
መላው ሕዝባችን ባደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል እና በከፈለው ከፍ ያለ መሥዋዕትነት ሀገራችን አሁን ላይ አስቸጋሪ የሚባሉ የለውጥ መንገጫገጮች ተሻግራ በተሻለ የለውጥ መንገድ ላይ ናት። እንደ ሀገር በለውጥ ማግስት ያሰብናቸውን ብሩህ ነገዎች እውን ለማድረግም ተስፋ ሰጪ ቁመና ላይ ትገኛለች።
ሀገራዊ ለውጡ እንደ ሀገር የሕዝባችንን ያደሩ ፣ የሰነበቱ እና ዘመናት ያስቆጠሩ ጥያቄዎች የፈጠሩት ከመሆኑ አኳያ ፣ ውስብስብ ጥያቄዎች ያዘለ ፤ የተዛቡ እና የሀሰት ትርክቶች የፈጠሯቸውን ግራ መጋባቶች እና ውዥንብሮች የገዘፉበት ፤ በብዙ መደበላለቅ ውስጥ የተከናወነ መሆኑ የለውጡ ተስፈኛ የሆነውን ሕዝባችንን እና የለውጥ ኃይሉን በብዙ ፈትኗል።
ከሁሉም በላይ የለውጡን ባህሪ እና ገፊ ምክንያቶች በአግባቡ መረዳት የተሳናቸው ኃይሎች፤ ለውጡን ለራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸሚያ ለማድረግ የሄዱበት ያልተገባ መንገድ ፤ በለውጥ ኃይሉ ውስጥ ሳይቀር ብዥታን ፈጥሯል። ያልተገቡ ጥያቄዎች እንዲነሱ እና ባልተገባ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙም ሙከራዎች ተደርገዋል።
በለውጡ ማግስት አደባባይ ወጥተው ለውጡን እንደ አንድ ታላቅ ሀገራዊ ብስራት አድርገው የቆጠሩ ፤ አደባባዮችን በእልልታ እና በሆይታ ያደመቁ አንዳንዶች ፤ ለውጡ ያሰቡትን ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒ የቆመ ግላዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ማስፈጸም የሚያስችል ባህሪ አለመላበሱን ሲረዱ ፤ ለውጡን በአደባባይ ከማውገዝ ጀምሮ በለውጡ ላይ ጠብመንጃ እስከ ማንሳት የዘለቀ የጥፋት መንገድ መርጠው ተጉዘዋል።
የለውጥ ኃይሉ በአንድ በኩል የለውጥ ወቅት ተገማች ችግሮችን ፤ በሌላ በኩል የለውጡ ገፊ ምክንያቶችን ባህሪ በመነሳት ለሕዝብ ጥያቄዎች ሰላማዊ እና ዘላቂ ምላሾችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለመስጠት ረጅም መንገድ ተጉዟል። ይህም ሆኖ ግን ለውጡ በፈተና ውስጥ ማለፍ ግድ ሆኖበታል።
መንግሥት የቀደሙ ችግሮችን በይቅርታ ለማለፍ የሄደበት መንገድ ፤ ስለ ሰላም የጸና አቋም ይዞ የሄደበት አዲስ የፖለቲካ እሳቤ በአንዳንዶች የአቅም ማነስ ተደርጎ መወሰዱ ፤ እንደሀገር ብዙ ዋጋ የከፈልንባቸው ግጭቶች ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል።
ለውጡ ከዋዜማው ጀምሮ ሕዝባችንን ለብዙ መስዋዕትነት ያነሳሳ ፤ ሕዝባዊ መሠረት ስለነበረው ፤ የለውጥ ኃይሉም ይዞት የተነሳው አዲስ የፖለቲካ እሳቤ ዘመኑን የሚዋጅ በመሆኑ ከብዙ መንገጫገጮች እና መንገዳገዶች በኋላ ለውጡ በሁለት እግሩ ጸንቶ የቆመበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀገር እና በሕዝባችን ላይ የተነገሩ ሟርቶች ከሟርትነት ሳያልፉ እንደ ሕዝብ አስቸጋሪውን የለውጥ ወቅት አልፈን ወደ ለውጥ ተስፋዎቻችን የሽግግር ምዕራፍ ደርሰናል ። እሁን እንደሀገር ከለውጥ ወቅት ስጋቶቻችን ወጥተን ተስፋዎቻችንን አሻግረን የምናይበት እና ለበለጠ ድል የምንተጋበት ወቅት ላይ ነን ።
በአስቸጋሪ ወቅቶች ችግሮችን በጽናት ተጋፍጠን ሀገርን እንደሀገር ማስቀጠል ፤ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻልንበት እውነታ እንደ ሕዝብ የለውጥ ተስፋችን የቱን ያህል አቅም ሆኖ እንዳሻገረን አመላካች ነው። በሌላ በኩል በችግሮች እና በሟርቶች ውስጥ ሆነን ተስፋዎቻችንን የሙጥኝ ስለማለታችን ማሳያ ነው።
አሁን ያ ድቅድቅ የሚመስለው በርግጥም ለብዙዎች ድቅድቅ ሆኖ የታየው የለውጥ ወቅት እንደ ሀገር ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን ቢያስከፍለንም፤ የብዙዎችን የፈኩ ፊቶች ቢያስጨፈግግም ፤ የብዙዎችን የተስፋ ዕልልታ ወደ ቁዘማ ቢለውጥም ፤ የብዙዎችን የለውጥ መነቃቃት ቢያደበዝዙም ተሻግረነዋል።
ከመሻገርም አልፈን የለውጥ ተስፋችንን በአግባቡ ማሰብ እና መያዝ በሚያስችል የተረጋጋ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ገብተናል ፤ በክፉ ቀናቶች የለውጥ ጉዟችን ተስፋ የሆኑ ስኬቶቻችንን እያጣጣምን በለውጡ ማግስት ተስፋ ያደረግናቸውን ብሩህ ነገዎች መሥራት የምንችልበትን የመረጋጋት እና የስክነት ምዕራፍ ውስጥ እየገባን ነው።
በብዙ መሥዋዕትነት እየተሸጋገርን ያለንበት የለውጥ ምዕራፍ ትናንት እንዳልነው ድህነትን ታሪክ በማድረግ ለራሳችን ሆነ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር መፍጠር የሚያስችል ነው። ነገዎቻችንን በጠራ አዕምሮ አቅደን የምንሠራበት ነው። ወደ ተሟላ ሀገራዊ መረጋጋት የምንገባበት ጅማሬም ነው!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም