
በቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ የሚያተኩረው የኢራን እና የአሜሪካ አራተኛ ዙር ድርድር ተራዘመ።ኢራን፣ ሁለቱ ሀገራት ድርድሩን ከምታመቻቸው ኦማን ጋር በመሆን ቅዳሜ ዕለት በሮም ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞ የነበረው ስብሰባ “በሎጂስቲክስና ቴክኒካል ምክንያቶች” ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ መስማማታቸውን ገልጻለች።አሜሪካ አስቀድሞም ለንግግሩ ቀን አልተቆረጠም ነበር ብላለች።
ይህ የተባለው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሙስ ዕለት የኢራን ነዳጅን ወይም ፔትሮኬሚካልን በሚገዙ ላይ ርምጃ እንደሚወስዱ ካስፈራሩ እና ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው ኩባንያዎች ላይ በእዚህ ሳምንት አዲስ ማዕቀብ ከጣለች በኋላ ነው።ትራምፕ እኤአ በ2018 በኢራን እና በአምስት ኃያላን ሀገራት መካከል ከተደረሰው የኒውክሌር ስምምነት አሜሪካንን አስውጥተው የነበረ ሲሆን “የተሻለ” ስምምነት እንደሚያደርጉ ሲናገሩ ቆይተዋል።
በሚያዝያ ወር የተጀመረው አዲስ ንግግር ካልተሳካ ወታደራዊ ርምጃ እንደሚወስድ ቀደም ሲል አስጠንቅቀዋል።ሁለቱም ወገኖች በኦማን ዋና ከተማ ሙስካት የተካሄደውን የመጀመሪያ ዙር ንግግር “ገንቢ” ሲሉ ገልጸውታል።የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራግቺ እንደተናገሩት፤ ቴህራን “በድርድር ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለማምጣት ቁርጠኝነቷ” አልተለወጠም።”በእርግጥም፣ ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ ማዕቀብ እንዲቆም ዋስትና መስጠት እና የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር የኢራን መብቶች ሙሉ በሙሉ መከበሩን በማረጋገጥ ሰላማዊ ሆኖ እንደሚቀጥል እምነት ለመፍጠር ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጠናል” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በበኩሉ የቅዳሜው ስብሰባ እንዳልተረጋገጠ እና ቀጣዩ ዙር “በቅርብ ጊዜ ውስጥ” ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁሉም ወገኖች ሲስማሙ አዲስ ቀን እንደሚወሰን ተናግረዋል።
አሜሪካ ረቡዕ ዕለት በኢራን ላይ የጣለችው አዲስ ማዕቀብ ድርድሩ እየተካሄደ ካለበት አቋም በተቃራኒ የቆመ ነው የሚሉ ተቺዎች፣ ስለንግግሮቹ ጠቃሚነት ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።ረቡዕ ዕለት የተጣለው ማዕቀብ ትራምፕ በቴህራን ላይ “ከፍተኛ ጫና” ለማድረግ የሚከተሉት ፖሊሲ አካል መሆኑ ተገልጿል።የማዕቀቡ ዒላማ የሆኑት በኢራን ፔትሮሊየም እና ፔትሮኬሚካል ሕገ ወጥ ንግድ ውስጥ የሚሳተፉት መሆናቸውን አሜሪካ አስታውቃለች።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ “የኢራን አገዛዝ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ግጭት በማባባስ፣ የኒውክሌር መርሃ ግብሩን በማስፋፋትና አሸባሪ አጋሮቹንና ተላላኪዎቹን መደገፉን ቀጥሏል” ብሏል።በወቅቱ አሜሪካ ባወጣችው መግለጫ ላይ “አገዛዙ ለማተራመስ ተግባራት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የሚጠቀምበትን የገቢ ፍሰት ለመግታት ዩናይትድ ስቴትስ ርምጃ እየወሰደች ነው” ብሎ ነበር።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያቸው “ማንኛውም ሀገር ወይም ሰው ከኢራን ማንኛውንም መጠን ያለው ነዳጅ ወይም ፔትሮ ኬሚካል የገዛ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ ይጣልበታል” ሲሉ ጽፈዋል።”ከዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ጋር በማንኛውም መንገድ እንዲሠሩ አይፈቀድላቸውም።”ኢራን በበኩሏ የአሁኑ ማዕቀብ “የአሜሪካ ባለስልጣናት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ባህሪ እና እምነት እንደሌላቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው” በማለት ተቃውሞዋን አሰምታለች።
ኢራን የየመን ሁቲ አማጺያንን በመደገፏ ዋጋ እንደምትከፍል ያስጠነቀቁትን የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሰትንን መልዕክትም የኢራን የሚዲያ በዘገባዎቻቸው ውስጥ ጠቅሰዋል።የአሜሪካን ልዑካን ሲመሩ የነበሩት የትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍም መልዕክቱን በድጋሚ ለጥፈዋል።”ለኢራን የተላለፈ መልዕክት፣ ለሁቲዎች ያደረጋችሁትን ድጋፍ አይተናል። ምን እየሠራችሁ እንደሆነ እናውቃለን። በዚህ ምክንያት በመረጥንበት ጊዜ እና ቦታ ዋጋ ትከፍላላችሁ።”
ትራምፕ የኢራንን የኒውክሌር ቦምብ ለመገንባት የምታደርገውን መንገድ የሚዘጋ መፍትሄ እየፈለግኩ መሆኑን ጠቁመዋል።በአስተዳደራቸው ውስጥ የኢራን የኒውክሌር ማበልጸጊያ ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ የሚፈልጉም መኖራቸውን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም