የኮሪዶር ልማት ሥራው ፕሮጀክትን ጀምሮ በፍጥነት የመጨረስ ተሞክሮ የተገኘበት ነው

አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያካሂደው ኮሪዶር ልማት ሥራ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በፍጥነት የመጨረስ ልምድና በጋራ በመሥራት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ምርጥ ተሞክሮዎች የተገኙበት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች ከጋዜጣ ፕላስ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ከተማ ኮሪዶር ልማት ሥራ በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ የከተማዋን አገልግሎት ማሳለጥ፣ የትራፊክ አደጋን መቀነስ እና ለዘመናት የቆየውንና የተበላሸውን የከተማ ፍሳሽ አገልግሎት ማስተካከል ተጠቃሽ ናቸው።

አዲስ አበባ መተንፈሻ እያጣች ነበር ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በእዚህ የተነሳ ከተማዋን መልሶ ማደስ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል። የኮሪዶር ልማት ሥራው ከተማዋን መልሶ በማደስ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው፤ ከፓርኪንግ አገልግሎት፣ ከተርሚናሎች ጭምር አዲስ አሠራር የፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላም በኩል ቀደም ሲል ተቋማት ተቀናጅተው ስለማይሠሩ አንዱ ሲገነባ ሌላው ያፈርሳል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ የኮሪዶር ልማት ሥራው ይህንን ችግር የፈታ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኮሪዶር ልማት ሥራው ሲከናወን ሁሉንም ማህበረሰብ ክፍል ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዜጎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ መደረጉን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፤ የልማት ተነሺዎች እቃቸውን እንኳን እንዳይሸከሙ የሚያደርስላቸው ሠራተኛ ተመድቦ ዜጎች ሳይጉላሉ ወደ ቤታቸው የሚገቡበት ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል።

በሚሄዱበት ስፍራም መሠረተ ልማትን በማሟላት ልጆቻቸው በቅርብ ርቀት ትምህርት ቤት እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ የአውቶቡስ ማቆሚያ ጭምር ተነሺዎችን ታሳቢ በማድረግ መገንባቱን ጠቁመዋል።

ወርቁ ማሩ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You