
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት አዲስ የሥራ ባሕል ማምጣት እየተቻለ ነው። ሳምንቱን በሙሉ ለሰባት ቀን እንዲሁም ሌት ተቀን ለሃያ አራት ሰዓት /በ7/24/ እየተካሄደ ባለው የኮሪዶር ልማት በርካታ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል። በግንባታ መጓተት ክፉኛ ስትቸገር በቆየች ሀገር በእዚህ አሠራር ግንባታን በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚቻል በተጨባጭ ታይቷል።
ከተማ አስተዳደሩ አሁን ደግሞ በንግዱ ዘርፍ የምሽት ንግድ እንዲካሄድ የሚያስችል አዋጅ አውጥቶ ወደ መተግበር ገብቷል። አዋጁ በሚገባ ይፈጸም ዘንድ የሚያስፈልጉ የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የትራንስፖርት፣ የጸጥታና ደህንነት የመንገድ መብራትና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት አስፈላጊነትን በማመንም በተቀናጀ አግባብ ወደ መሥራት ገብቷል።
ይህ እስከ ምሽት 3፡30 ድረስ እንዲካሄድ የሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ የንግዱ ማኅበረሰብ የሥራ ባሕሉን በመቀየር የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበትን፣ ሸማቹም በምሽት የግብይት አገልግሎት ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል ተብሎ ታምኖበታል። በምሽት ግብይቱ ነጋዴው ገቢውን እንደሚያሳደግ፣ መንግሥትም ከዘርፉ የሚያገኘው ገቢ እያደገ እንደሚመጣ ታሳቢ ተደርጓል። ተገልጋይም ከሥራው ወጥቶ በፈለገው የገበያ ማእከል ተገኝቶ የሚሸምትበት ሁኔታ ይፈጥርለታል።
ለእዚህ ግብይት መጀመርና በተሳለጠ መልኩ መቀጠል ግን የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የደህንነት መጠበቅ እንዲሁም የመንገድ መብራት ወሳኝ መሆናቸውን የንግዱ ማኅበረሰብ እየገለጸ ይገኛል። ከተማ አስተዳደሩም እነዚህ ችግሮች እንዳይከሰቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን እየገለጸ ነው። በተለይ ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክቷል።
የምሽት ንግዱን አስመልክቶ ሰሞኑን ያነጋገርናቸው የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ኃላፊ እንደገለጹት፤ የንግድ እንቅስቃሴው እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ተኩል እንዲቆይ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቱም እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ እንዲካሄድ የሚያስችል አዲስ አዋጅ ወጥቷል።
ኃላፊው ይህ የምሽት ንግድ ኬንያን በመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት ተለምዷል። በኢትዮጵያም በተለይ በምሥራቁ አካባቢ ድሬዳዋ እና ሀረርን በመሳሰሉት ከተሞች ይሠራበታል።
የምሽት ሥራ እንቅስቃሴው በመዲናዋ ተግባራዊ መሆኑ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሳደጉም በላይ የሥራ ሰዓቶችን በማራዘም ተጨማሪ ገቢ ማሳደግ ያስችላል። የገቢ ግብርንም እንደሚያሳድግ የንግድ ቢሮው መረጃ ያመላክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስመኘው ተሾመ፤ በመዲናዋ የምሽት የንግድ ሥራ ቁጥጥር ሂደት፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች፣ ተግዳሮቶች እና ምቹ ሁኔታዎችን በተመለከተ አብራርተውልናል።
አቶ ስመኘው እንዳብራሩት፤ አዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ እየተለወጠች ትገኛለች። ይህ ለውጥ በቀን የሚካሄደውን የንግድና አገልግሎት እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የምሽቱንም እያነቃቃው ነው። ምሽት ላይ ምርት እና አገልግሎት የሚሸጡትም ሆኑ የሚገዙት ተዋንያን በተሳለጠ ሁኔታ ግብይቱን እንዲያካሄዱና የነቃ እና የተሟሟቀ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማስቻል ያስፈልጋል።
ይህ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንዲጠናከር የምሽት ግብይት እስከ 3፡30 ድረስ እንዲካሄድ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋቱ ለንግድ እንቅስቃሴው ወይም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የራሱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አመላክተዋል። በመሆኑም የንግዱ ማኅበረሰብ እስከ ምሽት ሶስት ተኩል ድረስ ሁሉም የንግድ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም በንግድ አገልግሎት ሥራ ላይ የተሠማሩ አካላትም እንዲሁ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ደንብ ወጥቶ ለትግበራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው።
የመዲናዋ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትም እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ የሚሠራበት አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው፣ ይህም የምሽት የንግድ እንቅስቃሴው እንዲሳለጥ ለማድረግ የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው አመልክተዋል። ይህ የሚመለከታቸው አካላት ሥራውን በተቀናጀ መልኩ እንዲፈጽሙት ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ነው።
በመዲናዋ በምሽት የንግድ እንቅስቃሴ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን ከመከላከል ብሎም ሰላምና ፀጥታም ከማስጠበቅ አኳያ የደህንነት ችግር እንደማይገጥም ለማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ ዝግጅት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በከተማዋ ወደ ውስጥ ገባ ብለው በሚገኙ አካባቢዎችም እንዲሁ የመንገድ መብራትና የመሳሰሉት እንዲኖሩ በማድረግ በኩል የየአካባቢውም ማኅበረሰብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም እንቅስቃሴ የመብራት አገልግሎት እየተሟላ መሆኑን ጠቅሰዋል። በእነዚህ ዝግጅቶች በመታገዝ ወደ ሥራ መገባቱን አቶ ስመኘው አስታውቀዋል።
በመዲናዋ የሚታየው የምሽት የንግድ እንቅስቃሴ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በሂደት እየጎላ እንደሚሄድ አመልክተዋል። የዘርፍ ኃላፊው አሁን ባለው ሁኔታም የመዲናዋ የሥራ ባሕል እየቀየረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
“7/24 መሥራት አለብን” በሚለው አሠራር እንደ ከተማ የሚደረገው እንቅስቃሴ በስፋት እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል። ‹‹ከተማዋ እየተቀየረች ነው፤ ነጋዴውም ንግዱን በተሟላና ኅብረተሰቡን ተደራሽ በሚያደርግ መንገድ ማካሄድ አለበት›› ሲሉ ገልጸው፣ ይህ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ በመጣ ቁጥር ነጋዴውም ያተርፋል፤ በዚህም ግብርና ታክስ ይከፍላል። ይህም መልሶ ከተማዋን ለማልማትና ሀገርን ለማበልፀግ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል›› ብለዋል።
ኃላፊው እንዳብራሩት፤ በመዲናዋ በ119ኙም ወረዳዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች ቀደም ሲል አንስቶ እየተካሄደ ይገኛል። የምሽት ግብይቱም በሁሉም ወረዳዎች ከሞላ ጎደል የተጀመረ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ግን ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ ወይም ከወረዳ ወረዳ ልዩነት አለው።
እነዚህ ልዩነቶች የተፈጠሩት ከመንገድ፣ ከመብራትና ከመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች አለመሟላት ጋር በተያያዘ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ቢሆን እንደ ከተማ ግንዛቤውም እየተፈጠረ የበለጠ ወደ ተግባርም እየተገባ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከንግድ ቢሮ፣ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ ትራንስፖርት ቢሮ እንዲሁም በእነዚህ ተቋማት ስር ተጠሪ ከሆኑ ሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን በቅንጅት እና በመናበብ እየተሠራ መሆኑን አቶ ስመኘው ገልጸዋል። መንግሥት በመዲናዋ በርካታ የገበያ ማዕከላትን ለማስፋፋት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ ለእዚህም የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሸን ማዕከልን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚም እንዲሁ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸው አመልክተዋል።
በበለፀጉት ሀገራት ላይ እንደሚታየው በኮሪደር ልማቱ መሠረተ ልማቶች እየተስፋፉ ይገኛሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህም ለሀገሪቷም ተገቢና ሕጋዊ መሆኑን ተናግረዋል። ለንግዱ ሥራ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን፣ ይህንንም ኅብረተሰቡ እያደነቀ ብቻም ሳይሆን እየተጠቀመ መሆኑን አመልክተው፣ ይሄ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ፍላጎቱ እንዳለው ተናግረዋል። የዚህ ምቹ ሁኔታ መፈጠር ሠርቶ ለፈቶ ለሚያድረው ኅብረተሰብ ትልቅ እድል ይዞ እንደመጣም አስታውቀዋል።
የምሽት የንግድ እንቅስቃሴው ላይ በብዙ የዓለም ሀገራት የተለያዩ ተሞክሮዎች ቢኖሩም አብዛኛው የበለፀገ ማኅበረሰብ ክፍል ልምድ የሚያሳየው 7/24 በመሥራት ችግርን መሻገር መሆኑን አመልክተዋል። በሥራ ውጤት በማምጣት ከድህነት የመውጣት የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን ወደ ሀገሪቷ በማምጣት እየተሠራበት መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ አሠራር አሁን በመዲናዋ ቢጀመርም በሂደት ወደ ክልሎች እንደሚሰፋም ጠቁመዋል።
አቶ ስመኘው ለምሸት የንግድ ሥራው ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉትን አስመልክቶ ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እስከ አራት ሰዓት አገልግሎቱን እንዲሰጡ አቅጣጫ ተቀምጧል። ኅብረተሰቡ የትራንስፖርት አቅርቦት ያላገኘ ከሆነ በእዚህ በኩል አዋጁን በተሟላ ሁኔታ የማይፈፅሙ ሰዎች ካሉ በተቀመጠው አሠራር መሠረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል።
በተመሳሳይ የመንገድ መብራት የሌለበት በአካባቢው ከሌለም ችግሩ በሂደት ይፈታል። ያ አካባቢ መብራት ለሁልጊዜ አይኖረውም ማለት አይደለም። የደህንነትን ጉዳይ በተመለከተም እንዲሁ በሰላምና ፀጥታ ላይ የሚሠሩ አካላት አሉ።
በእዚህ በኩል አስቀድሞም የሰላም ሠራዊት ሥራ ውስጥ ገብቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሠራዊት ብዙ ችግሮችን ተጋፍጦ ያለፈ እና ኅብረተሰቡ የራሴ የሚለው አደረጃጀት መሆኑን ገልፀዋል። አሁንም በንቃት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከደህንነት አኳያ የሚፈጠር ችግር እንደሌለ አረጋግጠዋል። ከዚህ ያለፉ ችግሮች ከገጠሙም ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከዚያ ውጭ ቁጥጥር እና ክትትሉ በሁሉም አካባቢ ይካሄዳል፤ በተለይ በሁሉም የገበያ ማዕከላትና በነዳጅ ማደያዎች ላይ ቁጥጥር እና ክትትል የሚያደርጉ የንግድ ሬጉሌሽን ሥራ የሚሠሩ ሙያተኞች አሉ። በየደረጃውም ከ160 በላይ አመራሮች እንዲሁም በርካታ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው የቁጥጥር ሥራዎቹን ያደርጋሉ።
ቀደም ሲል ለምንም አገልግሎት የማይውሉ አካባቢዎችን መብራቶችንና እና በአንዳንድ መሠረተ ልማቶች በማሟላት የምሽት የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያግዙ ሥራዎች መሠራታቸውን አመላክተዋል። ለምሽት ንግድ ሥራው ምቹ ሁኔታዎችን ከሚያመቻቹት አንዱ የኮሪደር ልማቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የምሽት የንግድ እንቅስቃሴውም እየሰፋ መላ ሀገሪቱን ወደ ማሳተፍ እንዲሄድ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ከምሸት የንግድ እንቅስቃሴው መጀመር ጋር ተያይዞ ሊነሱ የሚችሉ የግልፅነት ጥያቄዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ እነዚህ ብዥታዎች ግልፅ እየሆኑ እንዲሁም ኅብረተሰቡም የምሽት ንግዱን አስፈላጊነት እየተረዳ በሄደ ቁጥር የበለጠ ተግባራዊ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታሰብም ተናግረዋል።
ለምሳሌ መብራት ያልተሟላ ከሆነ በሂደት ይሟላል ሲሉ ጠቅሰው፣ ምቹ መንገድ ከሌለም እየታየ በሂደት እንደሚፈታም ጠቁመዋል። አንድን ሥራ ጀምሮ ችግሮች ካሉም እየፈቱ መሄድ እንጂ መቃወም አያስፈልግም ሲሉም አስገንዝበዋል። ኅብረተሰቡ አዳዲስ ሃሳቦች በሚመጡት ጊዜ እየሞከረ፣ ውጤት ሲመጣም ውጤቱን ይበልጥ ለማሳደግ ሲሠራ ነገሮች እየተሟሉ እንደሚሄዱ ጠቁመዋል። ሥራ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል እምነታቸውን ይገልፃሉ።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ የትንሳኤ በዓል ገበያን አስመልክተው ባለፈው ሳምንት መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ የከተማዋን የንግድ እንቅስቃሴ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የደንብ ማስከበር ተቋማት የሚከታተሉት እንዳለ ሆኖ በንግድ በአዲስ ንግድ ቢሮ በኩል 160 አመራሮች፣ 2000 ያህል ባለሙያዎች ተመድበው የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
ሙያተኞቹ በገበያ ማዕከላት፣ በነፃ ገበያ እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ ገበያ ላይ የቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በዚህም ሁለት ዓይነት ቁጥጥር እንደሚደረግ ጠቁመው፣ መንግሥት በሚያስተዳድራቸው ቅዳሜና እሁድ ገበያዎች፣ ገበያ ማዕከላት እንዲሁም ባዛሮች ላይ ግብይቱ በተተመነ ዋጋ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በነፃ ገበያው ላይም እንዲሁ እያንዳንዱ ባለ ንግድ ተቋም ዋጋ ስለመለጠፉና በተለጠፈው ዋጋ እየተሸጠ ስለመሆኑ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። የንግድ ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ዋጋ የማይለጥፉትን ጨምሮ የንግድ ሕግ በተላለፉ 28 ሺህ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱንም ወይዘሮ ሀቢባ ገልጸዋል።
እስከ አሁን በተለይ በበዛሮች፣ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንዲሁም በገበያ ማዕከላት ላይ በልዩ ሁኔታ የተደረገውን ቁጥጥር ተከትሎ የገጠሙ ችግር እንደሌለም ገልጸዋል። ምርት በማከማቸት ወይም በመሰወር፣ ዋጋ ባለመለጠፍ መሥራት በሚያጋጥምበት ጊዜ የንግድ ፍቃድ የመሰረዝ፣ የማገድ፣ የተሰጠን የሥራ ቦታ እስከ መንጠቅ የደረሱ ርምጃዎች እንደሚወሰዱ አመላክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም