መሆን የምንፈልገውን ሆነን ለመገኘት!

የአንድ ሀገር ክብር በሁለንተናዊ መልኩ ጸንቶ የሚቆመው ዜጎች ለብሄራዊ ጥቅሞቻቸው ቅድሚያ ሰጥተው መንቀሳቀስ ሲችሉ ነው። ይህንን ማድረግ ያልቻለ ሕዝብ እና ሀገር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መውደቁ የማይቀር ነው። ውድቀቱ ሊያስከፍል የሚችለውም ዋጋ ትውልድ ተሻጋሪ ሊሆን እንደሚችል የብዙ ሀገራት እና ሕዝቦችን ተጨባጭ ታሪክ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል።

የሀገር ህልውና በአንድም ይሁን በሌላ የሀገርን ጥቅም አስጠብቆ ከመሄድ የሚመነጭ ነው ፤ ይህ በቀደመውም ዘመን ሆነ አሁን ላይ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የእያንዳንዱ ትውልድ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። የትውልዶችን የጠራ እውቀት፤ በእውቀት የሚገራ ራስን አሳልፎ የመስጠት ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው።

በተለይም አሁን ላይ ፤ የተለያዩ ፍላጎቶች ዓለምን እየናጡ ፤ ራስ ወዳድነት ፣ ዳተኝነት ፤ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት እና ዘረኝነት በተለያየ ቀለም ዓለምን እየተፈታተኑ ባሉበት ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ፤ ብሄራዊ ጥቅሞችን አስከብሮ ማስቀጠል የሚችል የትውልዶች መነቃቃት የግድ ነው ። ይህን መፍጠርም ለሀገራት ህልውና አልፋ እና ኦሜጋ ነው።

ለዚህ ደግሞ በማኅበረሰብ ውስጥ የሀገርን ጥቅም በሁለንተናዊ መልኩ ከግለሰብ እና ከቡድን ፍላጎት አልቆ ማየት የሚያስችል ዘመኑን የሚዋጅ የአስተሳሰብ ልእልና ፤ ለራስ ወዳድነት እና ለባንዳነት አጋልጦ የማይሰጥ የትውልዶች ግንባታ ይፈልጋል። ይህ ደግሞ የቤተሰብ፣ የሃይማኖት እና የትምህርት፣ የመንግሥት እና የሌሎች ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው።

የቀደሙት አባቶቻችን ለእውነታው ከነበራቸው ከፍ ያለ መረዳት ፤ ከዚያም በላይ እውነታው እንደ ሀገር ረጅሙን ዘመን ጸንተን እንድንኖር ያስቻለን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ፤ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ሠርተዋል። በትውልድ ግንባታ ውስጥ የሀገር ፍቅር እና ስለሀገር በሁለንተናዊ መልኩ መሰጠትን አስተምረዋል። ራሳቸውን በተግባር ሰጥተው ፤ እውነተኛ ምሳሌ ሆነውም አልፈዋል።

ዛሬ እንደ ሀገር ብሄራዊ ክብራችን ሆነ የክብራችን ምንጭ የሆነው ፣ ይህ አባቶቻችን በአስተምህሮ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ራሳቸውን ለሀገር ክብር /ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያስቀመጡልን የታሪክ ትርክት ነው ። ትርክቱ የብሄራዊ ማንነታችን ብቻ ሳይሆን የብዙ ትውልዶች መገለጫ ሆኖ ሀገረ -መንግሥቱን በማጽናት ዛሬ ላይ አድርሶታል።

የሀገራችን የረጅም ዘመን የሀገረመንግሥት ታሪክ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ፤ ከውስጥም ከውጪም ሰፊ መንገጫገጮች ውስጥ ያለፈ ነው ፣ ይህንን እስከ ዛሬ መሻገር የተቻለው እንደሀገር በትውልዶች ውስጥ በተገነባ የሀገር ፍቅር እና ሀገርን ከሁሉም በላይ የማስቀደም ሥራ ነው ። ለዚህ ተጨባጭ የአባቶች የመሥዋዕትነት የተጋድሎ ታሪክ ተጠቃሽ ናቸው።

የሀገር ክብር ብቻ ሳይሆን ፣ የሀገርን ውርደት የራስ አድርጎ የማየት ማህበራዊ ስሪታችን ፤ ትውልዶች በየዘመኑ ስለሀገር ራሳቸውን ሕያው መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ፤ ይህንንን የክብሮች ሁሉ ክብር አድርገው እንዲቀበሉ አስችሏቸዋል ። ዛሬም ያለው ትውልድ የዚህ እውነታ አካል በመሆኑ ተመሳሳይ መሥዋዕትነቶችን እየከፈለ እና አስደማሚ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። በዓባይ ግድብ፣ በስንዴ ልማት፣ በቱሪዝም መዳረሻዎች ማስፋፋት ወዘተ እየተመዘገቡ ፤ ድሎች የዚህ ትውልድ ዐሻራዎች እና የኢትዮጵያ ብልፅግና መሠረቶች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር በትውልድ መሥዋዕትነት የተጠበቀው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ነጻነት በኢኮኖሚ ሉዓላዊነትም ድል ማስመዝገቡን ቀጥሏል፡፡

ይኸው ብሔራዊ ጥቅሞችን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ፤ ራስን አሳልፎ የመስጠት ማኅበረሰባዊ ስሪታችን ባለፉት ቅርብ ዓመታት በነበሩ ትውልዶች ላይ በተጨባጭ ተስተውሏል። ለሀገር ጥቅም እና ክብር ሲሉ በክብር ያንቀላፉ እልፍ አእላፍ ፤ ለሰላምና ዕድገቷም የታተሩት ብዙዎች ናቸው፡፡ ራሳቸውን ለተመሳሳይ መሥዋዕትም ያዘጋጁ የአሁኑ ትውልድ አባላትን ስንመለከት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ መድረሱን ይመሰክራሉ። ይህ እውነታ እንደሀገር ያለንን ህልውና የሚያጸና ብቻ ሳይሆን እንደሀገር መሆን የምንፈልገውን ሆነን ለመገኘት ዋነኛ አቅማችን ነው።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You