: ለአብነትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቡና ወጪ ንግድ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ በመሆኑ ከቡና ወጪ ንግድ ቢሊዮን ዶላሮችን ማግኘት ተችሏል:: በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ዓመታዊ የቡና ምርት መጠን ከነበረበት 500 ሺህ ቶን በእጥፍ ማደግ መቻሉም ዘርፉን ለማሳደግ በተሠሩ ሥራዎች የተመዘገበ ውጤት እንደሆነ የባለሥልጣኑ መረጃ ያመላክታል::

በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣው የኢትዮጵያ ቡና በሀገር ውስጥም ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል:: በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ እየታየ ያለው የቡና ዋጋ ጭማሪ ከምን የመጣ እንደሆነ በዕለቱ ዝግጅታችን ለማየት ወደናል:: አሁን እየታየ ያለው የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ ጭማሪ መንስኤና መፍትሔውን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን እና ከምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርገናል::

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር፤ የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ሲጨምር ሀገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪም በዚያ ልክ ከፍ እንደሚል ይናገራሉ፤ በሀገር ውስጥ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ግን መረጋጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል::

አቶ ሻፊ እንዳሉት፤ የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ መጨመሩ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዓይነተኛ ድርሻ አለው:: ነገር ግን በሀገር ውስጥ እየታየ ያለውን የቡና ዋጋ መናር ጊዜያዊና ሊረጋጋ የሚችል ነው ሲሉ ገልጸውታል:: የቡና ወጪ ንግድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ እንደሆነና ሀገሪቱም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች መሆኑን ተናግረዋል::

የኢትዮጵያ ቡና በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ፣ ተመራጭና ተፈላጊነቱ ጨምሯል:: በመሆኑም በሀገር ውስጥ እየታየ ላለው የቡና ዋጋ ጭማሪ በሀገር ውስጥ ያለው የቡና ጠጪ ቁጥር ከፍተኛ ድርሻ አለው:: ለአብነትም በሀገር ውስጥ ከሚመረተው የቡና ምርት 50 በመቶ ያህሉ ቡና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እየዋለ ይገኛል:: በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ እየታየ ያለው የቡና ዋጋ መናር ዓለም አቀፉ ገበያ እያሳደረ ካለው ተጽዕኖ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ያለው ፍላጎትም ዓይነተኛ ድርሻ አለው::

ለኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቡና በሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ ላይ እያሳየ ያለው ጭማሪ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው:: ይህም ጊዜያዊና በቅርቡ ሊፈታ የሚችል እንደሆነ አቶ ሻፊ አብራርተዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ አንደኛውና ዋናው ምክንያት በዓለም አቀፉ ገበያ በነበረው ከፍተኛ የቡና ፍላጎት ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለዓለም ገበያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ማቅረቧ ነው::

ሁለተኛው ምክንያት ወቅቱ አዲስ የቡና ምርት የገባበትና ለዓለም ገበያ እየተዘጋጀ ያለበት በመሆኑ ነው:: ይህም ሲባል አዲሱ የቡና ምርት ተዘጋጅቶ ደረጃ እስኪወጣለት ለዓለም ገበያ ይዘጋጃል:: አዲሱ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ተዘጋጅቶ ደረጃ ለማውጣት ጊዜ ይፈልጋል:: ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ቡና ደግሞ ለዓለም አቀፍ ገበያ ተዘጋጅቶ የሚተርፈው ቡና በመሆኑ ለዝግጅት ጊዜ ይፈልጋል ይህም ሌላኛው ምክንያት ነው::

‹‹ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ቡና በተለምዶ ደረጃው ዝቅ ያለ ነው ይባል እንጂ ጥሩ ቡና ነው›› ያሉት አቶ ሻፊ፤ ዝቅተኛ የተባለውም ሌላ ስም ስለታጣላት እንደሆነ አመላክተዋል:: በአሁኑ ወቅትም ይኸው ዝቅተኛ የተባለውና ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውለው ቡና በዝግጅት ላይ በመሆኑ ወደ ገበያ አልወጣም ብለዋል:: በዚህ ምክንያት በሀገር ውስጥ ገበያ የተፈጠረው የቡና እጥረት የቡና ዋጋ ጭማሪ እንዲያሳይ አድርጓል:: ከእነዚህ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች በተጨማሪ የዓለም የገበያ ፍላጎትና ዋጋም በሀገር ውስጥ ገበያው ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው፣ አሁን እየታየ ያለው የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ ጭማሪ ጊዜያዊና በቅርቡ ሊፈታ እንደሚችል አመላክተዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት አዲሱ የቡና ምርት ተዘጋጅቶ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ አስፈላጊው የዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናቅቆ ቡናው ለውጭ ገበያ ሲዘጋጅ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውለው ዝቅተኛ የተባለው ቡና ለሀገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል:: በዚህ ጊዜ የቡና ዋጋ ወደ ቦታው የሚመለስ እንደሆነ ተናግረዋል::

በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬዘር ጥላሁን በበኩላቸው፤ በሀገር ውስጥ አሁን እየታየ ባለው በቡና ዋጋ ጭማሪ ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ የቡና ዋጋ ሲጨምር ሰዎች ቡናን ትተው ወደ ሻይ አልያም ወደ ሌሎች አማራጮች ይሄዳሉ:: ያን ጊዜ ቡና ጭራሽ ከገበያ ሊወጣ ይችላል:: ስለዚህ የቡና ዋጋ ሲጨምር ደንበኞች እስከማይሸሹበት ደረጃ ሊሆን ይገባል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል::

ዛሬ ላይ አንድ ኪሎ ቡና እስከ አንድ ሺ ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ አንድ ሲኒ ቡና ደግሞ ከአምስትና አስር ብር ተነስቶ 25 እና ከዛም በላይ ሲሉም ይጠቅሳሉ::

የቡና ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ ሰዎች ከቡና የሚያገኙትን ጥቅም ከሻይ ወይም ከሌላ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ቡናን ሊረሱት ይችላሉ ሲሉ አመልክተው፣ ምክንያቱም ቡና ሲቀር ሊቀር የሚችል እንጂ የምግብና የውሃ ወይም ለሕይወት የግድ የምንለው ነገር አይደለም ብለዋል::

ሰዎች ቡናን ‹‹ጥንቅር ብሎ ቢቀርስ›› ብለው ቢተውት በቡና ገበያው ላይ አደገኛ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስረድተው፤ ይህን ከግምት ያስገባ የቡና ዋጋ በሀገር ውስጥ ገበያ ሊኖር እንደሚገባ አመልክተዋል::

በተለይም አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ቡና መጠጣት ቅንጦት ይሆናል ያሉት አቶ ፍሬዘር፤ ሸማቾች የሚሰጡት አጸፋዊ ምላሽ ገበያው ላይ አደገኛ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ሰዎች የኑሮ ጫናዎችን ለመቋቋም ሲሉ ቡና መጠጣት ሊያቆሙ ይችላሉ:: በዚህ ጊዜ አምራችና ነጋዴው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል:: ስለዚህ ዋጋ መጨመር ብቻ ሳይሆን ነባራዊ ሁኔታውን ማገናዘብና የትርፍ ህዳጉን /ማርጂኑ/ን መጠበቅ ያስፈልጋል:: ለአብነትም አንድ ሲኒ ቡና ከአስር ብር ተነስቶ 15፣ 20ና 25 ብር ሲገባ ደንበኛ ይቀንሳል:: 30 ብር ሲገባ ደግሞ ደንበኛው ከመቀነስ አልፎ ጨርሶ ይጠፋል:: ይህም በቡና ገበያው ላይ አደገኛ ሁኔታን ይፈጥራል:: ስለዚህ ዋጋ ትመና ላይ የደንበኞችን ወይም የተጠቃሚዎችን አጸፋዊ ምላሽ ከግምት ማስገባት የግድ ነው በማለት አስገንዝበዋል::

እንደ መድኃኒት ያሉና ለሕይወት የግድ አስፈላጊ በሆኑ ምርቶች ላይ ዋጋ ሲጨመር ተጠቃሚው የግድ ስለሚያስፈልገው እስከቻለ ድረስ ዋጋ ጨምሮ ለመግዛት ይታገላል:: ቡና እንደ መድኃኒትና ለሕይወት አስፈላጊ እንደሆኑ ምግብና መጠጦች ባለመሆኑ ተጠቃሚው የተወሰነ ጊዜ ጨምሮ ሊገዛ ይችላል:: ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ‹‹ቢቀርስ›› ብሎ እርግፍ አድርጎ ሊተወው የሚችል መሆኑን ተናግረው፣ በሀገር ውስጥ ያለው የቡና ዋጋ ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ አመላክተዋል::

አቶ ሻፊ እንዳስታወቁት፤ የዋጋ ንረት የሚከሰተው አቅርቦትና ፍላጎት መጣጣም ሳይችል ሲቀር ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ አሁን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውለው ቡና በጊዜውና በሚፈለገው መጠን ገበያ ውስጥ አልገባም:: ይህ ቡና ተዘጋጅቶ ወደ ገበያው ሲገባ የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ የሚቀንስ ይሆናል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው ቡና ለውጭ ገበያ ተዘጋጅቶ ሲያልቅ የሚቀረው ተረፈ ምርት ነው:: ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበው ቡና ከኤክስፖርት የተረፈ ምርት ወይም በደረጃው ዝቅተኛ ነው ይባል እንጂ የተሻለና ጥራት ያለው ቡና እንደሆነም አቶ ሻፊ ተናግረዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ቡና ገዢ ሀገራት ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ወይም ተረፈ ምርቱን ጭምር የመግዛት ፍላጎት እያሳዩ ነው:: ይህም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳጅ፣ ተፈላጊና ተወዳዳሪ መሆኑን ያሳያል::

ስለዚህ የኢትዮጵያ ቡና በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ያለውን ተቀባይነት ማስቀጠል ይገባል:: በተለይም ዓለም አቀፍ ገበያው በሚፈልገው መንገድ ቡናን ማዘጋጀት የግድ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ቡናን በብዛትና በጥራት በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያለውን የቡና ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው::

ዓለም አቀፍ ገበያው በሚፈልገው መጠንና ጥራት ልክ ተደራሽ ለመሆን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ጥራት ላይ በመሥራት ሃምሳ ሃምሳ የሆነውን የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያን ማርካት የግድ ነው ያሉት አቶ ሻፊ፤ ለዚህም የምርት ጥራትን ማስጠበቅ አንደኛው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል:: የግብይት ዘርፉን ማዘመንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዲሁም እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ላይም ትኩረት ተሰጥቷል ሲሉ ጠቁመው፤ እነዚህንና መሰል ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ሀገሪቷ ከቡናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘት እንደሚቻል አመልክተዋል።

ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር ትርጉም ያለው ሥራ እየተሠራ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተነሳሽነት ተጠናክሮ በቀጠለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ስምንት ቢሊዮን የቡና ችግኞች መተከላቸውን ለአብነት አስታውቀዋል:: እነዚህ ችግኞችም በቀጣይ ሶስትና አራት ዓመታት ፍሬ መስጠት እንደሚጀምሩ ገልጸው፣ ይህ ሲሆን ምርትና ምርታማነቱም በዚያው ልክ እንደሚጨምር ተናግረዋል::

ሌላው በርካታ ያረጁ ቡናዎች መጎንደላቸውን የጠቀሱት አቶ ሻፊ፤ ይህም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል:: በተለይም ከ400 እስከ 500 ሄክታር በሚደርስ የቡና እርሻ ውስጥ የሚገኙ ከ70 እስከ 80 ዓመት ያስቆጠሩና ያረጁ ቡናዎች መጎንደላቸው ለምርትና ምርታማነት ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል:: በዚህም በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን የቡና ፍላጎት ማርካትና የሀገር ውስጥ ገበያንም ማረጋጋት እንደሚቻል አስታውቀዋል::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You