
ከተማዋ በርካታ ተፈጥሯዊ ሀብቶች ያሏት በመሆኗ የሀገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በየቀኑ ታስተናግዳለች። ታዲያ ተፈጥሯዊ ሥፍራዎች አልያም የቱሪስት መስህቦች ብቻቸውን ቱሪስቶች የሚመርጧቸው ላይሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም የቱሪስት መስህብ በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ላይ ለጎብኚዎች ምቹ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
ለዚህም ይመስላል የአርባምንጭ ከተማ አየር ማረፍያ ሥፍራ እንግዶችን ካረፉበት ሰዓት ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ መዳረሻቸውን አድርገው የተለያዩ አገልግሎቶችን በውስጣቸው ይዘው የሚገኙ ሆቴሎች ከአየር ማረፊያው መግቢያ ጀምሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ እንግዶቻቸውን የሚቀበሉት። ለከተማዋ አዲስ የሆኑና አስቀድመው ቦታ ያልያዙ ተጓዦች ቢኖሩ ይህ ጥሩ አማራጭ ይመስላል ።
ሆቴል እና መስተንግዶ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ውስጥ አንዱ ዘርፍ ሲሆን በቱሪስት አይን ከሚጎበኙ ሥፍራዎችን ሄደው ከማየት ባሻገር ቦታውን ለማየት በሥፍራው ቆይቶ እና ጥሩ የጉብኝት ጊዜን ለማሳለፍ የሚያርፉበት ቦታ ምቹነት አስቀድሞ ግምት ውስጥ የሚገባ ነው። በቆይታቸው የሚያርፉበት ሆቴል ምቹ የተረጋጋ እና ጥሩ የሚባል አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑን ማወቅ ይፈልጋሉ ።
ለጉብኝት ወደ አዲስ ቦታ መሄድ የሚሰጠው የራሱ የሆነ መደነቅ እና ቦታዎችን ለማየት መጓጓት የሚፈጥረው ልዩ ስሜት አለ። ታዲያ እነዚህን የቱሪስት መስህብ የሆኑ ሥፍራዎች ቦታ፣ ምንነትና ታሪክ ጎብኚዎች ባላቸው እና በመጠኑት የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚያሳይ ባለሙያም የጉብኝት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል።
በእግሊዝኛው ቱር ጋይድ የሚል ስያሜ ሲኖረው የአርባምንጭን ከተማ በመሰሉ የጉብኝት ሥፍራ የሚመጡ አዳዲስ ጎብኚዎችን ተቀብሎ ባላቸው የጊዜ ቆይታ ጥሩ ትውስታ እንዲኖራቸው ማድረግ አንዱ የአስጎብኚዎች ኃላፊነት ነው ።
ወጣት ዘካርያስ ጴጥሮስ ይባላል ። ትውልድና እድገቱ በአርባምንጭ ከተማ ጋሞ ዞን ውስጥ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። ዘካርያስ የልጅነት ጊዜው በአርባምንጭ ከተማ ያሉ የቱሪስት መስህቦችን ለማየትና ጠንቅቆ ለማወቅ እድል አግኝቷል። ነገር ግን ዘካርያስ የወጣትነት ጊዜውን በአስጎብኚነት እና የአገልግሎት ዘርፍ ላይ እንዲያሳልፍ ተጽዕኖ ያሳደረበት ሰው ነበር ። ‹‹ ልጅ ሆነን በምንኖርበት ቦታ ብዙ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ይመጡ ነበር። ታዲያ የእኔ አባት ብዙ መረጃ ስላለው እና ከሰዎች ጋር መግባባት ላይ ጥሩ ስለነበር ከእሱ ጋር ሆኜ ሁሌ የሚመጡትን ቱሪስቶች የማየት እና አባቴ የሚሠራውን ሥራ የመመልከት እድል ነበረኝ ። ›› በማለት ወደኋላ አስታውሶ ጎብኚዎች የጉብኝት ጊዜያቸውን አጠናቀው ሲሄዱ ለዘካርያስ የሚያበረክቱለት የተለያዩ የማስታወሻ ስጦታዎች እንደነበሩ ይገልጻል። በመሆኑም አድጎ በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ መሥራት ከልጅነት ጀምሮ ሕልሙ ሊሆን ችሏል ። ዘካርያስ የ12ተኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሆቴልና ቱሪዝም የትምህርት ዘርፍ የመጀመርያ ዲግሪውን አጠናቀቀ ።
ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በሆቴል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የፍቃድ ማረጋገጫ ተቋም ውስጥ ለአንድ ዓመት ያክል ከሠራ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሆቴል ኢንደስትሪ ሥራ በመግባት እየሠራ ይገኛል ። ከተማዋ የሚገኙ የሆቴል አገልግሎቶች በአብዛኛው የአርባምንጭ ከተማን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎችን ባለው ትርፍ ጊዜ የተለያዩ ቦታዎችን የማስጎብኘት ሥራውን ጀመረ ። የቱሪስት መስህቦች አስጎብኚ ለመሆን በርካታ ክሕሎቶች የሚያስፈልጉ ሲሆን ኃላፊነትን ከመቀበል ጋር ተያይዞ ቀላል የማይባል ሥራ መሆኑን ዘካርያስ ገልፀዋል ።
በመሆኑም ሥራውን ለመጀመር እና የመጀመርያ ጎብኚ ደንበኞቹን ለማግኘት በጥቂቱም ቢሆን መቸገሩን አስታውሷል ። ‹‹ ጎብኚዎች አንድን ቦታ ለመጎብኘት ሲመጡ ነጻነትን እና ያሰቡትን አሳክተው መሄድም ይፈልጋሉ። እና እንደ አስጎብኚ ደንበኞቻችንን ለማስደሰት መስዋዕት የምናደርገው ነገር ይኖራል። ›› በማለት ገልጾ ሰዎች እንደየመልካቸው ባሕሪያቸው የተለያየ ነውና ከሁሉም ጋር መልካም የሆነ ተግባቦትን ለመፍጠር የራሱ የሆነ ጥረትን ይጠይቃል። ዘካርያስ በዚህ ረገድ የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲሁ ልዩነት እንዳላቸውም ይገልጻል።
የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እያንዳንዱን ቀናቸውን እና ደቂቃቸውን በፕሮግራማቸው ውስጥ አካተው የሚመጡ በመሆናቸው ምንም አይነት የሰዓት ሽርፍራፊ ቦታ እንደሌለው በማስታወስ እንደ ሀገር ሰዓት አጠቃቀምና የሰዓት አከባበር ላይ ያለንን ክፍተት ጠቆም ያደርጋል። ሌላኛው የባሕሪ ልዩነት ሲሆን ጉብኝት የቱሪስት መስህብ የሆኑ ሥፍራዎችን እያዩ አዕምሮን ዘና ማድረግ መንፈስን ማደስ መዝናናት ነውና አንዳንድ ጎብኚዎች እንቅስቃሴቸው እንከን አልባ እንዲሆን ይመኛሉ ። ‹‹ ወደ አንድ ቦታ ለመጓዝ መንገድ ጀምረን መኪናችን ቢበላሽ አልያም በመንገድ እና አየር ንብረት ሁኔታ መኪናችንን ለመቆም ቢገደድ አንዳንድ ጎብኚዎች በጣም ይናደዳሉ ፤ ሌሎች ደግሞ ያንንም እንደ አንድ አጋጣሚ በመለየት ዘና ለማለት ይሞካራሉ ። ›› ሲል ሰዎች ምን ያህል የባሕሪም የስሜትም ልዩነት እንዳላቸው ከልምዱ ያስታውሳል ።
ጎብኚዎች አንድ የቱሪስት መስህብ ሥፍራ ለመጎብኘት ሲመርጡ አስቀድመው መረጃዎችን ይከታተላሉ። ከዚያም የቦታውን ሳቢነት ከእነርሱ ፍላጎት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ለመጎብኘት ትክክለኛ የሆነውን ሰዓት መርጠው ለጉብኝት ቀጠሮ ይይዛሉ ። ታዲያ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በመረጃ ሰምተው እና በተንቀሳቃሽ ምስሎች ተመልክተው የሚመጡት ቦታ አለመመጣጠን ሌላኛው ዘካርያስ ከደንበኞቹ የሚቀበለው አስተያየት ነው ። ወደ አርባምንጭ ከተማ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚመጡ ሲሆን ከጣልያን፣ ከጀርመን ፣ አሜሪካ እና ከስፔን የሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተደጋጋሚ ወደከተማዋ ለጉብኝት እንደሚመጡ ዘካርያስ ይገልጻል።
‹‹አስጎብኚዎች ብዙውን ጊዜ ለሚያስጎበኙት ሥፍራ በደንብ የሚያውቁት በመሆኑ ከመረጧቸው ጎብኚዎች ጋርበሚኖራቸው ቆይታ ይበልጥ ለመግባባት እና የጓደኝነት ተግባቦትን ለመፍጠር ይጥራሉ። ይህም ለጎብኚዎች የቤተሰባዊነት ስሜትን እንዲፈጥርባቸው ያደርጋል። ነገር ግን በዚህ መሀል አንዳንድ የአስጎብኚዎችን ድንበር የሚተላለፉ ደንበኞች ገጥመውት እንደሚያውቁ እና ይህንን ሁኔታ ማስረዳት ከባድ እንደሆነበት ይገልጻል ። ‹‹ አንዳንድ ጎብኚዎች ከሱስ ጋር በተያያዘ የሚጠቀሟቸውን አደንዛዥ እጾች እንድንጋራቸው ወይም ማጨስም ከሆነ አብረናቸው እንድናጨስ ይፈልጋሉ ፤ በዚህ ወቅት እንደማይሆን ስነግራቸው ንቀት ይመስላቸዋል ይሄ በሥራዬ አንዱ ከባድ ነገር ነው። ›› ሲል ሁኔታውን ያስረዳል።
‹‹የአርባ ምንጭ ከተማ ከስያሜ ጀምሮ በተፈጥሮ የታደለች በልምላሜዋ የምትታወቅ ናት። ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ያሉባት በመሆን እና በርካታ የፍራፍሬ ምርቶች ትታወቃለች ። ›› በማለት የሚገልጸው ወጣት ዘካርያስ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ ሲመጡ የስያሜ መጠርያ የሆነውን ተፈጥሯዊ ምንጮች ፣ ፍልውሀዎች በስፋት የሚታወቅበት የአዞ እርባታ ሲሆን ወጣቶች ከአዞዎች ጋር በመላመድ አዞ እርባታ ሥራዎች በይበልጥ የሚጎበኙ ሥፍራዎች ናቸው ።
ነጭ ሳር ፓርክ ፣ እንዲሁም የዶርዜ ባሕላዊ መንደር በይበልጥ ጎብኚዎች ወደ አርባምንጭ ከተማ ሲመጡ የሚያዩዋቸው ናቸው ። ታዲያ እነዚህ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ሥፍራዎች ተፈጥሯዊ ናቸውና ተንከባክቦ ለመጪው ትውልድ ማቆየት እሴት በመጨመር በዘርፉ ላይ ከተማዋ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ ማድረግ እና እንደ ዘካርያስ ላሉ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥር እና አዳዲስ ባለሙያዎችንም ለማፍራት የሚጋብዝ ሊሆን ይገባዋል ። በመሆኑም ዘካርያስ ሕብረተሰቡ ወደ ከተማዋ ከሚመጡ ጎብኚዎች የባለቤትነት ስሜትን በመፍጠር ተፈጥሯዊ ሀብቶቹ ሊጠብቃቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። ለዚህም ለማሕበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እና ተፈጥሮን የመጠበቅ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁሟል ።
በቀላል አገላለጽ አስጎብኚ ብለን የምንገልጸው ይህ የሥራ ዘርፍ ባለሙያውን ታሪክ አዋቂ መሆን ፣ የሚያስጎበኘውን ሥፍራ ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል ። የጎብኚዎች የመጡበት ስፍራ የተለያየ በመሆኑም በዚህ ዘርፍ ውጭ ቋንቋዎች ክህሎት እና ከሰዎች የሚኖረው የተግባበቦት ክህሎት ላይ መሥራት ይጠበቅበታል ። ዘካርያስ በአርባምንጭ ከተማ ተወልዶ ያደገ እና ለሥራው ፍላጎት ያለው መሆኑ፤ የአካባቢው ተወላጅ መሆኑ እና የሀገሩን ቋንቋ መቻሉም ይበልጥ ለሥራው እንደጠቀመው ይናገራል ። በተለያዩ መንገዶች እውቀቱን ለማዳበር እና ክህሎቱን ለማሳደግ ና አዳዲስ እንደ አረብኛ ያሉ የውጭ ቋንቋዎችን በመማር ሥራው ላይ ይበልጥ ተፈላጊ እንዲሆን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2017 ዓ.ም