
አዲስ አበባ፡- የዓለም አቀፍ ድጋፎች መቋረጥ ለመላው አፍሪካውያን የውስጥ አቅማቸውን ተጠቅመው ራሳቸውን እንዲችሉ የማንቂያ ደወል መሆኑን በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ሴንተር ፎር ገቨርናንስ ኤንድ ኢንትራ አፍሪካ ስተዲ ዳይሬክተርና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሰይፈ ታደለ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
በጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ሴንተር ፎር ገቨርናንስ ኤንድ ኢንትራ አፍሪካ ስተዲ ዳይሬክተር ሰይፈ ታደለ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካም ሆነ በሌሎች ሀገራት የሚደረጉ ድጋፎች መቋረጥና መቀነስ አፍሪካውን ከመደናገጥ ይልቅ በእጃቸው ያለውን የውስጥ አቅም ተጠቅመው ራሳቸውን ለማሳደግ የማንቂያ ደወል ሊሆናቸው ይገባል፡፡
አብዛኞቹን የአፍሪካ ሀገራት የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ውጤት በሆነው የተረጂነት አመላካከት ራሳቸውን ነፃ ማውጣት ያለመቻላቸውን ሰይፈ (ዶ/ር) ተናግረው፤ ጥቂት የማይባሉት ሀገራት የምዕራባውያኑ ርዳታቸው ሲቆም ሰማይ የተደፋባቸው ያህል ውጥንቅጥ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል፡፡ በተለይም በእጃቸው ላይ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና ሰፊ የሰው ኃይል ከመጠቀም ይልቅ የሃያሉን ሽርፍራፊ የመጠበቅ ሁኔታ እንደሚስተዋልባቸው አስረድተዋል፡፡
‹‹ርዳታ የለመደ እጅና አፍ ሁልጊዜም ቢሆን ርዳታ ነው የሚጠብቀው፤ አፍሪካውያን የጠባቂነት አስተሳሰብ አንገታችንን ሰቅዞ ይዞናል ያሉት ምሁሩ፤ ለእዚህም ነው ለም መሬት እያለን ስደት የምናፍቀው፤ አሁንም ቢሆን የአካል ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ባሪያ መሆንን መርጠናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ሀገራት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛቱ በፈጠረባቸው ጫና ካሉበት ችግር በራሳቸው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት በሚጠበቀው ልክ አለመሆኑን አብራርተዋል:: የአፍሪካ ሀገራት እንደ የአሜሪካ የርዳታ ድርጅት (ዩኤስ ኤድ) ያሉ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ድጋፎች መቋረጥ ሊያነቃቸውና እንደበረከት ሊቆጥሩት እንደሚገባ ተናግረዋል::
‹‹አልተረዳነውም እንጂ እነሱ እየነገሩን ያለው ነገር ቤታችሁ ያለውን ሥራ ሥሩ የሚል ነው፤ በጥቅሉ የአለም አቀፍ ድጋፎች መቋረጥ ወደ ውስጥ የምንመለከትበት እንደወርቃማ እድል የሚቆጠር ነው›› የሚሉት ሰይፈ (ዶ/ር)፤ በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ለራሳችሁ ሕዝብ ምግብ ማቅረብና ከውጭ ድጋፍ ጠባቂነት እንዲወጡ እንደ ገፊ ሁኔታ ሊቆጥሩትና ሊወስዱት እንደሚገባም አስገንዝበዋል::
‹‹እንደሚባለው አንዳንድ ሰዎች ውብ ቦታ ይሄዳሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ቦታቸውን ውብና ጽዱ ያደርጋሉ፤ እኛ እዚህ ሆነን የውጭውን ከምንናፍቅ አጠገባችን ያለውን ለም መሬትና አዕምሮ ተጠቅመን ሀገራችንን ብሎም አህጉራችንን ውብና ሳቢ ልናደርግ ይገባል›› በማለትም አብራርተዋል::
አፍሪካ ኢኮኖሚዋን ራሷ ከተቆጣጠረች ፤ በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ የሚደረገውን የውጭ ምዝበራ ካስቆመች፤ መሪዎቿም ሕዝቡንና የግሉን ዘርፍ አስተባብረው ከሠሩ ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች የበለፀጉ ሀገራት የተሻለ አቅም እንደሚኖራትም አመልክተዋል::
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም