የከተማዋ ውብና ፅዱ መሆን ለቱሪዝም ገበያው ዕድገት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ውብና ፅዱ መሆን ለቱሪዝም ገበያው ዕድገትና ለሥራ ዕድል ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ሲሉ አስጎብኚዎች ድርጅቶች ገለጹ፡፡እንደ ዜጋም በኩራት ቱሪስቶችን እያስጎበኙ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተር የቦርድ አባል እና የሞንፐይስ (Monpays) ቱር ባለቤት እንዲሁም ሥራ አስከያጅ አቶ ያሬድ ሙሉጌታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የከተማዋ አዲስ ገፅታ እጅግ ያማረ እና ደስ የሚያሰኝ ነው ፤በተለይ ለእኛ ቱሪስትን ለምናስጎበኝ ደግሞ ትልቅ ለውጥና ብዙ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ በእንደዚህ ዓይነት አዳዲስ መንገዶች እና የህንፃ ውበት አሸብርቃ መታየትዋ ቱሪስትን ለሚያስጎበኙ ትልቅ የሥራ ዕድል ፈጥሯል ያሉት አቶ ያሬድ፤ ከእዚህ ቀደም ቱሪስቶችን ስናስጎበኝ በከተማዋ ከአንድ ቀን በላይ አይቆዩም ነበር፤ እሱም ሆቴል ይዘው ለማደር ብቻ ነው፤ ምክንያቱም በፊት የነበረው የመንገድ እና የንፅህና ጉድለት እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ከተወሰኑ ቦታዎች በቀር ደረጃውን የጠበቀ የሚጎበኝ ነገር ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

ከእዚህ ቀደም ቱሪስቶች ከአውሮፓ፣እስያና ከአፍሪካም ሲመጡ ከአውሮፕላን ማረፊያ ተቀብለን መንገድ እየመረጥን ወስደን ቀጥታ ሆቴል ነበር የምናስገባቸው ያሉት አቶ ያሬድ፤በአሁኑ ወቅት ግን ቱሪስቶችን የምናቆይበት በርካታ የሚጎበኙ ቦታዎች እና በእግር ለመንቀሳቀስ የሚመቹ ሰፋፊ መንገዶች እና ፓርኮች ባማረ ሁኔታ መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለምሳሌ ዓድዋ ሙዚየም፣እንጦጦ ፓርክ እና ሌሎች በየቀኑ እንዲጎበኙ በማድረግ እንዲሁም አመቺ በሆነ ሁኔታ የተሠሩትን ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶችን ለአብነት ያህልም ከመስቀል አደባባይ- ፒያሳ በማሳየት የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ ማራዘም ተችሏል፤ቱሪስቶች በከተማዋ በቆዩ ቁጥር ደግሞ የአስጎብኚዎች ገቢ እና የሥራ ዕድል ይጨምራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ያሬድ፤አሁናዊ የከተማዋን ሁኔታ በተመለከተ ለዓለም መረጃ በማቅረብ እና በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ቱሪስት አዲስ አበባን ሲያያት በጣም ያልጠበቀው ለውጥ ይመለከታል፡፡

የከተማዋን ገፅታ የማስተዋወቅ ሥራ ቢሠራ እንዲሁም፤አስጎብኚዎች ፎቶ ግራፎችን በቀላሉ የሚያገኙበት መንገድ ቢፈጠር፤በተለይ አስጎብኚዎች ይዘን በምንመጣበት ወቅት የጊዜ ገደብ መኖሩን ቀድሞ ቢታወቅ፤ለምሳሌ አዲሱ ቤተ መንግሥት የማይጎበኝበት ቀን ካለ በግልፅ በፕሮግራም ማሳወቅ እንዲሁም የዋጋ ተመን ቀድሞ ለአስጎብኚዎች ማሳወቅ እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ተቀራርቦ መሠራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ለቱሪስቶች አመቺ የሆኑ ሬስቶራንቶች በከተማዋ ቢበራከቱ እንዲሁም ቅርሶች በየቀኑ ንፅህናቸው የበለጠ ተጠብቆ ሳቢ በሆነ ሁኔታ ቢቀመጡ መልካም ነው ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You