በአማራ ክልል ሰላም በመስፈኑ ኅብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል የፀጥታ ኃይልና በመከላከያ ሠራዊት በተደረገ ርብርብ በክልሉ አብዛኞቹ አካባቢዎች ላይ ሰላም ማስፈን በመቻሉ ኅብረተሰቡን የልማትና የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በክልሉ ያለውን ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በክልል መንግሥቱ በጋራ በሚያደርጉት ርብርብ በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ የሆነ ሰላም መስፈን ችሏል፡፡ አብዛኞቹ አካባቢዎች ወደነበሩበት ሰላም ተመልሰዋል፡፡ በከተሞች ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ያለ ሲሆን፤ የልማትም ፣ የመሠረተ ልማትም፣ የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ኅብረተሰቡን በማስተባበር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የአካባቢ ሚሊሺና ሰላም አስከባሪ ኃይል በማደራጀት በሚደረገው ርብርብ ከመቼው ጊዜ በላቀ በክልሉ ሰላም ማስፈን መቻሉን መንገሻ(ዶ/ር) አመልክተው፤ ሰላም በመስፈኑም ‹‹በተለይ ደግሞ በግብርና ልማታችን አኳያ የማዳበሪያ ስርጭቱ በስፋት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ በመደረጉ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ርብርብ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማምጣት ታቅዶ ከእዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ ወይም 43 በመቶ የሚሆነው ወደብ የደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስከአሁን ድረስም ለአርሶ አደሩ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆነው እየተከፋፈለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የክልሉ የፀጥታ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት በጋራ ባደረጉት ጥምረት የፅንፈኛ ኃይሉ የሚፈጥረውን መሰናክል በማለፍ የማደበሪያ ስርጭቱ ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡ በተመሳሳይ በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ረገድም 9 ሺህ 87 ተፋሰሶችን የማልማት ሥራ ተሠርቷል፤ በእዚህ መንገድ በርካታ ተራራዎችን በተፋሰስ ልማት እንዲሸፈኑ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

‹‹በዋና ዋና የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎቻችን ደግሞ 366 ሺህ 649 ሄክታር መሬት ለመሥራት ታቅዶ ፤ከእዚህ ውስጥ 366 ሺህ 654 መፈፀም ችለናል›› ብለዋል፡፡ በእዚህም ሥራ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆን የኅብረተሰብ ክፍል መሳተፉንና ይህም ሊሆን የቻለው የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከአረንጓዴ አሻራ አኳያም አንድ ነጥብ 62 ቢሊዮን የሚሆን ችግኝ ለተከላ ዝግጅት መደረጉን አመልክተው፤ ከእዚህ ውስጥ 85 በመቶ ቆጠራ ተካሂዶ አንድ ነጥብ 32 ቢሊዮኑን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የችግኝ መትከያ ጉድጓዶችም መቆፈራቸውና መላው የክልሉ ሕዝብ በተከላው የሚሳተፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከሰብል ልማት አኳያ ሰፊ የንቅናቄ ሥራ በክልሉ ዞኖችና ከተሞች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ ‹‹ በአሁኑ ወቅት በርካታ የክልላችንን መሬት ለሰብል ልማት ዝግጅት ተደርጓል፤ ምርትና ምርታማነትንም ለማሳደግ ወሳኝ የሆኑ የግብዓትና በቴክሎኖጂ ድጋፎችም እየተደረጉ ነው›› በማለት አብራርተዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በክልሉ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ በመሠራቱ የገቢ አሰባሰብ አቅም እየጎለበተ መጥቷል፡፡ በገቢ አሰባሰቡ ላይ ዘንድሮ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱም ለኅብረተሰቡ የሚያስፈልጉ የልማትና ማህበራዊ ሥራዎች ማስፈፀሚያ የሚውል የፋይናንስ አቅም እየጎለበተ መጥቷል፡፡

በትምህርት ዘርፍ ረገድም የተመዘገበው ውጤት እምብዛም የሚያበረታታ አለመሆኑን የተናገሩት ቢሮ ኃላፊው፤ ‹‹ በእዚህ ዓመት 7 ነጥብ 07 ሚሊዮን የሚሆን ተማሪ ለመመዝገብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በነበረው አለመረጋጋት አፈጻጸማችን በሚፈለገው ደረጃ አልነበረም›› በማለት ተናግረዋል፡፡ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ሰፊ ርብርብ ተደርጎ በርካታ ቦታዎች ላይ የመማር ማስተማሩ ሂደቱ እንዲቀጥል መደረጉን አብራርተዋል፡፡

አሁንም የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላት የሚገባ በመሆኑ በቀጣይ ዓመት በተሻለ ሁኔታ ሁሉም የክልሉ ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ፅንፈኛ ኃይሉ በርካታ የክልሉን ትምህርት ቤቶች ካምፕ አድርጎ መጽሐፎችን እያቃጠለ ፤ ንብረቶችን እያወደመ ፤ መምህራኖቻችንንም እየገደለ፤ እያሰቃየ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲያደርስ ቆይቷል›› ያሉት መንገሻ (ዶ/ር)፤ በተደረገው ብርቱ ጥረት ሰላም በመስፈኑ ትምህርት ቤቶችን የትምህርት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ከብሔራዊ ፈተና ጋር በተያያዘም ወደ 470 ትምህርት ቤቶች 99ሺህ 880 ተማሪዎችን 12ኛ ክፍልን መልቀቂያ ፈተና የሚፈተኑ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የስምንተኛ ክፍል ደግሞ 2ሺህ 642 ትምህርት ቤቶች ላይ 148 ሺህ 256 ተማሪዎች፤ ስድስተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ደግሞ 3ሺህ 551 ትምህርት ቤቶችና 154 ሺህ 260 ተማሪዎች ፈተና ላይ ይቀመጣሉ ብለዋል፡፡ በእዚህ ረገድ መምህራን ተፈታኝ ተማሪዎቻቸውን የማብቃትና ያለፉባቸውን ትምህርት የማካካሻ ትምህርት የመስጠት ሥራ በትርፍ ሰዓታቸው ጭምር በመጠቀም እየሠሩ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡ ለእዚህም መሳካት የክልሉ መንግሥትና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አስገንዝበዋል፡፡

ከትምህርት መሠረተ ልማት ግንባታ አኳያ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በእዚህ ዓመት ወደ 4ሺህ 229 አዲስ የመማሪያ፣ የአስተዳደር፣ ቤተ መጽሐፍት፤ የቤተ ሙከራና እና የመምህራን መጠለያ ክፍሎች ገንብተናል›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም 11 ሺህ 538 የሚሆኑ የመማሪያ፣ የአስተዳደር፣ ቤተ መጻሕፍት፤ የቤተ ሙከራና እና የመምህራን መጠለያ ክፍሎች ጥገና መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ለእዚህም የክልሉ መንግሥት ወደ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናግረው፤ በአሁኑ ወቅትም ሦስት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የእነዚህም አፈጻጸም 39 በመቶ መድረሱንም አመልክተዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You