ዝቅታዬን ወደድኩት

“ቁምነገሩ ሠርቶ ብዙ ማግኘት ሳይሆን ያገኙትን ጥቂት ገንዘብም ቢሆን በአግባቡ መጠቀም መቻል ነው” ይላል ወጣት ቤዛ መለሰ። ይህስ እንደምን ያለ ትህትና ነው ከውርደት ውስጥ ክብረትን ከዝቅታ ውስጥ ከፍታን መታደል? ጫማ ከመጥረግ ተነስቶ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ላይ ሠርቶ ለአሥር ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ታታሪ ወጣት ነውና ከልምዱና ከተሞክሮው ትማሩበት ዘንድ በመጋበዝ የብዕርን ዳና ተከትለን ከሕይወቱ ማጄት አብረን እንዝለቅ።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ነጭላላ መንደር እንሽርት ውሃውን ተከትሎ ወጣት ቤዛ መለሰ ለወላጆቹ ሶስተኛ ልጅ ሆኖ 1985 ዓ.ም ተወለደ። ታላቆቹ ቤተሰብን ለማገዝ በግብርና ሥራ ስለተሠማሩ ወላጅ እናቱ በቀዬው ልማድ ከቤት አንድ ልጅ ለቤተክርስቲያን አገልጋይነት ማብቃት ግድ ነውና አጋጣሚው ለቤዛ ደርሶ በስድስት ዓመቱ በአካባቢው በሚገኝ ደብር የቆሎ ትምህርት አስጀመሩት።

አንተ የአብነት ትምህርት የጀመርክበት እድሜ አልፎ አልፎ ጡት የማንጥልበት እናቶቻችን ገበያ ወጥተው እስኪመለሱ ድረስ እየነፈረቅን የምንጠብቅበት ነውና ከቤተሰብ ሃሳብ ከላመና ከጣመ ምግብ ርቀህ ሕይወትን እንዴት ተቋቋምካት እንዴትስ ተላመድካት? ስል ጠየኩት። በእሱ ቦታ ሆኜ የእኔን እድሜ እየፈተሽኩ። የትዝታ ማህደሩን ገልጦ የዘገነውን ወግ አጣፍጦ አጫወተኝ።

“መሪ ጌታ ልዑለ ቃል ማእላፍ ሥጋንም ነፍስንም በሚያጸና ምክር ኮትኩተው በማሳደግ ጠንካራ ሞራል ስላስታጠቁኝ ለሰሚ የሚያደናግር፤ ለፍርድ የሚያስቸግር ከባድ ፈተና አሳልፌ ይኸውልህ አሁን ላለሁበት ደረጃ ለመድረስ በቅቻለሁ” አለ ከገጹ የመከራ ሰንበሩ በብሩህ ጸዳል ተተክቶ እንደንቡጥ ጽጌሬዳ እየፈካ። ቀጠለና ጺሙን እያፍተለተለ በትዝታ ሰበዝ የሰፋውን የሕይወቱን ሰፌድ ቁልጭ አድርጎ አሳየኝ። “ቁራሽ ለመለመን ረጅም ሰዓት ተጉዘን ራቅ ወደአሉ አጎራባች ጎጦች እንሄዳለን፤ በእዚያ ላይ ቁራሽ እወስዳለሁ አትወስድም ውሻ ጋር ግብግብ መግጠሙ። በራሱ ፈተና ነው፡፡

አንድ ቀን ቁራሽ ለምኜ ስመለስ የጣለው ዝናብ ወንዝ በመሻገር ላይ እንዳለሁ ከባድ ማዕበል አምጥቶ ይዞኝ ተጓዘ፤ ችፍርግ ይዤ ባልቀር ኖሮ ሕይወቴን ቀምቶኝ እስካሁን እረሳ ነበር” አለ አሁን የሆነ ያህል እያንዘፈዘፈው።

ለተሻለ ትምህርት በአቀናበት ደጋ ዳሞት ወረዳ ቡጥላ እየሱስ የዜማና የቃል ትምህርቱን አጠናቆ ቋሪት ገበዘማርያም ተመለሰና የቀዬውን ደብር በድቁና ማገልገል በጀመረበት አጋጣሚ ከተሜነት ቀልቡን ገዝቶት የትኩረት መልህቁን እንደጣለበት ይናገራል። በከተማው ቴሌቭዥን ያለው አንድ ቤት ብቻ ስለነበር ገብቶ እንዳያይ አንድ ብር የለውምና ከቤቱ ትይዩ ባሻጋሪ ጉብታ ላይ ይቆምና “ሰይጣኑ ተለቀቀ” እያለ ይደነቅ ነበር፤ “እንዲህ ከሆነማ ሰፊ ከተማ ብሄድ የተሻለ ነገር አያለሁ፤ ጥሩ እድልም ሊገጥመኝ ይችላል” ብሎ በማሰብ በወረዳው ባለችው በአንድ ለእናቱ ሎንቺና ለመሳፈር ፍራንክ ስላልነበረው በልጅ እግሩ ወደ ፍኖተ ሰላም ተወዘወዘ።

ማረፊያ ሁነኛ ዘመድ ነበረህ? ወይስ ምን መተማመኛ አግኝተህ ነው ለመሄድ መቁረጥህ? አልኩት እድሜው ስምንት ዓመት ብቻ መሆኑ ጭንቀት ፈጥሮብኝ፤ አብሬው በመንከራተት ላይ ነበርኩና። መቼም የሰላ ሃሳብ ድርብርብ ልብ ቢታደል ነው እንጂ ይሄን ሁሉ መከራ እንኳን በልጅ አቅም ነፍስ አዋቂውስ እንዴት ሊቋቋመው ይችላልን? ትናንትን የመጣበት ጽናቱ፣ ዛሬን አሻግሮ ነገን የሚያይበት ተስፋውና የጠራ ህልሙ አብዝቶ ደነቀኝ።

“በቆሎ ተማሪ ቤት ያላወቁትን መጠየቅ ባሕል ነውና ፍኖተሰላም ደርሼ ቀምሼ የማድረው ቁራሽ ስለምን ቀስተ ደመና ሆቴል በሰንበት ቀን ድርሳነሚካኤል እንዳደርስላቸው በወር ሁለት ብር ቀጠሩኝ” አለ መላ ፊቱ እየፈገገ። “በእንዲህ መልኩ እየኖርኩ ሳለ ዘመናዊነቱ አማለለኝና ወረቀት ጠቅልዬ እጣ ስሠብቅ ባሕር ዳር ወጣችልኝና ከአምስት ቀን የእግር ጉዞ በኋላ መሬቷን ሳምኩ” ሲል ያቀለመውን የጉዞ ማስታወሻ አንድ በአንድ አስበረበረኝ።

እድሜው ገና ቢሆንም በትምህርት ደረጃው ለአቅመ ቅኔ ደርሷልና “የእግዜር እንግዳ” ብሎ በአረፈበት ሽንብጥ ሚካኤል መማር ይችል እንደሆነ ቢጠይቅ ደጅ እንዲጠና ነገሩት። እሺ ተብሎ ቦታ እስኪያገኝ ድረስ ማረፊያ ስፍራ ቸግሮት አማራጮችን ሲያስብ ወለል ከፍሎ ለማደርም ድንቡሎ ሳንቲም እንደሌለው ልብ ሲል ወዲያ ወዲህ ተራወጠ።

ገበያ ገብቶ ቋጠሮ ሲሸከም ያልጠና አካሉ “እንዲህ ያለ ሥራ አላውቅም” አላለም፤ ይልቁንም ራሱን ሁኔታዎች ጋር አስማምቶ መኖር ቻለ እንጂ። ከበሮ ማንጠልጠሉ፣ ጸናጽል ማንሿሿቱ፣ መቅረዝ ማብራቱ፣ መቀደሱ አስታብዮ ሥራ እንዲንቅ አላደረገውም፤ እንዲያውም ጨፌ እየሸጠ፣ ሲሚንቶ እያቦካ፣ ተባራሪ የጉልበት ሥራዎችን እያከናወነ ገጽታውን ለማሻሻልና የአስኳላ ተማሪዎች ዩኒፎርም ለብሰው ደብተር ይዘው ሲመለከት መንፈሳዊ ቅናት አድሮበት ዘመናዊ ትምህርት ለመጀመር እጅጉን ቋመጠ።

ከቀናት ደጅ ጥናት በኋላ በሽንብጥ ሚካኤል መሪጌታ መንግሥቱ ዘንድ ይሁንታ አግኝቶ ለሶስት ዓመታት ያህል ተምሮ ቅኔ ቢያጠናቅቅም በቤቱ ውስጥ እያሉ አስኳላ መማር እንደማይቻል ስለተነገረው ጥሎ ወጣና ወደ ሁመራ አማተረ። በመስከረም ትምህርት ለመጀመር ገንዘብ መያዝ እንዳለበት አምኖ ክረምቱን በመጠቀም የቀን ሥራ ለመሥራት ከባሕር ዳር ጎንደር ገብቶ አደረ። በነጋታው ኪሱን ሲያዋየው ቁና ሙሉ እየተነፈሰ ሲያዛጋ ስልሳ ብር ብቻ እንዳለው ልብ አለ።

መዳረሻው ማይካድራ ነውና ከሁመራ ቅርብ መሆኑን ስለሰማ “በእግሬ እሄዳለሁ” ብሎ በቅጥቅጡ መኪና ተሰቀለ። ማይካድራ እንደደረሰ ዘጠኝ ዓመት የተለየውን ወንድሙን አበባው መለሰን ለመፈለግ ከከተማው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘልቆ ለርዕሰ መምህሩ ሲያማክረው ጥበቃው እንዲያፋልገው አደራ ሰጠውና በያዘው ፎቶ እየተመሩ ወንድሙ ጋር ለዓይነ ሥጋ በቁ። ደስታቸው አይሎ ዓለም አለፈና የአካባቢውን ወዝ ሲያነሳ “የመጣሁት አንተን ለመፈለግ ሳይሆን ክረምቱን ሠርቼ በመስከረም ትምህርት ለመጀመር አስቤ ነው” በማለት ሃሳቡን ሲገልጽለት ወንድሙ ጊዜ ሳያጠፋ ፈቃዱን ሞላለትና ሕይወት ከበረሃው ንዳድ ጋር ትግል ገጠመች።

ከሰሊጥ አረም አንስቶ እስከ አጨዳው ድረስ ሶስት ሺህ ብር አፈራና ከእናቱ ጉያ ስር ሆኖ ለመማር እትብቱን ወደቀበረባት ነጭላላ ተመልሶ አስኳላ ትምህርቱን አሀዱ አለ። ለትምህርት የሚያግዙ ቁሳቁሶችን አሳክቶ በተረፈው ብር ክበድ በጎችን ገዛና ጎን ለጎን ማርባት ጀመረ። ከተማ ለምደህ ገጠር ስትገባ ስሜቱ ቀላል ነበር? አልኩት። “እዚህ መማር የቻልኩት እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያለውን ያጠናቀኩት ባሕር ዳር ነው” አለ የቀረ የባሕር ዳር ቆይታውን ታሪክ ዳግም እያሲያዘኝ።

8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ ቁልቋል ሜዳ ትምህርት ቤትን ያስጠራ እንጂ ኑሮውንም የመራበት ጥረቱ እጅን በአፍ ያስጭናል። በመቶ ሃምሳ ብር የወር ደመወዝ ማታ ማታ ለአልጋ ቤት በጥበቃነት ተቀጠረ፤ በተጨማሪም ከትምህርቱ በተቃራኒ ፈረቃ ሳይክል ቤት በአጣቢነት አገለገለ። ከዚህም ሌላ የአልጋ ቤቱ በር ላይ የሊስትሮ እቃ በማስቀመጥ ጫማ በማጽዳት ኪሱን ይደጉማል።

ምን ሰዓት ነው የምታነበው? ጊዜውስ እንዴት ይበቃሃል? ስል ጠየኩት። “ሰክሮ የሚረብሸኝ ከሌለ በቀር ደብተሬ ከኔ አትለይም” ሲል መለሰልኝ። የገንዘብ አጠቃቀም ላይስ እንዴት ነህ? አልኩት በማስከተል። “የምደክመውኮ በልቼ ለማደር ሳይሆን የኔንም የሀገሬንም ነገ ለማሳመር ነው” አለኝ በራስ መተማመኑ ከድምጹ ቃና እየተነበበ።

ክረምት ላይ የዓረፍት ጊዜውንም በዋዛ ፈዛዛ ሳያባክን ሱቅ በደረቴ እየሠራ ተጨማሪ ገቢ መፍጠር ቻለ፤ ይህም ዛሬ ላለበት የሀብት አቅም እርሾ እንደሆነው ይናገራል። ወትሮውኑ ቀልቡን የሚገዛው የጣና ሐይቅ ዩኒፎርም ጽናት አላብሶት ማትሪክን 3 ነጥብ 8 በማምጣት ማህበራዊ ሳይንስን ተቀላቀለና ወደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ443 ውጤት ተሻገረ።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የተማሪ ሕብረት ከመሆን ባለፈ በበጎ አድራጎት ሥራዎች በመሳተፍ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። በመመረቂያው ዓመት ኮርስ ተበላሽቶበት ከጓደኞቹ ወደኋላ ሲቀር ተስፋ ባለመቁረጥ ከማርቆስና ከአዲስ አበባ እያመጣ ብር ሸለቆ ልብስ ማዞር ጀመረ፤ ሥራው ጥሞት በተመረቀበት አካውንቲንግ ባንክ ተወዳድሮ ቢያልፍም “ቅጥር ለምኔ” አለና ቴንፖና ጋውኑን ለትዝታ አስቀምጦ ሱቅ በደረቴ መሃል መርካቶ ጀመረ።

“ከዚህ ሁሉ እኔን የሚቆጨኝ ጓደኞቼን አፍሬ የኮሮናን አጋጣሚ ተጠቅሜ ማስክና ሳኒታይዘር ሸጬ ማግኘት የነበረብኝን ጥቅም በማጣቴ ነው” አለ በሰው መስታወት ራሳቸውን እንዳያዩ ለወጣቶች እየመከረ።

ኪሱ ሲጎለምስ ከወንድሙ መኳንንት መለሰ ጋር ተማክሮ በአሜላ አክሲዮን ማህበር አማካኝነት የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍን ተቀላቅሎ ለአስር ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ቻለ። ብዙን ጊዜ ወጣቶች ላይ የሚስተዋለው ችግር ገንዘብ እያላቸው ሃሳብ ነውና ምን ትመክራቸዋለህ? አልኩት ባላለቀ የሚያሰኝ ወጉን እየኮመኮምኩ።

“በሕይወታችን ሪስክ ቴከር መሆን ካልቻልን የምንሻውን ስኬት ለማግኘት ያዳግተናል፤ ከዚህ ዓይነቱ የፍርሃት አባዜ ለመውጣት ስንቸገር መላ የምንፈጥር ስንናደድ ቶሎ የምንበርድ መሆን ይኖርብናል፤ አለበለዚያ ግን እንቅስቃሴ ካልታከለበት በአጭር ቁመት የረዘመ ልባችን ባለበት ይዳክርና ራሳችንን ሳናገኘው የነጋው ጀምበር ይጨልማል” ሲል ሞራልን የሚያበረታ ተስፋ መቁረጥን የሚረታ ፍቱን ሃሳብ ያዘለ ምክር ለገሰልኝ።

በአቋራጭ ለመክበር ለሚደክሙትስ ምን ትላቸዋለህ? አልኩት የወግ አቦላችን ሳይበርድ ፉት እያልኩ። “ለሰው ልጅ ጌጡ ሀገሩ አይደለች? ራስህንም አጥተህ ሀገርና ሕዝብህን ጎድተህ የምታገኘው ሀብት የማታ ማታ ትርፉ ክስረት ነውና ለሃሳባችሁም ቢሆን አትንገሩት” አለ ከሥራ ቦታው አገልግሎቱን ሽተው የመጡ ደንበኞቹን በትህትና እየተቀበለ።

እኔም ምስክርነታቸውን ልቀበል በእድሜ ጠና ያሉትን ደንበኛውን አናገርኳቸው። “ወጣት ቤዛ መለሰ የሚሸጠው ተግባቦትን ነው፤ ስንመጣ ወንበር ሰጥቶ እንዳንሰረቅ ተንከባክቦ ነው የሚሸኘን” አሉ የእናትነት ፍቅራቸው እየተፍለቀለቀ። ቀጥዬ ሃሳቡን ይሰጠኝ ዘንድ ከጎኑ የሚሠራውን ሲሳይ ዓለሙን ጠየኩት። ተምሪያለሁ ብሎ ትንሽ ሥራ ሳይንቅ መሥራቱ ሞራል እንደሆናቸውና ማህበራዊ መስተጋብሩ ጥሩ በመሆኑ እነሱንም አስተባብሮ ለወጣቶች ሥራ መፍጠር እንዲችሉ ስላገዛቸውም አሁን ላይ ሁሉም መልካም በሚባል ሁኔታ እንደሚገኙ አጫወተኝ።

ወንድሙ ልጅ ዓለም መለሰም ከሚሠራበት የመንግሥት ሥራ ለቆ ቤዛን ሲያግዝ በሥራው ውጤት ተስቦ የራሱን እንደጀመረ አወጋኝ። በቀጣይ ወጣት ቤዛ መለሰን የት እናግኘው? ስል የማብቂያ ጥያቄ አንስቼለታለሁና በሚሰጠኝ ሃሳብ ጽሑፌን በማሳረግ ልሰናበታችሁ።

“ትልቁ ቁም ነገር ሠርቶ ብዙ ማግኘት ሳይሆን ያገኙትንም ጥቂት ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም መቻል ነው፤ ስለዚህ ወጣት ወንድምና እህቶቼ በሱስ እንዳንጠመድ ራሳችንን ጠብቀን ጊዜን እንደ ሀብት ቆጥረን ከሠራን ካቀድነው በላይ በስኬት ጎዳና እንጓዛለን፤ በዚህ እሳቤ የጀመርኩት አላማዬ ከዚህ አድርሶኛልና በቀጣይ በየክልሎች ቅርንጫፍ ለመክፈት ዝግጅት ጨርሻለሁ” ሲል ሃሳቡን አሳረገ፡፡

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You