ባለሥልጣኑ የትግራይ ልማት ማህበር ያደረገው ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው አስታወቀ

አዲስ አበባ፡- በቅርቡ የትግራይ ልማት ማህበር ያደረገው ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በደብዳቤ እንዳስታወቀው ፤ የትግራይ ልማት ማህበር (ትልማ) በሲቪል ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በመዝገብ ቁጥር 0462 ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ይታወቃል።

በትልማ 12ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 11132011 እንዲሁም ሌሎች መመሪያዎች የተቋሙ አሠራሮች ጋር በተፃረረ መልኩ ማህበሩ ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ይኖርበታል የሚለውን መርህ በተቃረነ መልኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጥሪ ተደርጎላቸው በድምፅ ሰጪ ጉባዔተኝነት የተሳተፉበት መሆኑን ደብዳቤው አመልክቶ ፤ 12ኛ የቦርድ ምርጫ ጋር በተያያዘ ማህበሩን የሚከፋፍል እና አደጋ የሚፈጥር እንዲሁም የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን እንዳይከናወን የሚያደርግ በመሆኑ በባለሥልጣኑ በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጿል።

በዚሁ መሠረትም 12ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በመቐለ ከተማ ከሚያዚያ 17 እስከ 19 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚያካሂድ በመግለፅ ተቋማችን በጉባዔው ላይ እንዲገኝ ትልማ ጥሪ ባቀረበው መሠረት ሁለት ተወካዮች መሳተፋቸው ይታወቃል ያለው ደብዳቤው፤ ተቋማችን በመወከል የተገኙት አመራሮች በውይይቶች ወቅት ለሚነሱ ድጋፍ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ሕግንና አሠራርን መሠረት በማድረግ ገንቢ ሃሳቦችን አጋርቷል ብሏል።

ሆኖም ጉባዔው ከተሳታፊዎች አጠራር ጀምሮ መሠረታዊ መስፈርቶችን ያላሟላ በመሆኑ መካሄድ የሌለበት እና መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ለትልማ አመራሮች እና ለጉባዔው ሃሳብ የቀረበ ቢሆንም እስከነ ችግሩ ጉባዔው መቀጠሉን ደብዳቤው አመልክቶ፤ የጠቅላላ ጉባዔው የመጨረሻ አጀንዳ የሆነው የሥራ አመራር ቦርድ አመራሮች ምርጫ በጉባዔተኛው በኩል መግባባት ያልተፈጠረበት፣ የጋራ ስምምነት ያልተደረሰበት ብሎም ተሳታፊዎች ባለመስማማት ጉባዔውን ጥለው የወጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል ሲል ገልጿል።

ባለሥልጣኑ የትልማ ጠቅላላ ጉባዔ በአጀንዳችን ዙሪያ ተገቢው ውይይት የሚደረግበት የጋራ ግንዛቤ እና መግባባት የሚፈጠርበት፣ የማህበሩ አንድነት የሚጠናከርበት እንዲሁም ማህበሩ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች አቅም የሚፈጠርበት መሆን እንዳለበት ፅኑ እምነት አለው ያለው ደብዳቤው፤ ይሁን እንጂ በእለቱ የተፈጠረው ሁኔታ ከጉባዔው የሚጠበቁ ውጤቶች እንዳይሳኩ በማድረግ ማህበሩ የተከፋፈለ እና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚገባው ልክ ማረጋገጥ የማይችል እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን አመልክቷል።

ከዚህ አኳያም የሥራ አመራር ቦርድ ምርጫ መስተካከል እና መታረም የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉ በማድረግ፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስተባብሮ ሌላ ጊዜ እንዲካሄድ አቅጣጫ በመስጠት ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ተግባራት በባለሥልጣኑ እውቅና የሌላቸው መሆኑን አሳውቋል።

የትልማ ጉባዔ የቦርድ ምርጫ ባልተለመደ መልኩ አባላት የተከፋፈሉበት እና ለማህበሩ አደጋ የሚፈጥር ሆኖ መከናወኑ ግርታን የሚፈጥር ጉዳይ መሆኑን ገልጿል፤ እስከ አሁን ሲያስተዳድሩ የነበሩ የቦርድ አመራሮች በባለሥልጣኑ በኩል እውቅና ያላቸው በመሆኑ ማበሩን የመምራት እና የማስተዳደር ሥራን እንዲያከናውኑ በደብዳቤው አስታውቋል።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You