ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት ያላቸውን ሙያተኞች ለመለየት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፡- 4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የመወዳደር ብቃት ያላቸው ኢትዮጵውያን ሙያተኞች የመለየት እድል እንደሚፈጠር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አራተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ‹‹ ብሩህ አእምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች›› በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዚያ 27 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የክህሎት ማህበረሰብ አባል ናት:: በእዚህም መስከረም ወር በፈረንሳይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የክህሎት ኦሎምፒክ ላይ የአባልነት ምስክር ወረቀት ተቀብላለች::

በወቅቱም በተለያየ የሙያ ዘርፍ የተወዳደሩ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገባቸውን አውስተው፤ አራተኛው የክህሎት ውድድር ብቁና በዓለም አቀፍ መድረኮች የመወዳደር ብቃት ያላቸው ኢትዮጵውያን ሙያተኞች ተለይተው እንዲወጡ ያስችላል ሲሉ ጠቁመዋል::

ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ የውድድሩ ዓላማ የዘርፉን አዲስ እሳቤ መሠረት ያደረገ የአሰልጣኞች፤ ሰልጣኞች እና የሥራ ፈጠራ አንቀሳቃሾች ሙያዊ ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያግዝ ነው:: እንዲሁም የውድድር መንፈስ መፍጠር፣ ቴክኖሎጂ የመቅዳት፣ የማሻሻል እና የመፍጠር አቅም አጎልቶ ማሳየት ነው::

እንዲሁም አዳዲስ እና የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲያሸጋግሯቸው ማነሳሳት መሆኑን ጠቁመው፤ የሴቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ማሳደግ እና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ፋይዳ ለህብረተሰቡ ማስገንዘብ መሆኑን ጠቁመዋል::

ውድድሩ በሦስት ዘርፎች የሚካሄድ ሲሆን፤ በክህሎት ዘርፍ በ22 የስልጠና መስኮች የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን ብቻ ይሳተፋሉ ያሉት ሚኒስትሯ፤ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆነ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የፈጠሩ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች፣ ሰልጣኞች እና ሥራ ፈጣሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችም እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል::

ከውድድሩ ጎን ለጎን ለውድድር የቀረቡና እና ከየክልሉ የተመረጡ 70 ቴክኖሎጂዎች ለእይታ እንደሚቀርቡ አመልክተው፤ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት ኤግዚቢሽንና ባዛር ይካሄዳል:: በሌላ በኩል ደግሞ የፓናል ውይይት እንደሚኖር ገልጸዋል::

ወይዘሮ ሙፈሪያት እንደተናገሩት፤ በ2015 ዓ.ም የተካሄደው ሦስተኛው የክህሎት ውድድር በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተወዳደሩና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የፈጠሩ ተወዳዳሪዎች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ቴክኖሎጂያቸውን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችል ‹‹ሠመር ካምፕ›› ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲደረግ አስችሏል::

በፕሮግራሙም በ2016 በጀት ዓመት ከ80 በላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አምርቶ ለማውጣት የተቻለ መሆኑን ገልጸው፤ የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ በማቋቋም ወደ ምርት እንዲገቡ የሚያስችሉ የፋይናንስ፣ የማምረቻ ቦታ፣ የገበያ ትስስርና መሰል ድጋፎች እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል::

ቀጣይ የሚካሄደው ውድድር የሙያ ሥልጠናን አስመልክቶ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማዳበር፤ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፤ የስልጠና ጥራትን የሚያረጋግጡ ተግባራዊ ምርምሮች ለማግኘት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመወዳደር አቅም ያላቸው ሙያተኞች ለመለየት እንደሚያስችል ገልጸዋል::

ውድድሩ በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት፤ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እና በምሥራቅ ፖሊ ቴክኒክ ይካሄዳል:: በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በተካሄዱ ተመሳሳይ ውድድሮች አንደኛ ሆነው ያጠናቀቁ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች፤ ሰልጣኞች እና የኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች በውድድሩ ይሳተፋሉ ሲሉ ጠቁመዋል::

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You