የለውጡ ፍሬ ባለቤት ለመሆን!

የለውጥ መንገድ ከሁሉም በላይ የለውጥ ፍላጎትን መሸከም የሚያስችል የተለወጠ ማንነት የሚፈልግ ነው። በተለይም ሀገራዊ ለውጥ የብዙ ገፊ ምክንያቶች ውጤት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ባልተለወጠ ማኅበረሰባዊ ማንነት በለውጥ ውስጥ የሚነሱ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሻቶችን በቀላሉ እውን ማድረግ የሚችል አይሆንም ።

በተለይም እንደኛ ያሉ ተደጋጋሚ በሆኑ የለውጥ መንገዶች ውስጥ መግባት ችለው፤ ለውጡን በአግባቡ መግራት ባለመቻላቸው የክሽፈት ትርክት ባለቤት የሆኑ ሀገራት እና ሕዝቦች ፣ ስለለውጥ እና የለውጥ መሻቶችን በስኬት ለመውረስ በሚያስችሉ እውነታዎች ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ መጨበት ፣ ለውጥ በራሱ ከመሻት መነቃቃት ባለፈ ስክነት እና አስተውሎ መራመድን የሚጠይቅ ስለመሆኑም በቂ መረዳት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስድስት እና ሰባት አስርት ዓመታት የተለያዩ ተለውጦ የመለወጥ የለውጥ ዕድሎችን አግኝተናል፤ እነዚህን ዕድሎች ተጨባጭ ለማድረግ የሄድንባቸው መንገዶች ትናንቶችን ባልተሻገሩ፤ የትናንት ጥላ በሆኑ ፖለቲካዊ፣ አኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እሳቤዎች የተገዙ በመሆናቸው ብዙ ዋጋ አስከፍለውን ያሉ ስኬት አልፈዋል።

አንድም የለውጦቹን ገፊ ምክንያቶችን በአግባቡ ለመረዳት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ስክነት ማጣታችን ፣ለውጥን ከስሜት ባለፈ ከሚጨበጥ ሀገራዊ ተስፋ ጋር አስተሳስሮ ማየት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ዝግጁነት አለመፍጠራችን ለቀደሙ የለውጥ ክሽፈቶቻችን ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ይታመናል።

ይህም ሀገራዊ /ማኅበረሰባዊ የለውጥ መነቃቃቶችን ለግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎት ማስፈጸሚያ አድርጎ ማየትን ፈጥሯል፤ ይህም በራሱ ተነጋግሮ መደማመጥን ፣ ተስማምቶ ለሕዝቦች የለውጥ መነሳሳት ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሀገራዊ የፖለቲካ አውድ እንዳንፈጥር አድርጎናል።

ይህም ሆኖ፤ለውጥ በባህሪው በማይቆም የማኅበረሰብ ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ፤ዛሬ ላይ ተጨማሪ የለውጥ ዕድል አግኝተን በለውጥ ውስጥ መጓዝ ከጀመርን ስድስት ዓመታትትን እያስቆጠርን ነው። ለውጡ እንደቀደሙት የለውጥ ትርክቶች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆንም፤ በተገራ የለውጥ አስተሳሰብ በመመራቱ ከብዙ መንገጫገጮች በኋላ ተስፋ ሰጪ ወደሆነ ታሪካዊ ምዕራፍ ተሻግሯል።

ለውጡ እንደቀደሙት የለውጥ ታሪኮቻችን በብዙ ፈተናዎች ተፈትኗል፤ የለውጡን ሕዝባዊነት ያልተረዱ ኃይሎች ለውጡን በቀላሉ ቀልብሰው ወደሚፈልጉት መንገድ ለመውሰድ ጥረዋል ፤በለውጥ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ግራ መጋባቶች ተጠቃሚ ለመሆን ረጅም ርቀት የሄዱ ነበሩ ፤የለውጥ ትርክት ሽሚያ ውስጥ የገቡ፤ ለውጡን የራሳቸው ለማድረግ የሞከሩም አልጠፉም።

ከሁሉም በላይ ቀደም ሲል እንደ ሀገር የብዙ ለውጥ ገፊ ምክንያት የሆኑ ኃይሎች ፤ለውጡን በኃይል ለመቀልበስ ሞክረዋል፤ በተሳሳተ ስሌታቸው ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሀገርን እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ የከተተ የእብሪት መንገድን መርጠው፤ ሕዝባችን ሊከፍል የማይገባ ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል።

ለውጡ ያጋጠሙትን እነዚህን የውስጥ ፈተናዎች እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሀገርን እንደ ሀገር ለማፍረስ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ፤የእኛ የማደግ መነሳሳት ስጋት የሆነባቸው ኃይሎች ”ውሻ በቀደደው…” እንደሚባለው ሁኔታዎችን የተሻለ አጋጣሚ አድርገው በመውሰድ በስፋት ተንቀሳቅሰዋል። ከፍ ባለ ጣልቃ ገብነት ተጋልጠዋል።

በአጠቃላይ አሁናዊ ሀገራዊ ለውጡ በእነዚህን እና የእነዚህ መገለጫ በሆኑ መልከ ብዙ ፈተናዎች ተፈትኗል። ፈተናዎቹን በጽናት ለመሻገር መላው ሕዝባችንም ብዙ ዋጋ ከፍሏል። በተከፈለው ዋጋ ልክም ለውጡ በእግር ከመቆም አልፎ መራመድ የቻለበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

አሁን ላይ ለውጡ ብዙዎቹን ፈተናዎች ተሻግሮ ፤ ስኬታማ ትርክቶችን በመገንባት መንገድ ላይ ነው፤ ከፈተናዎች ባሻገር ተስፋዎችን ተጨባጭ የማድረግ ጅማዎሬች ላይ ነው። ይህም ሆኖ ለውጡን ወደ ተጨባጭ ተስፋ ለማሸጋገር አሁንም ለውጡ በሚፈልገው መጠን ተለውጦ መንቀሳቀስን ይጠይቃል።

በተለይም የለውጡ ዋነኛ ባለቤት የሆነው ሕዝባችን፤ ለለውጡ ስኬት ከከፈለው እና እየከፈለው ካለው ዋጋ አኳያ፤ ለውጡ ሀገርን እንደ ሀገር የማሻገር ትልቅ ዕድል አድርጎ በመውሰድ ከፍ ባለ ትውልዳዊ ኃላፊነት ሊንቀሳቀስ ይገባል። ከግላዊ እና ቡድናዊ ፍላጎት በወጣ መንገድ ለውጡን የራሱ ማድረግም ይኖርበታል።

ከሃይማኖታዊ ፣ማህበረሰባዊ እና ባህላዊ እሴቶቹ የሚቃረኑ አክራሪነትን ፣ጽንፈኝነትን ፣ዘረኝነትን በሁለንተናዊ አቅሙ ሊዋጋቸው እስካሁን ካስከፈሉት ፣መራራ ዋጋ በላይ ዋጋ እንዳያስከፍሉት በቃ ሊላቸውና አምርሮ ሊታገላቸው ይገባል። እነዚህም የጥፋት አስተሳሰቦች የሚጠየፍ ማኅበረሰባዊ ማንነት መገንባትም ይጠበቅበታል።

እንደ ሀገር እና ሕዝብ / የጀመርነው የለውጥ ጉዞ ከሁሉም በላይ ወንድማማችነትን እና ዕጣ ፈንታን የጋራ አድርጎ በጠራ ዕውቀት እና ቁርጠኝነት መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ነው። ይህን ማድረግ ስንችል ነው ብዙ ዋጋ እየከፈልንለት ያለው የለውጥ ተስፋ ባለቤቶች የምንሆነው። ከራሳችንም አልፈን ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር መገንባት እና ማስረከብ የምንችለው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You